ዩክሬን፡ አዲስ ማዕቀብ ግንኙነታቸውን ክፉኛ ሊያበላሽ እንደሚችል ቭላድሚር ፑቲን ጆ ባይደንን አስጠነቀቁ

ባይደንና ፑቲን ለ50 ደቂቃዎች የቆየ የስልክ ውይይት ባደረጉበት ጊዜ

የፎቶው ባለመብት, The White House via Reuters

የምስሉ መግለጫ, ባይደንና ፑቲን ለ50 ደቂቃዎች የቆየ የስልክ ውይይት ባደረጉበት ጊዜ

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በዩክሬን ጉዳይ አዲስ ማዕቀብ ከጣሉ ግንኙነታቸው ሙሉ በሙሉ ሊያበቃለት እንደሚችል የሩሲው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አስጠነቀቁ።

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ሐሙስ ዕለት አመሻሽ ላይ ከአሜሪካው አቻቸው ባይደን ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት ወቅት እንዲህ ዓይነቱ ማዕቀብ "ትልቅ ስህተት" ይሆናል ብለዋል።

ባይደን በበኩላቸው ዩክሬን ላይ ለሚደርስ ማንኛውም ወረራ ዩናይትድ ስቴትስ እና አጋሮቿ ቆራጥ ምላሽ እንደሚሰጡ ተናግረዋል ።

በሩሲያ ጠያቂነት የተካሄደው የስልክ ውይይት በዚህ ወር ለሁለተኛ ጊዜ የተደረገ ሲሆን ለአንድ ሰዓት ያህል ዘለቀ ነበር።

ውይይቱ በዩክሬን እና በሩሲያ ድንበር ላይ የተፈጠረውን አለመግባባት ለማርገብ የተደረገ ጥረት ሲሆን የዩክሬን ባለሥልጣናት ከመቶ ሺህ በላይ የሩሲያ ወታደሮች በድንበር አካባቢ ተሰማርተዋል ብለዋል።

ወታደራዊ እንቅስቃሴው በምዕራቡ ዓለም ስጋትን የፈጠረ ሲሆን ዩክሬን ጥቃት ከተሰነዘረባት ፑቲን "አይተውት የማያውቁት" ማዕቀብ እንደሚጠብቃቸው አሜሪካ አስጠንቅቃለች።

ጦሯ ለልምምድ መንቀሳቀሱን የጠቀሰችው ሩሲያ የወረራ ዕቅድ የለኝም ብላለች። ወታደሮቿን በምድሯ ላይ በነጻነት የማንቀሳቀስ መብት እንዳላትም አክላለች።

በስልክ ውይይቱ ወቅት ሁለቱም ማስጠንቀቂያዎችን ቢለዋወጡም የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አማካሪ ዩሪ ዩሻኮቭ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ፑቲን በውይይቱ ተደስተዋል። ለቀጣይ ውይይቶች "ጥሩ መሠረት" እንደሚጥል ነው ሲሉ አክለዋል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣን በበኩላቸው ውይይቱ "ኮስተር ያለ እና ተጨባጭ" ነበር ብለዋል።

የዋይት ሐሃውስ ቃል አቀባይ ጄን ሳኪ "ፕሬዚዳንት ባይደን ውይይቱ ተጨባጭ መሻሻል ሊፈጠር የሚችለው ውጥረት በረገበበት አካባቢ ብቻ ነው" ብለዋል።

አክለውም "ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች አሜሪካ እና አጋሮቿ ቆራጥ ምላሽ እንደሚሰጡ በግልጽ ተናግራለች" ሲሉ ገልጸዋል።

የአሜሪካ እና የሩሲያ ባለሥልጣናት በሚቀጥለው ወር በጄኔቫ በአካል ተገናኝተው ሊወያዩ ቀጠሮ ይዘዋል። እንደዋይት ሐውስ ከሆነ ባይደን የሩሲያ አቻቸው ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ እንዲከተሉ አሳስበዋል።

ፑቲን ከሐሙሱ ጥሪ በፊት ባደረጉት የበዓል መልዕክት አገራቱ "በጋራ መከባበር እና ብሔራዊ ጥቅምን ከግምት በማስገባት" አብረው ሊሠሩ እንደሚችሉ "እርግጠኛ ነኝ" ብለዋል ።

ቃል አቀባይያቸው ዲሚትሪ ፔስኮቭ በበኩላቸው ሞስኮ "ለውይይት ፍላጎት አላት" ብለዋል።

ፔስኮቭ አክለውም "ያሉብንን ሁሉንም ችግሮች መፍታት የምንችለው በውይይት ብቻ እንደሆነ እናምናለን" ሲሉ ገልጸዋል።