በዩኒቨርስቲ ቆይታዋ ወልዳ በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቀችው

የፎቶው ባለመብት, Fozia Jemal
ፎዚያ ጀማል በ 2010 ዓ.ም ኦዳ ቡልቶም ዩኒቨርስቲ ተመድባ ስትሄድ ገና አዲስ ሙሽራ ነበርች።
በዩኒቨርስቲው የኢኮኖሚክስት ትምህርት ክፍል እንድትማር ስትመደብ ነፍሰጡር መሆኗን አወቀች።
በዚህ ምክንያት ግን ምህርቷን ማቋረጥ አልፈለገችም።
በእርግዝናዋ ወራት በዙሪያዋ ምን አማረሽ? ምን ይምጣልሽ? የሚል ወላጅ እና ባል ባይኖርም፤ እንደ ሌሎች የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች በካፌም በቤተመጻህፍት በትምህርት ክፍልም እኩል እየተገኘች ትምህርቷን ተከታትላለች።
ፎዚያ የመጀመሪያ ዓመት ትምህርቷን ስታጠናቅቅ የወሰደቻቸውን ኮርሶች በአጠቃላይ ኤ ያመጣች ስትሆን ሴት ልጅ ወልዳ ለመሳምም በቅታለች።
ፎዚያ ከዚያ በኋላ በአንድ እጇ ልጇን አቅፋ በሌላ እጇ መጽሐፍ ዘርግታ ትምህርቷን በትጋተት ተከታትላለች።
ትጋቷም ፍሬ አልባ አልነበረም።
የሶስቱን ዓመት ትምህርት አጠናቅቃ ስትመረቅ ከወሰደቻቸው 38 ኮርሶች መካከል 31 A+ ሰባቱን ደግሞ A አምጥታለች።
ፎዚያ ጀማል ከኦዳ ቡልቶም ዩኒቨርስቲ በ2012 ተመራዊ የነበረች ቢሆንም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በ2013 ጥር ወር መጀመሪያ ላይ ዓ.ም የመጀመሪያ ዲግሪዋን በከፍተኛ ማዕረግ አጠናቅቃ ተመርቃለች።
የኦዳ ቡልቶም ዩኒቨርስቲ ከእርሷ ጋር አንድ ላይ 929 ተማሪዎችን አስመርቋል።
ምዕራብ ሐረርጌ ቦኬ ወረዳ የተወለደችው ፎዚያ የ11ኛ ክፍል ተማሪ እያለች ትዳር መመስረቷን ለቢቢሲ ትናገራለች።
በሶስት ዓመት የዩኒቨርስቲ ቆይታዋ አንድ ዓመት ነፍሰጡር ሆና ሌላኛውን ዓመት ደግሞ ጨቅላ ልጇን እያሳደገች ስትማር የተለያዩ ፈተናዎች የነበሩ ቢሆንም ዓላማዋና ትኩረቷን በአንድ ጉዳይ ላይ በማድረግ በድል ማጠናቀቋን ትናገራለች።
"ሥራዬ ነው ብለህ ራስህን አሳምነህ ከጀመርክ የማይቻል ነገር የለም። እኔም ነፍሰጡር መሆኔ በውጤቴ ላይ ተጽዕኖ ማሳደር የለበትም በማለት በርትቼ ሳጠና ነበር፤ ነፍሰጡር ሆኖ በትምህርት ፈተና ውስጥ ማሳለፍ በዚያ ላይ ልጅን እያሳደጉ ፈታኝ ቢሆንም ያሰብኩትን አሳክቻለሁ።
የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ ሳለች እርግዝና ተጨማሪ ኃላፊነት ይዞባት ስላመጣ በእርግዝናና ልጅ ማሳደግ ነጥቧ እንዳይቀንስ ከበፊቱ በበለጠ ስታነብ እንደቆየች ታስታውሳለች።
ከዚህ ስኬቷ ጀርባም የባለቤቷ ድጋፍ ብዙ እንደነበር ለቢቢሲ ገልጻለች።

የፎቶው ባለመብት, Fozia Jemal
ለዚህ ሁሉ ስኬቴ የባለቤቴ ሚና ትልቅ ነው የምትለው ፎዚያ "ባለቤቴ እውነቱን ለመናገር የተለየ ሰው ነው፤ እርሱ ለትምህርቴ ልዩ ትኩረት ይሰጣል። ልክ ለእርሱ እንደምማር ነው የሚወስደው፤ ከእኔ በላይ እርሱ ነው የሚጨነቀው። በሁሉም በኩል በጣም ያግዘኛል። እርሱ የስኬቴ ምስጢር ነው።"
ፎዚያ ሶስት ዓመት ኦዳ ቡልቶም ዩኒቨርስቲ በቆየችበት ወቅት ላስመዘገበችው ከፍተኛ ነጥብ ሁለት ዋንጫ እና አንድ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸልማለች።
እቅዴን ፈጣሪ ረድቶኝ ስለተሳካልኝ፣ ያሰብኩትን ስላሸነፍኩ በማለት የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ እያለች የወለደችውን ልጅ ሞኔት [ Mooneet] ብለው እንደሰየሟት ትናገራለች።
ሞኔት የሚለው ወደ አማርኛ ሲመለስ አሸነፍን ማለት እንደሆነ ትናገራለች።
ሴቶች ስኬታማ ለመሆን ቆራጥ መሆና ያስፈልገናል የምትለው ፎዚያ፣ ኋላ ቀር የሆኑትን አስተሳሰቦች በመተው የስኬት መንገዶችን ማየት አለብን በማለት ሴቶችን ትመክራለች።
"ምንም አንችልም ብለን ራሳችንን ማሳመን የለብንም። አንችልም ብለን ራሳችንን ካሳመንን እውነትም አንችልም። እችላለሁ ብሎ ያመነ አእምሮ ይችላል። በሥራዬ ከግብ እደርሳለሁ ብላ የምትሰራ እደርሳለሁ ያለችው ቦታ ለመድረስ የሚከለክላት የለም " ትላለች።
ፎዚያ በአሁኑ ጊዜ በኦዳ ቡልቶም ዩኒቨርስቲ በኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል በመምህርነት ተቀጥራለች።
ለወደፊት ደግሞ ትምህርቷን ማሳደግ እና ባገኘችውና እውቀት ኅብረተሰቡን የማገልገል ፍላጎት እነዳላት ትናገራለች።ፎዚያ ጀማል በ 2010 ዓ.ም ኦዳ ቡልቶም ዩኒቨርስቲ ተመድባ ስትሄድ ገና አዲስ ሙሽራ ነበርች።















