ኡጋንዳና ግብጽ የወታደራዊ ደኅንነት መረጃ ልውውጥ ስምምነት ተፈራረሙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኡጋንዳና ግብጽ ወታደራዊ የደኅንነት መረጃዎችን ለመለዋወጥ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተዘገበ።
ስምምነቱ የተፈረመው በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ላይ ለዓመታት የዘለቀው ድርድር አጣብቂኝ ውስጥ በገባበት ወቅት ነው።
የኡጋንዳ ሕዝብ መከላከያ ኃይል ባወጣው መግለጫ ስምምነቱ የተፈፀመው በሁለቱ አገራት ወታደራዊ ደህኅነት ከፍተኛ ባለስልጣናት አማካኝነት በያዝነው ሳምንት ረቡዕ ያደረጉትን ውይይት ተከትሎ ነው።
"እውነታው ኡጋንዳና ግብጽ የናይልን ወንዝ የሚጋሩ አገራት ናቸው። በሁለቱ አገራት መካከል ያለ ትብብር ሊቀር የሚችል አይደለም። ኡጋንዳ ላይ ተፅእኖ የሚያደርስ ጉዳይ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ግብጽ ላይ ተመሳሳይ ሁኔታ መፍጠሩ አይቀርም" በማለት ወደ ኡጋንዳ አቅንቶ የነበረው የግብፍ ደኅንነት ኃላፊውን ጄኔራል ሳሜህ ሳበር ኤል ደግዊን ዋቢ አድርጎ በመግለጫው አትቷል።
የህዳሴ ግድብ በግብፅና በኢትዮጵያ መካከል ለአመታት ያህል ከፍተኛ ውጥረት መንስኤ ሆኗል። በባለፈው አመት ተሰናባቹ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አወዛጋቢ የተባለውን ግብፅ የህዳሴ ግድብን ልታፈነዳው ትችላለች በማለት ሲናገሩ ተሰምተዋል።
ኢትዮጵያ ይህንን የሃይድሮኤሌክትሪክ ግድብ ቁልፍ የሆነ የኃይል ምንጭ እንደሆነና አገሪቷ ለምታደርገው ኢኮኖሚያዊ እድገት መሰረቴ ነው ትላለች።
የታችኛው ተፋሰስ አገራት ግብፅና ሱዳን በበኩላቸው አራት ቢሊዮን ዶላር የወጣበት ይህ ግድብ ወደ አገራቱ የሚፈሰውን ውሃ በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሰዋል በማለት ይሰጋሉ።
የአባይ ወንዝ ከሁለት አገራት የሚነሳ ሲሆን አንደኛውና ትልቁን ድርሻ የሚይዘው ጥቁር አባይ መነሻና ገባሪ ኢትዮጵያ ስትሆን የነጭ አባይ ምንጭ ደግሞ ኡጋንዳ ናት።
ለዓመታት ሲደረግ የነበረው የሦስትዮሽ የሕዳሴ ግድብ ድርድር ከሰሞኑም ያለምንም ፍሬ ተቋጭቷል።
በአፍሪካ ሕብረት ጥላ ስርና በዲሞክራቲክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ፊሊክስ ትሽሴኬዲ አሸማጋይነት ሲካሄድ የነበረው ድርድር ባለመግባባት የተቋጨው በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ ነበር።
ግብጽ በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር በሚደረገው ድርድር ላይ የተለያዩ አገራት ከጎኗ እንዲቆሙ በተለያየ መልኩ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ስታደርግ ቆይታለች።
ከዚህ ቀደም በግድቡ ዙሪያ እምብዛም ተቃውሞ አሰምታ የማታውቀው ሱዳን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከግብጽ ጋር የሚቀራረብ ሀሳብ ስታንጸባርቅ እንደነበር ተነግሯል።
ከቅርብ ወራት ወዲህም ከሱዳን ጋር የወታደራዊ ትብብር ስምምነት የተፈራረመችው ግብጽ ከተለያዩ የተፋሰሱ አገራት ጋር መልካም ግንኙነት ለመፍጠር እጣረች ትገኛለች።
ከኡጋንዳ ጋር የደረሰችው ስምምነትም የዚሁ ጥረቷ አንድ አካል እንደሆነ ይታመናል።












