ወንዶች ላስረገዟቸው ሴቶች የእርግዝና ወጪ እንዲጋሩ የምታስገድደው ግዛት

በአሜሪካ ዩታህ ግዛት እርግዝና ከተከሰተ በኋላ ወንዶች እንደ ጭስ ብን ብለው መጥፋት አይችሉም። እያንዳንዷን የእርግዝና ወጪ ይጋሯታል።
ይህ ግዴታ አባቶችንም፣ የፍቅር ተጣማሪዎችንም፣ የአንድ ጊዜ የከንፈር ወዳጆችንም ለጽንሱ መፈጠር ምክንያት እስከሆኑ ድረስ የሚመለከታቸው ነው።
የወጪ መጋራቱ ታዲያ ከእያንዳንዱ በእርግዝና ወቅት ከሚያስፈልገው መድኃኒት ጀምሮ፣ ለ9 ወራት የሚዘልቁ የምግብ፣ የጤናና ተያያዥ ጉዳዮችን ያካትታል። የወሊድ ወጪንም አባት የግድ ይጋራል።
ይህ አዲስ ሕግ በአሜሪካ ሲተገበር ዩታህ ግዛት የመጀመሪያዋ ናት።
የዚህ ሕግ ደጋፊዎች አዲሱን ሕግ "የአሜሪካ ሴቶች የሚደርስባቸውን መከራና ፍዳ በትንሹ የሚያቀል" ሲሉ አሞካሽተውታል።
ይህ ደንብ የጸደቀው በሪፐብሊካንም በዲሞክራቶችም የጋራ ድጋፍ አግኝቶ ነው።
ሕጉ ከጸደቀ በኋላ ግን በአሜሪካ የወላጆች ወጪ ላይ አዲስ ውይይት እንዲከፈት ምክንያት ሆኗል።
በተለይም ዩታህ ግዛት ጽንስን የማቋረጥ መብትን ተፈጻሚ ለማድረግ ሴቶች ማሟላት ያለባቸውን ዝርዝር ሁኔታ እያጠበቀች ከመምጣቷ ጋር ተያይዞ አዲሱ ሕግ ብዙ እያነጋገረ ነው።
ሕጉ ምን ይላል?
የዩታህ የእርግዝና ወጪ መጋራት ሕግ ማንኛውም የተፈጥሮ አባት ለልጁ እናት ጽንሱ ከተፈጠረ ጊዜ ጀምሮ ግማሽ ወጪን እንዲሸፍን ያስገድዳል።
ይህም የኢንሹራንስ ወርሃዊ ክፍያን እና ሌሎች ማናቸውም የሕክምና ወጪዎችን የሚጨምር ነው።
ይህ ቀጥታ ወጪ መጋራቱ የተረገዘው/ችው ልጅ ከ9 ወር እርግዝና በኋላ የሚመጣውን የማዋለጃ ዋጋንም ይጨምራል።
ለአንዲት አሜሪካዊት እርጉዝ ሴት አንድ ልጅ አርግዞ መውለድ በገንዘብ ደረጃ በአማካይ 4 ሺህ 500 ዶላር ያስወጣታል።
ይህ የኢንሹራንስ ወጪን ሳይጨምር ከኪሷ ብቻ የምታወጣው የገንዘብ መጠን ነው።
ኢንሹራንስ ለሌላቸው እርጉዝ ሴቶች ይህ ወጪ እጥፍ ይሆናል። እንደ ፌይር ሔልዝ ጥናት ከሆነ ብዙውን ጊዜ የመድኅን ሽፋን አልባ እርጉዝ ሴቶች አርግዘው እስኪወልዱ 10 ሺህ ዶላር አይበቃቸውም።
በዚህ ጊዜ ፍቅረኛ/ባል መጠርያው ማንም ይሁን ማን 'የጽንሱ አባት' ከዚህ ቀደም ወጪውን ለመጋራት አይፈቅዱ ስለነበር ሁኔታው ሴት አሜሪካዊያን ላይ ከባድ ጭናን ያሳርፍ ነበር።
በአዲሱ ሕግ ግን ይህ ወጪ የባል/የፍቅረኛ ወይም የአንድ አፍታ ወዳጅም ሊሆን ይችላል 'የጽንሱ አባት' ይጋራዋል።
ለሴቷ እርግዝና ምክንያት የሆነው ወንድ ቢክድ ወይም ማንነቱ ለጊዜው የማይታወቅ ከሆነና በምርመራ ሂደት ላይ ካለ ወጪ መጋራቱ ለጊዜው እንዲዘገይ ተደርጎ የጽንሱ ባለቤት ሲታወቅ፣ ወይም ጽንሱ ሲወለድ ወጪዎች ተሰልተው ይቀርቡለታል።
ሆኖም እርጉዝ ሴቶች የልጁን ባል እገዛ የማይሹ ከሆነ ለአባት ይህ ጨርሶዉኑ እንዳይነገረው፣ ወጪም እንዳይነካው ሊያደርጉ መብቱ አላቸው።
ይህ ሆኖ ሳለ ግን እርጉዝ ሴቶች ጽንሱን ማቋረጥ ቢፈልጉ ወጪው አባትን አይመለከተውም።
ሴቷ ጽንስ እንዲቋረጥ ስትወስን 'የጽንሱ አባት' ወጪ ሸፍን ተብሎ አይገደድም። ለጽንስ ማቋረጡም የሚሆን ገንዘብ ክፈል ተብሎ በሕግ አይገደድም።
ሆኖም የእናትዬው ሕይወት አደጋ ላይ ከሆነ ወይም ጽንሱ የተፈጠረው በእናት ፈቃድ ካልሆነ ወጪውን ወንዱ እንዲሸፍነው ሊደረግ ይችላል።

ይህ ወጪ የመጋራት ሕግ ከመጪው ግንቦት 5 ጀምሮ በዩታህ ግዛት ተግባራዊ ሆኖ ይሠራበታል።
በአሜሪካ አሁን ባለው አማካይ ዋጋ ለአንዲት ሴት ጽንስ ማቋረጥ ብቻ በትንሹ 1ሺህ ዶላር ያስወጣታል።
ይህንን ሕግ በማስተዋወቅና ሕግ እንዲሆንም ከፍተኛ ድጋፍ ካደረጉ እንደራሴዎች መካከል ብራዲ ብራመር ይገኙበታል።
"ስለ ጽንስ ማቋረጥ ጉዳይ ሳንጨቃጨቅ እርጉዝ ሴትና ልጇን ማገዝ እንደሚቻል ያሳየ ሕግ ነው" ብለዋል ብራመር ለቢቢሲ። እንደራሴ ብላመር የጽንስ ማቋረጥን የሚቃወሙ ሪፐብሊካን ናቸው።
የጽንስ ማቋረጥ ደጋፊዎች ግን ይህን ይኮንናሉ።
ጽንስ የምታቋርጥ ሴት የግድ ተስፋ በመቁረጥ አይደለም ድርጊቱን የምትፈጽማው። ጽንስ ማቋረጡ ምርጫዋ ስለሆነ እንጂ ይላሉ።
በአሜሪካ 24 ከመቶ የሚሆኑ ሴቶች ዕድሜያቸው 45 እስኪደርስ ድረስ የጽንስ ማቋረጥ ተግባር ይፈጽማሉ ይላል አንድ ጥናት። ከነዚህ መሀል ግማሾቹ የሚሆኑት ከድህነት ወለል በታች ባለ ሁኔታ የሚኖሩ ናቸው።
ጽንስን ማቋረጥ መብት ነው ብለው የሚከራከሩ ይህን አዲሱን የዩታህ ግዛት ሕግ በበጎ ይመለከቱታል።
ሆኖም ይህ ሕግ ነገሩን የተመለከተበትን መንገድ አልወደዱትም።
ከዚህ ይልቅ የተሻለ የጤና መድኅን አቅርቦት፣ የጋራ የቤተሰብ ጤና አገልግሎት፣ ተከፋይ የቤተሰብ የእረፍት ፍቃድ የመሳሰሉት በፖሊሲ ደረጃ ቢተኮርባቸው ለሴቷ ሰፊ አማራጭ የሚሰጡ ናቸው ይላሉ።
ይህ ወንዱ የእርግዝና ወጪን እንዲጋራ ማድረግ ሕግ ብቻውን ለሴቷ የሚፈይድላት ነገር እምብዛምም ነው ባይም ናቸው።
የአሜሪካ የእርሻና ቤተሰብ ኤጄንሲ እንዳወጣው መረጃ ከሆነ በአሜሪካ አንድ ቤተሰብ አንድ ልጅን ለማሳደግ (ልጁ/ልጅቷ 17 ዓመት እስኪደርሱ ድረስ) እስከ 233 ሺህ ዶላር ድረስ ያስፈልጋቸዋል።
ይህ ስሌት የ2015 ዓ.ም የኑሮ ሁኔታ ላይ ተመሥርቶ የተሠራ ነው። ይህ ወጪ የኮሌጅ ትምህርት ክፍያን የማይጨምር ነው።
ዩታህ ጽንስ ማቋረጥን በእጅጉ የማታበረታታ ግዛት ናት። ይህ አዲሱ ሕግም ለዚሁ ተብሎ የተቀመመ ዘዴ ነው ይላሉ የጽንስ ማቋረጥ መብት ተሟጋቾች።
ሜሪሊ ቦያክ ከነዚህ አንዱ ናቸው። "የዚህ ሕግ ዓላማ ጽንስ ማቋረጥን ከሴቷ አእምሮ እንዲፋቅ ማድረግ ነው" ሲሉ ለቢቢሲ አስተያየት ሰጥተዋል።
በአሜሪካ በርካታ ግዛቶች ጽንስ በማቋረጥ መብት ላይ ሁሉን አቀፍና መልከ ብዙ ቅድመ ሁኔታዎችን በማስቀመጥ ነገሩን ለሴቶች ከባድ እያደረጉት ይገኛሉ።
ዩታህ በ2019 ያሳለፈችው ሌላ ሕግ በተለዩ ሁኔታዎች ካልሆነ በስተቀር ልጅ ከተረገዘ ከ18 ሳምንት በኋላ ጽንስ ማቋረጥን ይከለክላል። ለማቋረጥ የፈለጉ ሴቶች ከባለሙያ ተከታታይ ምክር ማግኘት አለባቸው ሲልም ያስገድዳል።
ሴቶች ጽንሱን በማቋረጥ ከጸኑ ድርጊቱን ከመፈጸማቸው በፊት 72 ሰዓት ሐሳባቸውን እርግፍ አድርገው እንዲተዉ የሚያደርግ ሌላ የምክር አገልግሎት የማግኘት ግዴታ ተጥሎባቸዋል።
ይህንን ሲያሟሉ ብቻ ነው 72 ሰዓት ጠብቀው ጽንስ ማቋረጥ የሚችሉት።
ባለፈው ዓመት ደግሞ 'ትሪገር ባን' የሚል ስም ያለው አዲስ ሕግ ጸድቋል። ይህም ጽንስ ማቋረጥ አገልግሎት እንዲሰጡ የተፈቀደላቸው ጥቂት ክሊኒኮች ጽንሱን የመቅበር ግዴታን ጥሎባቸዋል።
ሴቶች ጽንስ ማቋረጥ የሚችሉባቸውን ዕድሎችም በእጅጉ የሚያጠብ ሕግ ወጥቷል።
ከ18 ዓመት በታች ያሉ ሴቶች ጽንስ ለማቋረጥ ወላጆቻቸው ስምምነት መፈረም አለባቸው።
በ2017 ብቻ በአሜሪካ ከ800 ሺህ በላይ ሴቶች በጤና ተቋማት የጽንስ ማቋረጥ አገልግሎት አግኝተዋል። ከእነዚህ ውስጥ 3 ሺህ የሚሆኑት የዩታህ ግዛት ነዋሪዎች ናቸው።













