ባይደን እና ፑቲን በዩክሬን ጉዳይ 'ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ' ፍለጋ ሊወያዩ ነው

ፕሬዚዳንት ፑቲን እና ፕሬዚዳንት ባይደን

የፎቶው ባለመብት, EPA

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በዩክሬን ያለውን ውጥረት ለማርገብ ከሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር በዚህ ወር ለሁለተኛ ጊዜ ሊወያዩ ነው።

መሪዎቹ ሐሙስ ዕለት በስልክ ይነጋገራሉ ተብሏል።

እንደዋይት ሐውስ ባለሥልጣን ከሆነ ፕሬዝዳንቶቹ በአገሮቹ መካከል በቀጣይ ስለሚደረጉ የፀጥታ ውይይቶች እና በአውሮፓ ባለው ሁኔታ ላይ ይወያያሉ።

ከዩክሬን ጋር በሚያዋስናት ድንበር ላይ ጦር ያሰፈረችው ሩሲያ አገሪቱን ለመውረር አላቀድኩም ስትል አስተባብላለች።

ሩሲያ ወታደሮቿ በቦታው ለልምምድ መገኘታቸውን ጠቅሳ ጦሯን በአገሯ በነጻነት የማንቀሳቀስ መብት እንዳላት ተናግራለች።

ለጉዳዩ የጋራ ምላሽን ለመስጠት ከሐሙሱ ውይይት በፊት አሜሪካ፣ የአውሮፓ መሪዎችን አማክራለች ሲል የዋይት ሐውስ መግለጫ አስታውቋል።

የዩክሬን የደኅንነት ባለሥልጣናት ከ100 ሺህ የሚበልጡ የሩሲያ ወታደሮች ወደሚጋሩት ድንበር መላካቸውን ገልጸዋል። ዩክሬን ጥቃት ከደረሰባት ፑቲንን "አይተውት የማያውቁት" ማዕቀብ እንደሚጠብቃቸው አሜሪካ ዝታለች።

አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደገለጹት ባይደን ለሩሲያ አቻው "ዲፕሎማሲያዊ መንገድ" የሚያቀርቡ ቢሆንም በድንበር ላይ ያለው የሩሲያ ጦር መጠናከር "በጣም ያሳስባቸዋል" ብለዋል።

ሩሲያ "ዩክሬን ላይ ተጨማሪ ወረራ" ከፈጸመች አሜሪካ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆኗን ባይደን ለፑቲንን ይነግራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከዩክሬኑን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘሌንስኪን ጋር ረቡዕ ዕለት ተነጋግረዋል።

የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ እንዳሉት ብሊንከን "ሩሲያ በዩክሬን ድንበሮች ላይ የምታደርገውን ወታደራዊ እንቅስቃሴ ዩናይትድ ስቴትስ በመቃወም ለዩክሬን ነጻነት፣ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ያላትን የማይናወጥ ድጋፍ በድጋሚ ገልጸዋል።"

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ሁለቱ ፕሬዚዳንቶች በስልክ ባደረጉት ውይይት ባይደን ለዩክሬን ሉዓላዊነት እና ግዛታዊ አንድነት ድጋፋቸውን ገልጸዋል።

ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል ባትሆንም ከሕብረቱ ጋር የጠበቀ ግንኙነት አላት።

ሩሲያ በበኩሏ ኔቶ ወደ ምሥራቅ እንደማይንቀሳቀስ እና የጦር መሳሪያ ዩክሬንን ጨምሮ ወደ የትኛውም የጎረቤት አገር እንደማይላክ በሕጋዊ መንገድ ዋስትና እንደምትፈልግ ተናግራለች።

የኔቶ ዋና ፀሐፊ የንስ ስቶልተንበርግ በበኩላቸው የዩክሬን የሕብረቱ አባልነት የኔቶ እና የኪየቭ ጉዳይ ነው ሲሉ አበክረው ገልጸዋል። "ከሩሲያ ጋር የሚደረገው ማንኛውም ውይይት የአውሮፓ ደኅንነት የተመሰረተባቸውን ዋና መርሆች በማክበር መሆን አለበት" ሲሉ ቀደም ብለው ተናግረዋል።

የሊቱዌኒያው ፕሬዝዳንት ጊታናስ ናውሴዳ ደግሞ አሁን ያለውን ሁኔታ ምናልባትም "በ30 ዓመታት ውስጥ ከታዩት እጅግ አደገኛው" ሲሉ ገልጸውታል።

የሩሲያ ባለሥልጣናት በአውሮፓውያኑ ጥር 10 ከአሜሪካ አቻዎቻቸው ጋር በጄኔቫ ሊገናኙ ቀጠሮ ይዘዋል። በዕለቱ ከፑቲን ጋር ይገናኙ እንደሆነ የተጠየቁት ባይደን "እስቲ እናያለን" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። ሆኖም በጄኔቫ በሚደረገው ድርድር ላይ ይገኛሉ ተብሎ አይጠበቅም።