ሩሲያ ዩክሬን ድንበር ላይ ወታደር እያሰፈረች ያለችው ለምንድነው?

የዩክሬን ፕሬዚዳንት ወታደሮችን እየጎበኙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ሩሲያ ባልተለመደ ሁኔታ ወታደሮቿን ወደ ዩክሬን ድንበር ማስጠጋቷ አዲስ ጦርነት እንዳይቀሰቀስ ፍርሃት ፈጥሯል፡፡

ሩሲያ በበኩሏ ዜጎቼን ለመታደግ ነፍጥ ላነሱ ተገንጣይ ቡድኖች እገዛ አደርጋለሁ ብላለች፡፡

አንድ የሩሲያ ከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣን እንዲያውም ‹ሞስኮ በምሥራቅ ዩክሬን ሩስኪ ተናጋሪ የሆኑ ተገንጣዮችን ለመደገፍ ሁሉንም እገዛ ታደርጋለች› ብለዋል፡፡

ባለሥልጣኑ ጨምረውም ዩክሬን በተገንጣዮቹ ላይ እጇን ካነሳች ደግሞ ሞስኮ ሳታወላውል ጦር ታዘምታለች ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በሩሲያ የሚደገፉ ተገንጣዮች በምሥራቅ ዩክሬን ከመንግሥት ጋር ግጭት ውስጥ ከገቡ ሰነባብተዋል፡፡

ይህን ተከትሎ ሩሲያ ወታደሮቿን ወደዚያው ድንበር ማስጠጋቷን ገፍታበታለች፡፡

ባለሥልጣኑ ዲምትሪ ኮዛክ ሩሲያ ዜጎቿን የመጠበቅ ግዴታና ኃላፊነት አለባት ብለዋል፡፡

‹‹ሁሉም ነገር የሚወሰነው በዩክሬን ጠብ አጫሪነት መጠን ነው› ሲሉም ሊወሰድ ስለሚታሰበው እርምጃ ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡

እኚሁ ባለሥልጣን ዩክሬን በሩሲያ ተናጋሪ ሕዝቦች ላይ እጇን ካነሳች ምናልባትም የዩክሬን መጨረሻ ሊሆን ይችላል ሲሉ ነገሩ የት ድረስ ሊሄድ እንደሚችል አስገንዝበዋል፡፡

ዩክሬን ላይ ከተኮስን እግር ላይ ሳይሆን ፊት ላይ ነው የሚሆነው ሲሉም በወታደራዊ ቋንቋ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል፡፡

ሩሲያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወታደሮቿን ወደ ዩክሬን ድንበር ብታስጠጋም ለክፋት እንዳልሆነ ስትናገር ነበር የቆየችው፡፡

የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ጄን ወደ ድንበር የተጠጉ የሩሲያ ወታደሮች ብዛት በ2014 ከነበሩት በላይ ናቸው ብለዋል፡፡ ሩሲያ በዚህ ዓመተ ምሕረት ዩክሬንን መውረሯ አይዘነጋም፡፡

ዋይት ሐውስ ጉዳዩን አሳሳቢ ብሎታል፡፡

አንድ በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች እየተጋራ የሚገኝ ተንቀሳቃሽ ምሥል ሩሲያ ከባባድ መሣሪያዎችን ወደ ዩክሬን ድንበር ስታመላልስ የሚያሳይ ነው፡፡

በዩክሬን ወታደሮችና በሩሲያ የሚደገፉት ምሥራቅ ተገንጣዮች መካከል በዶንባስ ግዛት ወታደራዊ ግጭቶች ባለፉት ወራት ጨምረው ነበር፡፡

ባለፈው ሐሙስ አንድ የዩክሬን ወታደር በግጭት መሞቱ በዚህ ዓመት የተገደሉ ወታደሮችን ቁጥር 25 አድርሶታል፡፡ ባለፈው ዓመትም በተመሳሳይ በግጭቱ 50 ወታደሮች ሞተው ነበር፡፡

የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲመር ዘለኔስኪ ሐሙስ ወታደራቸው ከተገደለ በኋላ አካባቢውን መጎብኘታቸው ሌላ ውጥረት ፈጥሯል፡፡

ያንኑ ቀን ሐሙስ ነገሮች መስመር እንዳያልፉ በሚል የጀርመኗ መራሒተ መንግሥት አንግላ ሜርክል ወደ ፑቲን ስልክ መተው ነገር እናብርድ ሲሉ ተማጽነዋል፡፡

ሜርክል ሩሲያ ወታደሮቿን ከድንበር ዘወር እንድታደርግ ነበር ቪላድሚር ፑቲንን የጠየቁት፡፡

በ2014 ሩሲያ የዩክሬን አካል የነበረችውን ክሪሚያ ግዛትን በኃይል በቁጥጥር ሥር ማድረጓ ይታወሳል፡፡

ይህ ክስተት ምዕራባዊያንን ፍጹም ያስደነገጠ ነበር፡፡ የሩሲያን ወረራ ተከትሎም የአውሮጳ ኅብረትና አሜሪካ በሩሲያ ላይ ከባድ ያሉትን ማዕቀብ ጥለው ቆይተዋል፡፡

ይህን የሩሲያን ወረራ ተከትሎ እነዚህ ተገንጣዮች በዶንባስ ክልል የዶኔስክ እና ሉሃነስክ ግዛትን ተቆጣጥረዋል፡፡ በዶንባስ በአመዛኙ የሩስኪ ተናጋሪዎች ናቸው የሚበዙት፡፡

ሩሲያና ዩክሬን በነበራቸው የተራዘመ ግጭት ቢያንስ 14ሺ ወታደሮች እንደሞቱ ይገመታል፡፡