በጠለፋ 'ጋብቻ' የተገደለችው ሴት ጉዳይ ከፍተኛ ቁጣን ቀሰቀሰ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በጠለፋ ጋብቻ ለመፈፀም በሚል አንዲት ሴት ተጠልፋ መገደሏ ከፍተኛ ቁጣን አስነስቷል።
ይህ የተፈፀመው በእስያ በምትገኘው ካይሪጊስታን በምትባለው አገር ነው።
የ27 አመት እድሜ ያላት አይዛዳ ካናትቤኮቫ የተጠለፈችው ሰኞ እለት ሲሆን ሶስት ወንዶችም ገፍተው መኪና ውስጥ ከተቷት። ከነዚህ ውስጥ አንደኛው በግድ ሊያገባት የፈለገው ሰው ነው ተብሏል።
የጠለፋው ቪዲዮ በማህበራዊ ሚዲያ ገፆች በከፍተኛ ሁኔታ ቢጋራም ፖሊስ መኪናውን ለማግኘት አዳጋች ሆኖበት ነበር።
አይዛዳ ከተጠለፈች ከሁለት ቀናት በኋላ አስከሬኗ አንድ ከጥቅም ውጭ በሆነ መኪና ውስጥ ሊገኝ ችሏል።
አስከሬኗ የተገኘው በአንድ እረኛ አማካኝነት ከመዲናዋ ቢሽከክ ወጣ ብሎ በሚገኝ ሜዳ ነው።
ጠልፎ ገድሏታል ተብሎ የሚታመነው ግለሰብ አስከሬንም በዚያው ስፍራ ተገኝቷል።
ፖሊስ የግለሰቡን አሟሟት አስመልክቶ እንደሚለው የሞተው በቢላ እንደሆነና ራሱንም እንደገደለ ፍንጮች ማግኘቱን ነው።
የሟቿ ቤተሰቦች እንደተናገሩት ልጃቸው ግለሰቡን እንደምታውቀውና ከዚህ በፊትም ትንኮሳዎች ሲያደርስባት እንደነበርና ከዚህ ተግባሩም እንዲታቀብ መጠየቃቸውን ነው።
ግለሰቧን በመጥለፍ የተባበሩት ሌሎች ሶስት ወንዶች በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንደዋሉ የአገሬው ሚዲያ ዘግቧል።
የግለሰቧን ግድያ ተከትሎም በመቶዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች በያዝነው ሳምንት ሃሙስ "አሳፋሪ" ነው በማለት በቁጣ ሲጮሁ ተሰምተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የአገሪቱ የውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር እንዲለቁ ጥሪ አቅርበዋል።
በአገሪቷ ውስጥ የጠለፋ ጋብቻ በከፍተኛ ሁኔታ ተስፋፍቷል።
ምንም እንኳን አንዳንዶች የጠለፋ ጋብቻ የካይርጊዝ የቀደመ ባህል ነው ብለው ቢከራከሩም ተመራማሪዎች በበኩላቸው በመካከለኛ እስያዊቷ አገር መስፋፋትን ያሳየው ከጥቂት አስርት አመታት በፊት ነው ይላሉ።
በአውሮፓውያኑ 2013 የጠለፋ ጋብቻ ህገወጥ ሆኖ በህግ ቢደነገግም ሪፖርት የሚያደርጉ ሴቶች ቁጥር በጣም አናሳ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ለዚህም እንደ ምክንያትነት የሚጠቀሰው ሊደርስባቸው የሚችለውን አፀፋዊ ምላሽ በመፍራት እንደሆነ ተነግሯል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በአገሪቷ ከሚፈፀሙ አምስት ጋብቻዎች መካከል አንዱ አስገዳጅ በሆነ ሁኔታ ሴቷ ተጠልፋ እንደሆነ ነው።












