የኦሚክሮን ዝርያ ማዕበል የመጨረሻው ጫፍ ላይ ደርሶ ሊሆን እንደሚችል ደቡብ አፍሪካ አስታወቀች

የፎቶው ባለመብት, AFP
በኦሚክሮን ዝርያ ምክንያት ጥላው የነበረውን የሰዓት እላፊ ገደብ ያነሳችው የደቡብ አፍሪካ ባለሥልጣናት አገሪቱ አራተኛውን የኮቪድ-19 ማዕበል ጫፍን እንዳለፈች ተናግረዋል።
የአገሪቱ መንግሥት ባወጣው መግለጫ የኦሚክሮን ዝርያ በከፍተኛ ፍጥነት የሚዛመት ቢሆንም ከቀደምት የኮሮናቫይረስ ዝርያዎች ጋር ሲነጻጻር ወደ ሆስፒታል የሚገቡ ሰዎች ቁጥር ዝቅተኛ ነው ብሏል። በቫይረሱ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ደግሞ በመጠኑ መጨመሩንም ጠቅሷል።
ባለፈው ወር ለመጀመሪያ ጊዜ በደቡብ አፍሪካ ሪፓርት የተደረገው የኦሚክሮን ዝርያ ወደ ሌላው የዓለም ክፍል በፍጥነት የተሰራጨ ሲሆን፤ አገራት የተለያዩ የመከላከያ እርምጃዎች እንዲወስዱ ያስገደደም ነበር።
በዴልታ እና ኦሚክሮን ዝርያዎች የሚከሰተው በቫይረሱ የመያዝ ምጣኔ የሚያስነሳው "ማዕበል" የጤና ሥርዓቶች ላይ ጫና ሊፈጥር እንደሚችል የዓለም ጤና ድርጅት አስጠንቅቆ ነበር።
ሆኖም የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ካደረገው ልዩ የካቢኔ ስብሰባ በኋላ የወጣው መግለጫ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ማለት በሚቻል ደረጃ በቫይረሱ የሚያዙ እና ወደ ሆስፒታል የሚሄዱ ሰዎች ቁጥር ቀንሷል ብሏል።
በፈረንጆቹ ታኅሳስ 25 መገባደጃ ሳምንት ቫይረሱ እንዳለባቸው የተረጋገጡ ሰዎች ቁጥር 89 ሺህ 781 ሆኖል። ይህም ከሳምንት በፊት ከነበረው 127 ሺህ 753 ጋር ሲነጻጻር ዝቅተኛ ሆኖ ተመዝግቧል።
የአገሪቱ መንግሥት ሰዓት እላፊ እና አልኮል መሸጥ ላይ ጥሎት የነበረውን ገደብም አንስቷል።
በደቡብ አፍሪካ የኦሚክሮን ማዕበል ቢኖርም አገሪቱ አሁንም "በተለመደው የጤና አገልግሎት ታካሚዎችን የመቀበል አቅም" አላት ሲሉ ባለሥልጣናቱ ተናግረዋል ።
ኅብረተሰቡ አሁንም ክትባት እንዲወስድ እና ግዴታ የሆነውን ማስክ ማድረግ ጨምሮ የሕዝብ ጤና ፕሮቶኮሎችን እንዲከተል ማሳሰቢያ ቀርቦለታል።
አካላዊ ርቀትን ለማስጠበቅ እንዲረዳ በአዳራሽ እና ከአዳራሽ ውጭ የሚሳተፉ ሰዎች ብዛት ላይ ገደብ ተጥሏል።
መግለጫው የብሔራዊ ኮሮናቫይረስ መከላከያ ኮማንድ ምክር ቤት ሁኔታውን ተከታትሎ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ወይም በቫይረሱ ምክንያት ወደ ሆስፒታል የሚሄደው ሰው ከጨመረ ማስተካከያ ያደርጋል ሲል ያትታል።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ ወዲህ በደቡብ አፍሪካ ወደ 3.5 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን ከ90 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸውን አጥተዋል።












