በዩክሬን ጦርነት እንዳይከሰት ያስችላሉ የተባሉ አምስት መንገዶች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ዩክሬን ውስጥ ጦርነት ተቀሰቀሰ ማለት በርካታ ችግሮችን ይዞ ነው የሚመጣው። ሩሲያ እውነትም እንደሚባለው ዩክሬንን የምትወር ከሆነ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸው የማይቀር ሲሆን ሚሊዮኖች ደግሞ ሊሰደዱ ይችላሉ።
ኢኮኖሚያዊ ኪሳራውም ቢሆን ቀላል የሚባል አይደለም።
ነገር ግን አሁንም ድረስ ሩሲያ ከዩክሬን አቅራቢያ የተሰማሩ ወታደሮቿን በማጠናከር ተደጋጋሚ ልምምድ ማድረግ ይዛለች። ሩሲያ በማንኛውም መልኩ ወደ ዩክሬን የምትገባ ከሆነ ምዕራባውያን አገራት ጠንከር ያለ እርምጃ እንደሚወስዱ እያስጠነቀቁ ነው።
ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችም ቢሆኑ እስካሁን አስተማማኝ የሚባል ውጤት ማምጣት አልቻሉም። ለመሆኑ ይህንን ውጥረት ማርገብ ይቻል ይሆን? ከተቻለስ የትኞቹ አማራጮች ውጤታማ ይሆናሉ?
1) ምዕራባውያን አገራት ፕሬዝደንት ፑቲንን ሊያግባቡ ይችላሉ
በዚህ አማራጭ የምዕራቡ ዓለም ጠንካራ አገራት ምናልባት ፕሬዝደንት ፑቲን ከጦርነት ይልቅ ቁጭ ብሎ መነጋገሩ ኪሳራን እንደሚያስቀር ሊያሳምኗቸው ይችላሉ።
ፕሬዝደንት ፑቲን ምንም እንኳን በወታደራዊው መስክ ትልቅ ድል ቢያስመዘግቡም የሚደርሰውን ሰብአዊ ኪሳራና ኢኮኖሚያዊ ድቀት ቆም ብለው እንዲያስቡ ሊያደርጋቸው ይችላል። የምዕራቡ ዓለም መሪዎችም የሚመጡት እዚህ ጋር ነው።
ፕሬዝደንት ፑቲን ይህንን መንገድ ከተከተሉ ምን እንደሚከሰትና ምን አይነት እርምጃዎች እንደሚወስዱ ካስረዷቸው ሁኔታውን ረገብ ሊያደርጉት ይችላሉ።
በሌላ በኩል የምዕራቡ ዓለም አገራት በዩክሬን ተቃዋሚ ኃይሎችን የሚደግፉ ከሆነ ለዓመታት የሚዘልቅ ጦርነት ሩሲያን ይጠብቃታል። ይህ ለፕሬዝዳንት ፑቲን ትልቅ ራስ ምታት ነው። ምናልባትም መሰል ክስተቶች በአገር ውስጥ ያላቸውን ድጋፍና ተቀባይነት ሊያሳጣቸው ይችላል።

የፎቶው ባለመብት, Russian defence ministry
2) የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን (ኔቶ) እና ሩሲያ ስምምነት ላይ ሊደርሱ ይችላሉ
ምዕራባውያን ኃይሎች በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ምንም አይነት ድርድር እንደማይኖር አሳስበዋል። በዋናነት የዩክሬን ሉአላዊነትና ዳር ድንበር መጠበቅ የሚለው ምንም ከድርድር ውስጥ የማይገባ እንደሆነ አስረግጠዋል። በሌላ በኩል ዩክሬን የኔቶ አባል የመሆን መብት እንዳላት ገልጸዋል።
ነገር ግን አሜሪካ እና ኔቶ እነዚህ ጉዳዮች ከግምት ውስጥ ገብተው ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚቻል ገልጸዋል።
በዚህ የስምምነት ሀሳብ መሰረት ሁለቱም አገራት ያሏቸውን የሚሳኤል ቁጥር መቀነስ፣ በሩሲያና በኔቶ መካከል መግባባትና መተማመን መፍጠር፣ ወታደራዊ ልምምዶችን በግልጽ ማካሄድ እንዲሁም ሚሳኤሎች ያሉባቸውን ቦታዎች ማሳወቅ የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው።
ነገር ግን ሩሲያ በአብዛኛዎቹ ቅድም ሁኔታዎች አትስማማም። ምክንያቱም በሩሲያ መከራከሪያ መሰረት ዩክሬን የኔቶ አባል እንድትሆን የሚፈቀድላት ከሆነ የደኅንነት ስጋት ያጋጥማታል።
ነገር ግን በሌላ በኩል የኔቶ ሚሳኤሎች ቁጥር በእጅጉ የሚቀነስ ከሆነ ሩሲያን ከሚያሳስቧት ትላልቅ ጉዳዮች መካከል አንደኛው ተቀረፈ ማለት ነው።
እስካሁን ባለው አካሄድ ፑቲን ያሸነፉ ይመስላል። ምክንያቱም የአውሮፓ አገራት ወታደራዊ ንንግር እያደረጉ የሚገኙት በሩሲያ ቅድመ ሁኔታዎች ላይ ተመስርተው ነው።
3) ሩሲያ እና ዩክሬን የሚንስኩን ስምምነት ሊያድሱት ይችላሉ
ይህ ስምምነት በአውሮፓውያኑ 2014 እና 2015 ላይ በቤላሩስ ዋና ከተማ ሚኒስክ በድርድር የተገኘ ነው። በወቅቱ በምሥራቃዊ ዩክሬን ሩሲያ የምትደግፋቸው አማጺያን ከመንግሥት ጋር ከፍተኛ ውጊያ ውስጥ ገብተው ነበር።
ምንም እንኳን ስምምነቱ ውጤታማ ባይሆንም ሌላው ቢቀር ለጊዜውም ቢሆን የተኩስ አቁም እንዲደረግና ጉዳዩ ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲያገኝ ጥረቶች እንዲጀመሩ አድርጓል።
አንዳንድ ምዕራባውያን ፖለቲከኞች የሚኒስኩን ስምምነት እንደገነና ማስቀጠል አሁን ለተፈጠረው ውዝግብ መፍትሄ ሊሆን እንደሚችል እየጠቆሙ ነው።
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮንም ቢሆኑ የዚህ ሀሳብ ደጋፊ ናቸው። "የሚኒስክን ስምምነት ማስቀጠል ሰላምን ለማስፈን ብቸኛው መንገድ ነው" ብለዋል።
ነገር ግን የሚኒስኩ ስምምነት በጣም የተወሳሰበና ከመግባባት ላይ ለመድረስ አስቸጋሪ የሆነ ነው። ሩሲያ ዩክሬን ውስጥ ፑቲንን የሚደግፉ ፖለቲከኞች የሚሳተፉበት ምርጫ እንዲካሄድ ፍላጎት አላት።
በሌላ በኩል ዩክሬን ደግሞ ሩሲያ ያስታጠቀቻቸው ወታደሮች ትጥቅ እንዲፈቱና የሩሲያ ወታደሮች አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ ትፈልጋለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
4) ልክ እንደ ፊንላንድ ዩክሬንም ገለልተኛ አገር ልትሆን ትችላለች
ምንም እንኳን እውነትነቱን ማረጋገጥ ባይቻልም አንዳንድ የፈረንሳይ ባለሥልጣናት ዩክሬን ፊንላድን እንደ ምሳሌ እንድትወስድና ገልተኛ አገር እንድትሆን ሀሳብ ማቅረባቸው ተገልጿል።
ፊንላንድ በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ነበር ገልተኛ አገር መሆኗን ያወጀችው። ፊንላንድ ራስ ገዝ፣ ሉአላዊ እና ዴሞክራሲያዊ አገር ነች። ነገር ግን የኔቶ አባል አይደለችም።
ጥያቄው ይህ ሀሳብ ዩክሬንን ያስደስታት ይሆን ወይ የሚለው ነው። ይሄኛው አማራጭ ወታደራዊ እሰጥ አገባዎችን በእጅጉ ይቀንሳል። በሌላ በኩል ፕሬዝዳንት ፑቲን ለዓመታት ዩክሬን የኔቶ አባል እንዳትሆን ሲከራከሩ የነበረው ጉዳይ መፍትሄ ያገኛል ማለት ነው።
ዩክሬን ገለልተኛ አገር የምትሆን ከሆነ በአውሮፓ ያላትን ቦታ በእጅጉ የሚያሳንሰው ሲሆን የአውሮፓ ሕብረት አባል ለመሆን የምታደርገውንም እንቅስቃሴ ያበላሽባታል።
5) አሁን ያለው ሁኔታ ብዙም ሳይባባስ ባለበት ሊቀጥል ይችላል
ምናልባት አሁን ላይ ያለው መካረርና ፍትጊያ በጊዜ ብዛት እየተቀዛቀዘና አሳሳቢነቱ እየቀነሰ ሊሄድ ይችላል። ሩሲያ ወታደራዊ ልምምዱ አብቅቷል በማለት ወታደሮቿን ከዩክሬን ድንበር አቅራቢያ ቀስ በቀስ ልታስወጣ ትችላለች።
ነገር ግን ምናልባት ያልታሰበ ነገር ቢከሰት በሚል በርካታ ዘመናዊ ወታደራዊ መሳሪያዎች ባሉበት ሊቀመጡ ይችላሉ።
ሞስኮ አሁንም ዶንባስ የሚገኙትን አማጺያንን መደገፏን የምታቆም አይመስልም። በሌላ በኩል ደግሞ በሩሲያ ተጽዕኖ ስር ያለው የዩክሬን ኢኮኖሚ መረጋጋት ሊያቅተው እንደሚችል ይገመታል።
በጎን ደግሞ የምዕራቡ ዓለም አገራት በምሥራቅ አውሮፓ የኔቶን እንቅስቃሴና ተጽዕኖ ለመጨመር ይንቀሳቀሳሉ። ፖለቲከኞቻቸውና ዲፕሎማቶቻቸው ከሩሲያ አቻዎቻቸው ጋር ተደጋጋሚ ንግግሮችን ሊያደርጉ የሚችሉ ሲሆን እዚህ ግባ የሚባል ለውጥ ያመጣሉ ተብሎ ግን አይገመትም።
በዚህ አካሄድ ዩክሬን እንደ ሀገር በጣም ልትቸገር የምትችል ቢሆንም ከከፋ ጦርነት ግን ትድናለች። በጊዜ ሂደትም ጉዳዩ ከዓለም መነጋገሪያነት ወደ ተረሳ ጉዳይ ተቀይሮ ለዓመታት ሊንከባለል ይችላል።
ወጣም ወረደ በዚህ ውዝግብ ውስጥ ትልቋ ተጎጂ ዩክሬን ነች። ስለዚህ ዋነኛውና ትልቁ ጥያቄ የከፋ ጦርነት እንዳይቀሰቀስ ምን ማድረግ ይቻላል የሚለው ነው። አሁን ላይ የንግግር በሮች የተከፈቱ ቢመስሉም መጨረሻውን መገመት ግን ከባድ ነው።















