በዱባይ እርቃናቸውን ፎቶ የተነሱት ሴቶች ወደ አገራቸው ሊባረሩ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዱባይ ባለፈው ሳምንት እርቃናቸውን ፎቶ ተነስተው በቁጥጥር ሥር ውለው የነበሩት የውጭ አገር ዜጎች በአስቸኳይ ወደ አገራቸው ሊባረሩ ነው፡፡
በትንሹ 12 ዩክሬናዊያን እና አንድ ሩሲያዊ በዚህ ‹ከባሕል ያፈነገጠ› በተባለ ድርጊት ጠርጥሮ የዱባይ ፖሊስ በቁጥጥር ሥር አውሏቸው እንደነበር አይዘነጋም፡፡
በዱባይ ማሪና አካባቢ በሚገኝ በረንዳ 12ቱ ሴቶች እርቃናቸውን ፎቶ የተነሱበት ቪዲዮ በማኅበራዊ የትስስር መድረኮች ከተጋራ በኋላ ነበር የዱባይ ፖሊስ የውጭ ዜጎቹን አድኖ በቁጥጥር ሥር ያዋላቸው፡፡
በዱባይ የጋራ ባሕልና እሴትን የሚሸረሽሩና ከባሕል ያፈነገጡ የሚባሉ እንዲህ ዓይነት ድርጊቶች እስከ 6 ወራት እስርና እስከ 5ሺህ ዲርሃም የሚያስቀጡ ናቸው፡፡
ዱባይ ምንም እንኳ ዓለም አቀፍ የጎብኚዎች መዳረሻ ብትሆንም የራሷ ጥብቅና ምዕራባዊ ጎብኚዎችን የማያፈናፍኑ ሕጎች አሏት፡፡
በዱባይ አገሬው የሚገዛባቸው ሕጎች ጎብኚዎችም እንዲከተሏቸው አስገዳጅ የሆኑ ናቸው፡፡
ይህ በማኅበራዊ የትስስር መድረኮች በመቶ ሺዎች ተቀባብለውታል የተባለው ቪዲዮ 12 ዩክሬናዊያንና አንድ ሩሲያዊ የፎቶ ጥበብ ባለሙያ የእርቃን ፎቶ መነሳት ሥነ ሥርዓት ሲያደርጉ የሚያሳይ ነበር፡፡
ከ12ቱ ዩክሬናዊያን ሴቶች በተጨማሪ የየት አገር ዜጎች በዚህ ሕግ መተላለፍ ውስጥ እጃቸው አለበት የሚለው ገና እየተጣራ ነው፡፡
ፖሊስ ይህ ገላን አጋልጦ ፎቶ የመነሳት ተግባር የኢምሬቶችን እሴት የሚጻረር ነው ሲል መግለጫ አውጥቷል፡፡
የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩሉ ዱባይ የሚገኘው ቆንጽላው በእስር ላይ የሚገኙትን 12ቱን ሴቶች እንደጎበኘ ይፋ አድርጓል፡፡
የዱባይ ሚዲያዎች የሚመለከታቸውን ባለሥልጣናትን ጠቅሰው እንደተናገሩት ሁሉም በዚህ ወንጀል ተሳትፎ ያላቸው ወደ አገራቸው እንዲባረሩ ይደረጋል፡፡
በዱባይ የውጭ ዜጎች በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ከአገር ሲባረሩ ይህ የመጀመርያው አይደለም፡፡
በ2017 እንደ አውሮጳዊያኑ አንዲት የእንግሊዝ ዜጋ ከአንድ ማንነቱ ካልተጠቀሰ ወንድ ጋር በትዳር ሳትተሳሰሪ ወሲብ ፈጽመሻል በሚል የአንድ ዓመት እስር ተላልፎባት ነበር፡፡
ስለ ግንኙነታቸው የተደረሰበት እንግሊዛዊቷ አንሶላ የተጋፈፈችው ሰው ማስፈራሪያ መልእክቶችን እየላከ ሲያስቸግራት ይህንኑ ለዱባይ ፖሊስ ባሳወቀችበት ጊዜ ነበር፡፡












