በደብረ ማርቆስ ሠርግ፣ ተዝካር እና መሰል ድግሶች እንዳይካሄዱ ተከለከሉ

የፎቶው ባለመብት, Debremarkos City Police
የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ሠርግ ተዝካርና የመሳሳሰሉ ድግሶች እንዳይካሄዱ መከልከላቸውን የከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ይትባረክ አወቀ ለቢቢሲ ገለጹ።
ለዚህ ክልከላ ዋነኛ ምክንያት የሆነው በባለፉት ወራት የክልሉ ምጣኔ ሀብት በከፍተኛ ሁኔታ መጎዳት፣ በተለይም ጦርነቱ ያስከተላቸውን መፈናቀልና ሌሎች ኪሳራዎች ለመደጎም እንደሆነ ምክትል ከንቲባው አስረድተዋል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ጽህፈት ቤት ሕዝብ ግንኙነት የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ላይ ባወጣውና በተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ተፈርሞ ለተለያዩ መሥሪያ ቤቶች በተላለፈው መመሪያ የተለያዩት ድግሶች እንዳይካሄዱ ታዟል።
ይህን ጊዜያዊ እገዳ መጣል ያስፈለገው በጦርነቱ ምክንያት በርካታ ሚሊዮኖች ተፈናቅለው፣ የበርካቶች ህይወት ተቀጥፎ፣ ንብረት ወድሞ ባለበት ሁኔታ ነዋሪው ለከፋ ርሃብና ችግር እንዳይጋለጥ አስፈላጊውን ጥንቃቄና ቁጠባ ለማድረግ ነው ሲል መመሪያው ያብራራል።
እንዲሁም በአሁኑ ወቅት እንዲህ ያሉ ድግሶችን መደገስ በሞራልም ሆነ በሐይማኖት ተቀባይነት የለውም ብሏል።
በሁለተኛ ደረጃ እንደ ምክንያት የተቀመጠው አገሪቱ ካለችበት ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር የአካባቢውን ሰላምና ደኅንነት በተለመደው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለማስፈፀም ካለመቻሉ ጋር ተያይዞ አስቸኳይ አዋጁ የጣለውን የእንቅስቃሴ ገደብን ጠቅሷል።
ሠርግና ተዝካር የመሳሰሉ የድግስ ሥነ ሥርዓቶች የበርካታ ሰዎችን መሰባሰብ እንዲሁም ያለ ገደብ እንቅስቃሴን መሻታቸው ከወጣው መመሪያና አዋጅ ጋር ተቃርኖ ይፈጥራል ብሏል።
በጦርነቱ ምክንያት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ነዋሪ መሞቱን የገለጹት አቶ ይትባረክ በአሁኑ ወቅት ጦርነቱ አለመቋጨቱንም ገልጸው፣ ይህንንም ጦርነት ያለ ምጣኔ ሀብት ማሸነፍ ስለማይቻልና እነዚህ ድግሶችም በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ጫና ስለሚፈጥሩ እንደሆነም ያስረዳሉ።
ሠርግ፣ ተዝካር እንዲሁም ሌሎች ድግሶች ማኅበረሰቡ የሚገናኝበት ሌሎች ትውፊቶቹንም የሚገልጽበት እሴቶች ከመሆናቸው አንፃር የሕዝቡን መብት መጋፋት አይሆንም? ወይ ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ አቶ ይትባረክ ሲመልሱ፡
"ለተጎዱት እናድርገው ነው። በቅንነት የታሰበ ነው። ለተጎዱት ማድረግ እንኳን ካልቻልን የአካባቢውን ኢኮኖሚ አንጉዳው። አንዱ ቤት ሐዘንና መከራ፣ ሌላኛው ቤት ደግሞ ሠርግ በእውነቱ ሁለቱ አብረው አይሄዱም። በእውነቱ ለመናገር የአማራን ሕዝብ አንድነትንም ይፈታተናሉ" ብለዋል።
ይህንንም ለማድረግ በየደረጃው ላለው ሕዝብ መረጃ እንደተሰጠና ለየቀበሌው ደብዳቤ መጻፉንም አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት ኅብረተሰቡ የተፈናቀሉ የአካባቢውን ሕዝብ ለመርዳትና የፀጥታ መዋቅሩንም ለመደገፍ ከፍተኛ ወጪ እያደረገ ነው የሚሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው፣ ለወደፊቱም ቤታቸው የፈረሰባቸው፣ ሃብት ንብረታቸው የተዘረፈባቸውንም መደገፉ ስለማይቀር የሕዝቡም ወጪ እንደሚጨምር ጠቅሰዋል።
የከተማው መስተዳድርም ሕዝቡ እንዲያዋጣና እንዲተባበር እየቀሰቀሰ ሲሆን ከነዚህ ድግሶች ጋር ተደማምሮ ማኅበረሰቡ ለከፍተኛ ኪሳራ መዳረግ እንደሌለበት አስረድተዋል።
"አቅሙ ያላቸው ሰዎች የሚችሉትን ለፀጥታ መዋቅሩ ቢያበረክቱት፤ ለህልውና ዘመቻ ድጋፍ ቢያደርጉት፣ የተፈናቃዮችን አካባቢዎች ቢደግፉት መልካም ነው። ስምም ይሆናል ታሪክም ነው" ብለዋል።
መመሪያው ተፈፃሚ የሚሆነው ከታኅሣሥ ጀምሮ ሲሆን ይህንን እግድ ተላልፎ በሚገኝ ሰው ላይ ይህ ነው የሚባል ቅጣት እንደሌለ፣ ነገር ግን ኅብረተሰቡ ውሳኔውን እንደሚረዳው ምክትል ከንቲባው ጠቁመዋል።
በተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ተፈርሞ በወጣው መመሪያ እንዲሁም የደብረ ማርቆስ ከተማ ፖሊስ ማኅበራዊ የትስስር ገጽ የኮማንድ ፖስት አባል እና የደብረ ማርቆስ ፖሊስ ጽ/ቤት ኃላፊ ኮማንደር ባንተአምላክ ካሳሁን ዋቢ አድርጎ ባሰፈረው መረጃ መሰረት በከተማው ጋብቻ፣ ሠርግም ሆነ ተዝካር የተከለከለ ሲሆን በልዩ ሁኔታ መጋባት ያለባቸው ለኮማንድ ፖስቱ ጥያቄ አቅርበው በማስፈቀድ ጋብቻው ከሠርግ ዝግጅት ውጪ እንዲፈፀም የሚደረግ ይሆናል።
ይህንን ክልከላ ተላልፎ ጋብቻም ሆነ ተዝካር እንዲወጣ የሚፈጽም እና የሚያስፈፅም የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ አስፈፃሚ ግብረ ኃይሉ አስፈላጊውን ሕጋዊ እርምጃ የሚወስድ መሆኑም ሰፍሯል።
ለተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ክልከላው እስከ መቼ እንደሚቆይ በቢቢሲ ተጠይቀው "የአማራ ሕዝብ ከደረሰበት ሁለንተናዊ ጉዳት፣ ቁስለትና ኪሳራ ተላቆ፤ አንገቱን ቀና አድርጎ መሄድ አስኪጀምር ድረስ ነው" ብለዋል።












