'የሰይጣን ጫማ'ን የገዙት ሰዎች ጫማውን እንዲመልሱ ጥሪ ቀረበ

የፎቶው ባለመብት, MSCHF
ናይኪ ኩባንያ የኔን ምርት አመሳስለው ሰርተውብኛል ካላቸው የወለፈንዲ ጥበብ አምራችና ሰብሳቢዎች ቡድን ጋር በ'ሰይጣን ጫማ' ዙርያ ስምምነት ደርሻለሁ ሲል ተናገረ።
ይህ አወዛጋቢ 'የሰይጣን ጫማ' የተመረተው ከዝነኛው ናይኪ ኤይር ማክስ 97 ምርት ተመሳስሎ ሲሆን 666 ጫማዎች ብቻ ነበር ለገበያ የቀረቡት። ከአንዱ በስተቀር ሁሉም ተሸጠው አልቀውም ነበር።
ጫማው አምስት ጫፍ ያለው ኮከብ እንዲሁም ሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 10 ቁጥር 18 (እርኩስ መንፈስ እንደ መብረቅ ከገነት ሲወረወር ተመለከትኩት) የሚል የሰፈረበት ሲሆን የተሰራው ናይኪ ኤይር ማክስ 97ን በማስመሰል ነበር።
ይህ ብቻም ሳይሆን እያንዳንዱ ጫማ የናይኪን ሶል የያዘ 60 ኪዮቢክ ሴንቲሜትር ቀይ ቀለም እና ከጥበብ ሥራዎችን ከሚሰበስበው ድርጅት አባላት የተወሰደ የሰው ጠብታ ደም ነበረበት።
በዚህ አወዛጋቢ ጫማ ምክንያት ስሜ ጎድፎብኛል ሲል ወደ ክስ አምርቶ የነበረው የስፖርት እቃዎች አምራች ናይኪ ከአምራቹ ጋር ተነጋግረንበት ገዢዎቹ በበጎ ፈቃደኝነት ጫማውን እንዲመልሱ በመስማማታችን መሥርቼው የነበረውን ክስ ለማንሳት ተቃርቤያለሁ ብሏል።
ይህ 'የሰይጣን ጫማ' የሚል ስም የተሰጠው ምርት የአንዱ መሸጫ ዋጋ 1ሺህ 18 ዶላር ተመን ነበረው።
ጫማውን ያመረተው የወለፍንዲ ጥበብ ሰብሳቢ ቡድን ኤምኤስሲኤችኤፍ (MSCHF) ይባላል። በብሩክሊን መቀመጫውን ያደረገ ሲሆን የልዩ ሥነ ጥበባዊ ውጤቶች አምራችና ሻጭ ነው። ይህ ነው የሚባል የሥራ ወይም የምርት ዘርፍ የለውም።
ይህ የጥበበኞች ስብስብ የሆነው አዲስ ኩባንያ አወዛጋቢ ምርቶችን ወደ ገበያ በማውጣት ስመ ጥር እየሆነ ነው።
ይህ ነው የሚባል የምርት መለያ የሌለው ኩባንያው ዋንኛ ተግባሩ ፍጹም የማይጠበቁ ምርቶችን ወደ ገበያ አውጥቶ ውዝግብ በመፍጠር በአጭር ጊዜ የበይነ መረብ ጉሊት ሽያጭ ማካሄድ ነው።
በዚህ የገበያ መርህ መሠረት ይህ ኩባንያ አምርቶት የነበረው 'የሰይጣን ጫማ' በዓለም ላይ ከፍተኛ መነጋገርያ ለመሆን በቅቶ ነበር።
ይህን ተከትሎም ናይኪ ኩባንያ ያመረታችሁት ጫማ የኔን ይመስላል፣ ለዘመናት የገነባሁት መልካም ስሜን እያጎደፋችሁት ነው በሚል ክስ መሥርቶበት ነበር።
ክሱን ተከትሎ አሁን ኤምኤስሲኤችኤፍ ከናይኪ ጋር አዲስ ስምምነት ላይ ደርሷል። የሸጣቸውን ጫማዎች ከገዢዎቹ ለማስመለስ።
ሆኖም የማስመለሱ ተግባር የሚከናወነው በገዢዎቹ መልካም ፈቃድ ይሆናል።
ኩባንያው ጫማዎቹን ለሚመልሱለት ደንበኞቹ የከፈሉትን ብር ወዲያውኑ ተመላሽ ያደርጋል።
ይህን ሲያደርግ ደግሞ ክስ መሥርቶ የነበረው ዝነኛው ናይኪ ክሱን ያነሳል ማለት ነው።
ይህ አወዛጋቢ ነገሮችን አምራች ኩባንያ 'የሰይጣን ጫማን' ያመረተው ከዝነኛው ራፐር ሊል ናስ ኤክስ ጋር በመተባበር ነበር። ሞዛቂው ባለፈው ሳምንት አዲስ ሙዚቃን ወደ ገበያ ለቆ ነበር።
በናይኪና በዚህ አወዛጋቢ የወለፈንዲ ጥበብ አምራች ኩባንያ የተደረሱ ዝርዝር ስምምነቶች ይፋ አልተደረጉም።
ምናልባትም ኩባንያው በ2019 በተመሳሳይ 'የኢየሱስ ጫማ' በሚል ያመረተው ሌላ አወዛጋቢ ምርትም ድርድር ሳይደረግበት አልቀረም።
ያ ምርት በተመሳሳይ የናይኪን ኤይር ማክስ 97 ጋር ተመሳስሎ የተመረተ ነበር።
የናይኪ ኩባንያ በሰጠው መግለጫ "ይህ ኩባንያ የኛን ምርቶች አንዳች ተለዋጭ በማድረግ ለገበያ የሚያቀርበው ድርጊት እኛን የሚወክል አይደለም፤ የሰይጣንም ሆነ የኢየሱስ ጫማ ከኛ ጋር ምንም የሚያያይዘው ነገር የለም፤ እወቁልኝ" ሲል አውጇል።
ብዙውን ጊዜ እንዲህ ዓይነት አወዛጋቢ ምርቶች በቁጥር ትንሽ ስለሚመረቱ ዋጋቸው በጊዜ ብዛት እየናረ ነው የሚሄደው። በመሆኑም ምን ያህል ገዢዎች ጫማውን ለመመለስ ፍቃደኛ ይሆናሉ የሚለው ሚዲያዎችን እያነጋገረ ነው።
ይህ የወለፈንዲ ጥበብ አምራች ኩባንያ (MSCHF) ጫማዎቹን ባለፈው ሳምንት ለገበያ ሲያቀርብ አንድ ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ነበር ሙሉ በሙሉ ተሸጠው ያለቁት።












