ሴቶች፡ በ13 ዓመት ዕድሜ እርግዝና እና ትምህርት

ፋቱ የ13 ዓመት ታዳጊ ስትሆን በደረሰባት ጾታዊ ጥቃት የተነሳ የአራት ወር ነብሰ ጡር ናት

የፎቶው ባለመብት, WAVES

የምስሉ መግለጫ, ፋቱ የ13 ዓመት ታዳጊ ስትሆን በደረሰባት ጾታዊ ጥቃት የተነሳ የአራት ወር ነብሰ ጡር ናት

የታንዛኒያ መንግስት ባለፉት ወራት ያረገዙ ሴት ተማሪዎችና በልጅነታቸው የወለዱ ሴቶች ወደ ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ መከልከሉን ተከትሎ ፍርድ ቤት ክስ ቀርቦበት ነበር። እንዲህ አይነት መሰል ሕግ በመተግበር ታንዛኒያ በዓለማችን ላይ ካሉ ጥቂት አገራት መካከል አንዷ ናት።

የዛሬ ዓመት አካባቢ ደግሞ የሴራሊዮን ከፍተኛ ፍርድ ቤት መንግሥት በተመሳሳይ ያወጣውን ሕግ እንዲተወው ወስኗል። ለመሆኑ በዚህች ምዕራብ አፍሪካዊት አገር ከሕጉ መሻር በኋላ ምን ተቀይሮ ይሆን?

ፋቱ (ትክክለኛ ስሟ አይደለም) የ13 ዓመት ታዳጊ ስትሆን የአራት ወር ነብሰ ጡር ናት። ያረገዘችውም በደረሰባት ጾታዊ ጥቃት ነው።

እስከያዝነው ዓመት ድረስ ፋቱ ባለችበት ሁኔታ ትምህርቷን ማቋረጥ ግድ ይላት የነበረ ሲሆን፣ በግድ ትዳር እንድትመሰረትም ትደረግ ነበር። ነገር ግን በአሁኑ ሰአት ትምህርቷን በመከታተል ላይ ትገኛለች። ወደፊትም ነርስ የመሆን ህልም አላት።

በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት መጋቢት ወር ላይ ነበር ሴራሊዮን ነብሰ ጡር ታዳጊዎች ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ የሚከለክለውን ሕግ ውድቅ ያደረገችው። የምዕራብ አፍሪካ አገራት ማህበር የሆነው ኢኮዋስ ፍርድ ቤት ሕጉ አግላይና ትምህርትን የማያበረታታ መሆኑን መግለጹን ተከትሎ ነው ሕጉ እንዲቀር የተደረገው።

ሴራሊዮን ለረጅም ዓመታት ታዳጊ ሴቶች ቶሎ ቶሎ የሚያረግዙባት አገር ስትሆን በአውሮፓውያኑ 2013 በተሰራ ዳሰሳ መሰረት ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ከሆኑት ዜጎቿ መካከል 35 በመቶ የሚሆኑት የልጅ እናቶች ናቸው።

በአገሪቱ የኢቦላ ወረርሽኝ ተከስቶ በነበረበት ወቅት ደግሞ ቁጥሩ ወደ 65 በመቶ አድጎ ነበር። 2014 ላይ ወረርሽኙን ተከትሎ ትምህርት ቤቶች ተዘግተው ስለነበር በርካታ ታዳጊዎች አርግዘዋል።

ይህንን ተከትሎም ነው የሴራሊዮን መንግሥት ትምህርት ቤት የሚማሩ ታዳጊዎች ካረገዙ ትምህርታቸውን መቀጠል እንደማይችሉ ያስታወቀው። በወቅቱ መንግሥት ይህ ውሳኔ ታዳጊዎች መሰል ነገር ከመፈጸማቸው በፊት ቆም ብለው እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል ብሎ ነበር።

ሴራሊዮን ለረጅም ዓመታት ታዳጊ ሴቶች ቶሎ ቶሎ የሚያረግዙባት አገር ስትሆን በአውሮፓውያኑ 2013 በተሰራ ዳሰሳ መሰረት ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ከሆኑት ዜጎቿ መካከል 35 በመቶ የሚሆኑት የልጅ እናቶች ናቸው

የፎቶው ባለመብት, WAVES

የምስሉ መግለጫ, ሴራሊዮን ለረጅም ዓመታት ታዳጊ ሴቶች ቶሎ ቶሎ የሚያረግዙባት አገር ስትሆን በአውሮፓውያኑ 2013 በተሰራ ዳሰሳ መሰረት ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ከሆኑት ዜጎቿ መካከል 35 በመቶ የሚሆኑት የልጅ እናቶች ናቸው

2015 ላይ በተሰራ አንድ ጥናት መሰረት በዚሁ ሕግ ምክንያት 3 ሺ የሚጠጉ የሴራሊዮን ታዳጊ ሴቶች ከትምህርታቸው እንዲሰናከሉ ተደርገዋል። እንደውም ቁጥሩ ከዚህ ከፍ ያለ እንደሆነ የሚከራከሩም አልጠፉም።

ምንም እንኳን እርጉዝ ተማሪዎችና ወላድ እናቶች ከትምህርት ተቆራርጠው እንዳይቀሩ በሚል ተመሳሳይ የትምህርት ማዕከላት የተቋቋሙ ቢሆንም በሳምንት ሶስት ቀን ብቻ ነው ትምህርት የሚሰጥባቸው። በተጨማሪም የሚሰጡት የትምህርት አይነቶች አራት ብቻ ናቸው።

ይህንን ተከትሎም ነው ኢኮዋስ 2019 ላይ ሕጉ በሴቶች ላይ የሚፈጸም ማግለልን የሚያበረታታና የትምህርት ዕድልን የሚነጥቅ እንደሆነ የገለጸው። ሴራሊዮንም ሕጉን በቶሎ እንድትሽረው አዝዟል።

በሴራሊዮን ሕጉ ተግባራዊ በተደረገበት ወቅት በርካታ ሴት ተማሪዎች ወደ ሁለተኛ ደረጃ እና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለመግባት የሚሰጠውን ብሔራዊ ፈተና መውሰድ እንዳይችሉ አድርጓቸዋል። ፈተናውን ላለፈ ሰው ትምህርቱን ባይቀጥል እንኳን ስራ ማግኘት ቀላል ነው።

''ታዳጊ ሴቶችን እምነት ገደል ከትተነዋል'' ይላሉ በሴራሊዮን በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት ላይ የሚሰራው ድርጅት ውስጥ የሚሰሩት ፋትማታ ያምባሱ። ይሄው ድርጅት ከሌሎች ጋር በመተባባር ነው መንግሥትን ፍርድ ቤት የከሰሰው።

''በወቅቱ ሁሉም ሰው ኢቦላን ማጥፋትና መከላከል ላይ ነበር ትኩረቱ። በታዳጊ ሴቶች ላይ ይፈጸም የነበረውን ጥቃት ማንም ዞር ብሎ አላየውም። ነገር ግን አሁን ትምሀርት አግኝተናል። በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት እነዚህን ታዳጊዎች ግን ብቻቸውን አንደማንተዋቸው ቃል ገብተንላቸዋል''

በአሁኑ ሰአት በአገሪቱ ነገሮች የተለወጡ ይመስላሉ። መንግስትም ችግሩን በመረዳት የመፍትሄ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል። ፕሬዝዳንት ጁሊየስ ማዳ ባሳለፍነው ዓመት አስገድዶ መድፈር ብሔራው አስቸኳይ ጉዳይ መሆኑን እስከማወጅ ደርሰዋል። ፈጣን እርምጃም እንደሚወሰድ ቃል ገብተዋል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ዴቪድ ሞይኒና ባሳለፍነው መጋቢት ወር ላይ የሕጉን መሻር ሲያበስሩ ''ሁሉም ህጻናት ህልማቸውን የማሳካትና ዓለማቀፍ መብት የሆነው የመማር መብታቸውን ተግባራዊ እንዲያደርጉ መፈቀዱን አስታውቃለሁ'' ብለው ነበር።

የዓለም ባንክ ታንዛኒያ ውስጥ በየዓመቱ ትምሀርታቸው ከሚያቋርጡ 60 ሺ ተማሪዎች መካከል ከአምስት ሺ በላይ የሚሆኑት ትምህርታቸውን የሚያቋርጡት በእርግዝና ምክንያት ነው ብሏል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የዓለም ባንክ ታንዛኒያ ውስጥ በየዓመቱ ትምሀርታቸው ከሚያቋርጡ 60 ሺ ተማሪዎች መካከል ከአምስት ሺ በላይ የሚሆኑት ትምህርታቸውን የሚያቋርጡት በእርግዝና ምክንያት ነው ብሏል

ከዚህ ሕግ መሻር በኋላም 1 ሺ ሴት ተማሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ብሔራዊ ፈተናውን ለመውሰድ ተቀምጠዋል።

ነገር ግን ፋትማታ ያምባሱ እና ሌሎችም በጉዳዩ ላይ የሚሰሩ ሰዎች እንደሚሉት ምንም እንኳን መንግሥት በጉዳዩ ላይ ማሻሻያዎችን እያደረገ ቢሆንም ዋናው መቀየር ያለበት ግን የማህበረሰቡ አስተሳሰብ ነው። አሁንም ድረስ ሴራሊዮን ውስጥ ያረገዙ ሴቶችን ከትምህርት ቤት ማባረር የተለመደ ነገር ነው። ሕጉ እንዲሻር ፍርድ ቤት ከወሰነ በኋላ እንኳን በርካታ ቤተሰቦች እንዴት ልጆቻችንን ካረገዙ ታዳጊዎች ጋር አብረው እንዲማሩ እናደርጋለን? በማለት ተቃውመውት ነበር።

'ለልጆቻችን ጥሩ መልዕክት አያስተላልፍም' ነው የሚሉት ቤተሰቦች።

የፋቱ ቤተሰቦች ልጃቸው ተመልሳ ትምህርት ቤት መግባት መቻሏ በጣም ያስደሰታቸው ሲሆን የመንግሥት ውሳኔ በጉዳዩ ላይ ያላቸውን አመለካከት እንዲቀይሩ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል።

ቤተሰቦቿ እንደሚሉት በጉዳዩ ላይ ማህበረሰቡ ውስጥ የተቀላቀለ አመለካከት ነው ያለው።

''አንዳንዶች ልጃችን ላይ የደረሰውን ጥቃት ለፖሊስ በማሳወቃችን እና ጉዳዩን ይፋ በማድረጋችን ደስተኞች ናቸው። ነገር ግን አንዳንዶቹ ልጃችሁን እንዴት ወደ ትምሀርት ቤት ትልካላችሁ? ይሉናል'' ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ፋቱ ደግሞ ትምሀርት ቤት መሄዷ ቢያስደስታትም ነገሮች ግን ቀላል እንዳልሆነ ትገልጻለች።

''ትምህርት ቤት ሄጄ የሚመች አቀማመጥ ማግኘት ከባድ ነው። ለረጅም ሰአት አንድ ቦታ ላይ መቀመጥም ቢሆን አልችልም። ስለዚህ ትምህርቴን በአግባቡ መከታተል አልችልም'' ትላለች።

''በተጨማሪም የትምህርት ቤት ጓደኞቼ አብረውኝ ለመጫወትም ሆነ ሌሎች ነገሮችን ለማድረግ ፈቃደኞች አይደሉም። ምሳ እንኳን አብሮኝ የሚበላ ልጅ የለም'።' ነገር ግን ምንም ቢፈጠር ትምህርቷን ማቋረጥ እንደማትፈልግና እንደማታቋርጥ ለቢቢሲ ተናግራለች።

''አንድ ቀን ትምህርቴን ጨርሼ ነርስ መሆን እፈልጋለሁ። ትልቅ ሰው ስሆን ለሌሎች ሴቶች አርዓያ መሆን እፈልጋለሁ''

ፋቱ የምትማርበት ትምህርት ቤትም ቢሆን ነገሮች ቀላል እንዳልሆኑ ገልጿል። አንዳንድ ተማሪዎች ፋቱን እንዳገለሏትና አብረዋት መጫወት እንደማይፈልጉ አንድ አስተማሪ ገልጾ ነበር። በተጨማሪም አንዳንድ መምህራን ፋቱን በተለየ መልኩ ያይዋት ነበር።

ከሶስት ዓመት በፊት የታንዛኒያው ፕሬዝዳንት ጆን ማጉፉሊ ያረገዙ ተማሪዎች ከትምህርት ቤት መባረር አለባቸው ብለው ከተናገሩ በኋላ በአገሪቱ እየተበራከተ የመጣው የታዳጊዎች እርግዝና ጉዳይ በዓለም አቀፍ ደረጃ የውዝግብ ርዕስ ሆኖ ነበር።

ፕሬዝዳንቱ አንድ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተው "ካረገዛችሁ፤ አለቀላችሁ" በማለት ተማሪ ልጃገረዶችን ካስጠነቀቁ በኋላ ከፍተኛ ወቀሳና ትችት ቀርቦባቸው ነበር።

በወቅቱ ፕሬዝዳንቱ አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት፣ ያለውን የአገሪቱን ሕግ ጠቅሰው ነበር። እንደ አውሮፓዊያኑ በ2002 የጸደቀው ሕግ ተማሪ ልጃገረዶች አርግዘው ከተገኙ ከትምህርት ቤት ማባረርን ይፈቅዳል።

የተባበሩት መንግስታት ባወጣው መረጃ መሰረት ታንዛኒያ ውስጥ በአውሮፓውያኑ 2016 እድሜያቸው ከ15 እስከ 19 ከሆኑ ታዳጊ ሴቶች መካከል ከአራቱ አንዷ አርግዛለች አልያም ልጅ ወልዳለች። በሌላ የመንግሥት መረጃ መሰረት ደግሞ በዚያው ዓመት በአገሪቱ ትዳር ከመሰረቱ ሴቶች መካከል 36 በመቶ የሚሆኑት እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ነበር።

የዓለም ባንክ ደግሞ ታንዛኒያ ውስጥ በየዓመቱ ትምሀርታቸው ከሚያቋርጡ 60 ሺ ተማሪዎች መካከል ከአምስት ሺ በላይ የሚሆኑት ትምህርታቸውን የሚያቋርጡት በእርግዝና ምክንያት ነው መሆኑን ገልጿል።