ትምህርት፡ አራት ሜዳሊያ እና ዋንጫ የተሸለመችው ቆንጂት

ቆንጅት ሐብታሙ

የፎቶው ባለመብት, KONJIT HABTAMU

የምስሉ መግለጫ, ቆንጅት ሐብታሙ

ቆንጂት ሐብታሙ ትባለላች። ተወልዳ ያደገችው በሰሜን ሸዋ ጊዳ ሲሆን የከፍተኛ ትምህርቷን ያጠናቀቀችው ዘንድሮ ነው። ቆንጂት በመቱ ዩኒቨርስቲ ቆይታዋ ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገቧ ሶስት ሜዳሊያ እና አንድ ዋንጫ ለመሸለም በቅታለች።

ለስኬቷ ምክንያት የሆነውንና የወደፊት እቅዷን በማስመልከት ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ባደረገች ወቅት " ፊደል ካልቆጠሩ የገጠር ቤተሰብ መገኘቴ ለስኬቴ እንቅፋት አልሆነብኝም" ብላለች።

"ተወልጄ ያደግኩት ገጠር ነው። ቤተሰቦቼም ፊደል የቆጠሩ አይደሉም። እኔ እንድማር ግን አብረውኝ ለፍተዋል። ከተማረ ቤተሰብ ይልቅ ተምሬ ትልቅ ሰው እንድሆንላቸው ያስቡልኛል" በማለት ቤተሰቦቿ ያደረጉላትን ትገልጻለች።

ቆንጂት ከመቱ ዩኒቨርስቲ በአፕላይድ ባዮሎጂ የትምህርት ዘርፍ ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገቧ የተለያዩ ሽልማቶችን ለማግኘት በቅታለች።

"ያስመዘገብኩት ውጤት 3.96 ነው" የምትለው ቆንጂት፣ በመቀጠልም "እንደ ኮሌጅ አንደኛ በመውጣቴ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸልሜያለሁ። እንዲሁም ከሴቶች አንደኛ በመሆን ሌላ ተጨማሪ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸለምኩ" በማለት ታስረዳለች። ሶስተኛ ወርቅ ያገኘችው ደግሞ ከአጠቃላይ መቱ ዩኒቨርስቲ ሴት ተማሪዎች አንደኛ በመውጣት መሆኑን ገልጻለች።

ከዚህ በተጨማሪ ከአጠቃላይ ዩኒቨርስቲው በሶስተኛ ደረጃ በመገኘቷ የነሐስ ሜዳሊያ እና በአጠቃላይ በዩኒቨርስቲው ካሉ ተማሪዎች በመላቋ ደግሞ ዋንጫ አግኝታለች።

በዩኒቨርስቲ ቆይታዋ ከፍተኛ ውጤት ለማስመዝገብ ያበቋትንም ነገሮች ስታስረዳ " ዩኒቨርስቲ እንደገባሁ እቅድ በማውጣት ጊዜዬን በአግባቡ ተጠቅሜ ነበር። ክፍልም በአግባቡ እከታተል ነበር። አጠቃላይ ትኩረቴ በትምህርቴ ላይ በማድረግ ነበር ስከታተል የነበረው" ትላለች።

በመቀጠልም "የተማርነውን መከለስ ብቻም ሳይሆን ወደ ፊት ልንማራቸው የምንችላቸውን ቀድሜ በማንበብ እዘጋጅ ነበር።" በማለት ልምዷን መለስ በማለት ታስታውሳለች።

የዩኒቨርሰቲ ቆይታ በራስ ሕይወት ላይ ትኩረት በማድረግ ከተሰራ የወደፊት ሕይወት መስመር የሚይዝበት ነው የምትለው ቆንጂት፣ ይህ ሳይሆን ቀርቶ የተወጣበት ዓላማ ከተዘነጋ ግን የወደፊት ሕይወት የሚጠፋበት ስፍራም መሆኑን ታስረዳለች።

"እኔ ዩኒቨርስቲ እንደገባሁኝ ከኔ በፊት የነበሩትን ሰዎች ምክር አግኝቼ ነበር። ለምሳሌ በዩኒቨርስቲ ሕይወት ምን ማድረግ እንዳለብኝና እንደሌለብኝ አስመልክቶ ከኔ በፊት ከነበሩት ተማሪዎች ጥሩ ምክር አግኝቻለሁ" በማለት የቀድሞ ተማሪዎች የሰጧት ምክር ለዛሬ ውጤቷ ማማር ድርሻ እንዳለው ትናገራለች።

ሕይወት በርካታ እንቅፋቶች አለው የምትለው ቆንጂት " ያጋጠሙኝን እንቅፋቶችና ፈተናዎች በትዕግሥትና በዓላማዬ ላይ ትኩረቴን በማድረጌ ስኬታማ ለመሆን በቅቻለሁ" ትላለች።

" እኛ ሴቶች በዓላማችን ላይ ጠንክረን ከሰራን ላንደርስበት የምንችለው ስፍራ የለም። በሴትነት የሚደርሱብን ፈተናዎችን ደግሞ በትዕግሥት ማለፍ በጣም አስፈላጊ ነው በማለት ምክሯን ትለግሳለች።

በዩኒቨርስቲ ሕይወት ሴት ተማሪዎች በተለያዩ ነገሮች ሊታለሉ ይችላሉ በማለትም፣ ይኹን እነጂ ለወጡለት ዓላማ ቅድሚያ መስጠት ለወደፊት ዓላማ መመቅናት ወሳኝ ነው በማለት ሃሳቧን ታካፍላለች።

ተማሪዎእ ዩኒቨርስቲ መግባትን የዓለም መጨረሻ አድርጎ መውሰድ እንደሌለባቸውም ትናገራለች።

"ሌሎች ሕይወቶች የወጣንበትን ዓላማ ካሳካን በኋላ የሚደረሱ ናቸው።"

ቆንጂት ስለወደፊት ሕይወቷ ስትናገር የከፍተኛ ትምህርቷን በመቀጠል አቅም ሲኖራት ደግሞ ለሴቶች ድጋፍ የሚያደርግን ተቋም አቋቁማ ለመስራት እቅድ እንዳላት ገልጻለች።