ወደ ስልክ መተግበሪያ የተሻገረው ዕቁብ

ዮሐና ኤርምያስ

የፎቶው ባለመብት, eQUB/Twitter

የምስሉ መግለጫ, ዮሐና ኤርምያስ

ተንቀሳቃሽ ስልክ መደዋወያ ብቻ የነበረበት ዘመን አልፏል። ስልካችን ገንዘብ መላኪያ፣ ምግብ ማዘዣ፣ ዜና መመልከቻ ወዘተ. . . ሆኗል።

ስልክ ምስጋና ይግባውና፤ በአካል መገናኘት ይጠይቁ የነበሩ ክንውኖች ወደ ስክሪን ከተሻገሩ ሰነባብተዋል።

መተግበሪያ ሠሪዎች በተለምዶ 'ባህላዊ' የምንላቸውን ነገሮች ለማዘመን የኮምፒውተር ቀመር ያወጣሉ።

በዚህ መልኩ ወደ መተግበሪያ ከተሻገሩ አንዱ ዕቁብ ነው። እድሜ ጠገቡ ማኅበራዊ መረዳጃ አሁን በስልክ መከናወን ጀምሯል።

በሰፈር ወዳጅነት፣ በዘመድ አዝማድ ትስስር ወይም በሥራ ባልደረባነት ዕቁብ የሚገቡ ሰዎች ሙሉ ሂደቱን በስልክ የሚያከናውኑበት መተግበሪያ ነው።

ስሙ ዕቁብ ይባላል። እንደ ፕሌይ ስቶር ባሉ መተግበሪያ መጫኛዎች ላይ eQUB ተብሎ ተመዝግቧል። ባለፉት ሳምንታት ከ1000 በላይ ሰዎች መተግበሪያውን ጭነዋል።

"ሰውን ሰው ያደረገው ዕቁብ ነው"

ዮሐና ኤርምያስ የዕቁብ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂስ አጋር መስራች እና ዋና የቴክኒክ ኃላፊ ናት።

ዕቁብ መተግበሪያን እውን ለማድረግ አንድ ዓመት እንደወሰደ ትናገራለች።

"ሁሉንም ነገር በስልካችን እየተጠቀምን ነው። የባንክ አገልግሎት፣ የንግድ ልውውጥና አብዛኛው ነገር በስልክ ሆኗል። እኛም ባህላዊውን ዕቁብ ወደ ስልክ መተግበሪያ አመጣነው" ትላለች።

ብር ለመቆጠብ እንዲሁም ጠቀም ያለ ገንዘብ በአንድ ጊዜ ለማግኘት የሚረዳው ዕቁብ በመተግበሪያ ሲከወን ቀላል እንደሚሆን ታምናለች።

በእርግጥ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የኢንተርኔት አገልግሎት ውስንነት፣ ስማርት ስልክ የሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥር ማነስና ሌሎችም መሰናክሎች ከግምት መግባት አለባቸው።

ዮሐናም በዚህ ትስማማለች። "ረዥም ጊዜ እንደሚወስድ እንጠብቃለን። ያለው የቴክኒክ እውቀት ውስንነትም መታሰብ አለበት። ሆኖም ግን በጊዜ ሂደት ብዙ ሰው እንዲጠቀምበት ነው የምንፈልገው" ትላለች።

ዮሐና እንደ ዕቁብ ያሉ ዓመታት ያስቆጠሩ ማኅበራዊ እሴቶችን ወደ ዲጂታሉ ዓለም በማሻገር ታምናለች። ላለንበት ዘመን ምቹና ቀላሉ መንገድ ዲጂታል አሠራር ነው።

"ዲጂታል አሠራር የሚሰጠውን ቅለት ወደ ዕቁብም አምጥተናል። ሰውን ሰው ያደረገው ዕቁብ ነውና የአሁኑ ትውልድም ዕቁብን እንዳይረሳ መተግበሪያው ይረዳል" ስትል ታስረዳለች።

ወደ ስልክ መተግበሪያ የተሻገረው ዕቁብ

የፎቶው ባለመብት, eQUB/Twitter

ዲጂታል ዕቁብ እንዴት ይሠራል?

መተግበሪያው ሲጠነሰስ ቀድሞውንም ዕቁብ የነበራቸውን ሰዎች ወደ ዲጂታሉ ለማምጣት ነው። በተጨማሪም ዕቁብ ያልነበራቸውን ወጣቶች ለመሳብ ታቅዷል።

ዕቁብ በቤተሰብ ወይም በሥራ በሚተዋወቁ ሰዎች ሲገደብ፤ ዲጂታል ዕቁብ ግን በየትኛውም ቦታ ያሉ ሰዎች ገንዘብ እንዲጥሉ ያደርጋል።

መተግበሪያውን በስልኩ የሚጭን ሰው ስም፣ የትውልድ ቀን፣ መታወቂያ ጽፎ ይመዘገባል።

መተግበሪያው ሁለት አማራጮች አሉት። ዕቁብ መፍጠር እና ዕቁብ መሳተፍ።

ዕቁብ መፍጠር ማለት የዕቁብ ሰብሳቢ ሆኖ፣ ሰዎችን አስገብቶ ሂደቱን መምራት ነው። መሳተፍ ደግሞ የዕቁብ ቡድኑ አባል መሆን።

ዕቁቡ የግል (ፕራይቬት) ወይም የሕዝብ (ፐብሊክ) ሊሆን ይችላል።

የግል ዕቁብ እርስ በእርስ የሚተዋወቁ ሰዎች ተገባብዘው ዕቁብ የሚጥሉበት ነው። አሁን ላይ አገልግሎት የሚሰጠውም ይህኛው የመተግበሪያው ክፍል ነው።

ዕቁብ ሰብሳቢ ምን ያህል ሰው መሰብሰብ እንደሚፈለግ፣ በምን ያህል ጊዜ ዕቁብ እንደሚጣል እና የገንዘብ መጠኑን ይወስናል።

ዕቁብ በቀን፣ በሳምንት ወይም በወር መጣል ይቻላል። ትንሹ የገንዘብ መጠን 10 ብር ሆኖ 50፣ 100 ወይም ከዛ በላይም መጣል ይቻላል።

ሰብሳቢው ዕቁብ ፈጥሮ ሰው ይጋብዛል። ከዚያም አባላቱ መለያ ቁጥር ይሰጣቸዋል። እያንዳንዱ የዕቁብ ቡድን የራሱ መለያ ቁጥር አለው።

ዕቁቡ ከመጀመሩ በፊት ሰዎች እንዲገቡ ሦስት ቀን ይሰጣል።

የተጋበዙት ሰዎች መስፈርት አሟልተው ከተመዘገቡ በኋላ ለዕቁቡ በተቀመጠው ቀን የተስማሙትን የገንዘብ መጠን ይከፍላሉ።

ሰብሳቢው ገንዘብ የሚገባበትን የባንክ ቁጥር ይፋ ያደርግና፤ አባላቱ ባንክ ሄደው የሚጠበቅባቸውን ገንዘብ ያስተላልፋሉ።

ከዚያም ብር ያስገቡበትን ደረሰኝ መተግበሪያው ላይ ይጭናሉ። ሲጭኑ የዕቁብ ሰብሳቢው መልዕክት ይደርሰዋል። ትክክለኛ መሆኑንም ያረጋግጣል።

የዕቁቡ ቀነ ገደብ ሲያልቅ ሰብሳቢው ለአሸናፊው ሰው ገንዘብ ያስተላልፋል።

ዕቁብ ጣዮች እንዴት ይተማመናሉ?

ዕቁብ የሚጥሉ ሰዎች በትክክል ገንዘብ ስለማስገባታቸው፣ የሚያስገቡት ገንዘብ ሰብሳቢው ጋር ስለመድረሱ ወይም አሸናፊው ሰው ገንዘቡን ስለማግኘቱ መተማመኛ ያስፈልጋቸዋል። ሂደቱ ዲጂታል መሆኑ ደግሞ ነገሮችን ሊያወሳስብ ይችላል።

ዮሐና እንደምትለው፤ የሚተዋወቁ ሰዎች የግል ዕቁብ እንዲመሠርቱ የወሰኑት መተማመን ለመፍጠር ነው። ተቋሙ የገንዘብ አቅም ኖሮት እዳ (ላየቢሊቲ) ውስጥ መግባት ሲችል ደግሞ የሕዝብ (ፐብሊክ) ዕቁብ መጀመር ይቻላል።

"ለአሁን ዕቁብ የሚገቡት የሚተዋወቁ ሰዎች ናቸው። የዕቁቡ እዳ ሰብሳቢው ላይ ወድቆ፣ የዕቁቡ ተሳታፊዎችም አውቀው ነው የሚገቡት" ትላለች።

ተቋሙ አቅሙን አሳድጎ እዳውን መካፈል እስኪችል ሰዎች የግል ዕቁብ ብቻ እንዲገቡ ቢፈቅድም፤ ለወደፊት ከባንኮች ጋር ተጣምሮ የመሥራት እቅድ እንዳላቸውም ትናገራለች።

እንደ ምሳሌ የምትጠቅሰው ከባንኮች ጋር አጋር ሆኖ ለዕቁብ የሚሆን የተለየ የሒሳብ ቁጥር መፍጠርን ነው።

ከባንኮች ጋር በጥምረት መሥራት ሲጀምሩ፤ አንድ ሰው መተግበሪያውን ተጠቅሞ ከፈለገበት ቦታ ገንዘብ እንዲያስገባ ማድረግም ይቻላል።

አሁን ባለው አሠራር የዕቁብ ሰብሳቢ አካውንት ሲፈጥር፣ ተሳታፊዎቹ ገንዘብ ሲያስገቡና ሰብሳቢው ለአሸናፊው ገንዘብ ሲያስገባም መተግበሪያው እንዲያሳውቅ ተደርጓል።

"ገንዘብ ሲገባ የዕቁብ ሰብሳቢው ትክክለኛነቱን ያረጋግጣል። ማን ከፈለ ወይም አልከፈለም የሚለው ይታያል። ዕቁብ ሰብሳቢው ያሸነፈው ሰው አካውንት ተሰጥቶት ገንዘቡን ያስገባል። አሸናፊው ደግሞ ገንዘቡ መግባቱን ያረጋግጣል" ስትል ታብራራለች።

ግልጽ አሠራር ለመፍጠር ሲባል መተግበሪያው ከክፍያ ሥርዓት ጋር የተያያዘ ነጥብ አሰጣጥ አለው። ለምሳሌ ዕቁብ አሸናፊው ብር ካልገባለት ከዕቁብ ሰብሳቢው ነጥብ ይቀነሳል።

ዮሐና እንደምትለው፤ ቀጣይ እቅዳቸው፤ ማንኛውም ሰው የሚገባበት (ፐብሊክ) ዕቁብን መተግበር ነው። ይህም የተቋሙን የገንዘብ አቅም ማጠንከርና ከባንኮች ጋር መጣመር ይጠይቃል።