ዩክሬን ከሩሲያ ጋር በጠረጴዛ ዙሪያ ለመነጋገር ጥያቄ አቀረበች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዩክሬን እየጠነከረ የመጣውን የጦርነት አታሞ ለማብረድ ከሩሲያና ከቁልፍ የአውሮፓ ሕብረት አባላት ጋር ውይይት ለማድረግ ጥሪ አቅርባለች።
የዩክሬን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዲሚትሮ ኩሌባ እንዳሉት ሩሲያ እያደራጀችው ስላለው ወታደር እንድታስረዳ በይፋ ብትጠየቅም መልስ አልሰጠችም።
ሚኒስትሩ ቀጣዩ እርምጃ በ48 ሰዓታት ውስጥ ስብሰባ ጠርቶ ሩሲያ ስላላት ዕቅድ "በግልፅ" ማውራት ነው ብለዋል።
ሩሲያ፤ 100 ሺህ ገደማ ወታደሮች ዩክሬን ድንበር አቅራቢያ ብታሰልፍም ዩክሬንን ልትወር ነው ተብሎ የሚቀርብባትን ወቀሳ እያጣጣለች ትገኛለች።
ነገር ግን አንዳንድ ምዕራባዊያን ሃገራት ሩሲያ ዩክሬን ላይ ወታደራዊ እርምጃ ልትወስድ ትችላለች ሲሉ፤ አሜሪካ ደግሞ ሞስኮው ወረራውን በአየር ጥቃት ልትከፍት ትችላለች ስትል አስጠንቅቃለች።
በርካታ ሃገራት ዜጎቻቸው ዩክሬንን ጥለው እንዲወጡ አሳስበዋል። አንዳንዶች ደግሞ የኤምባሲ ሠራተኞቻቸውን ከዋና ከተማዋ ኪዬቭ አሽሽተዋል።
ሲቢኤስ የተሰኘው የቴሌቪዥን ጣቢያ ከምንጮቼ ተረዳሁ እንዳለው አሜሪካ የኤምባሲዋን ሠራተኞች በሚቀጥሉት 48 ሰዓታት ለማስወጣት ዝግጅት ላይ ነች።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኩሌባ እንዳሉት ዩክሬን አርብ ዕለት ሩሲያ በቪዬና ሕግ መሠረት ማብራሪያ እንትሰጣት ጠይቃለች።
የቪዬና ሕግ ሩሲያን ጨምሮ የአውሮፓ ሃገራትን ያካተተ ስለጋራ ደህንነት የሚያትት ሰነድ ነው።
ነገር ግን የዩክሬን ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ እየታየ ያለውን "አለመረጋጋት" ወቅሰው ሩሲያ በጥቂት ቀናት ዩክሬንን ልትወር ነው የሚባለው ማስረጃ የሌለው ወሬ ነው ሲሉ አጣጥለዋል።
ዜሌንስኪ ከአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ጋር እሑድ ዕለት ቢያንስ ለአንድ ሰዓት የቆየ የስልክ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ባይደን ሃገራቸው ለዩክሬን ያላትን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ነግረዋቸዋል ሲሉ የዋይት ኃውስ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።
ቅዳሜ ዕለት ደግሞ ለአንድ ሰዓት ያክል በስልክ ያወሩት ባይደንና የሩሲያው መሪ ቭላድሚር ፑቲን ስምምነት ላይ ሳይደርሱ ቀርተዋል።
ምዕራባዊያን፤ ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን [ኔቶ] አባል እንደትሆን ሊፈቀድላት አይገባም የሚለውን የሩሲያን ሐሳብ ውድቅ አድርገው አዳዲስ አባላት መግባት አለባቸው ይላሉ።
በለንደን የዩክሬን አምባሳደር ቫዲም ፕሪስታይኮ ሃገራቸው ኔቶን ለመቀላቀል ያላትን ዕቅድ እርግፍ አድርጋ ልትተው እንደምትችል ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ሰላማዊ መፍትሔ ለማምጣት እየተጣጣርን ነው የሚሉት ምዕራባዊያን ሃገራት ከሩሲያው መሪ ጋር ለመነጋገር ደፋ ቀና እያሉ ነው።
የጀርመኑ መራሔ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ሰኞ ዕለት ወደ ኪዬቭ አቅንተው ከፕሬዝደንት ዜሌንስኪ ጋር ማክሰኞ ደግሞ ወደ ሞስኮው ሄደው ከፑቲን ጋር ለማውራት ዕቅድ ይዘዋል።
ከአንግላ ሜርክል ባለፈው ታኅሣሥ ሥልጣን የተረከቡት ኦላፍ ሩሲያ ወታደራዊ እርምጃ ከወሰደች ከባድ ምጣኔ ሃብታዊ ቅጣት እንደሚጠብቃት ማስጠንቀቂያ ሰጥተው ነበር።
ነገር ግን የበርሊን ባለሥልጣናት ምናልባት ጉዞው ለውጥ ላያመጣ ይችላል የሚል ስጋት አላቸው።
በሌላ በኩል የዩኬው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ከአውሮፓ ሃገራት ጋር አዲስ ውይይት አድርገው ሩሲያን 'ከጦርነት ቋፍ' ለመመለስ መዘጋጀታቸው ተሰምቷል።
የፕሬዝደንት ባይደን ብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ጄክ ሱሊቫን "ወረራው በማንኛውም ቀን ሊጀምር ይችላል" ሲሉ ተደምጠዋል።
ሩሲያ ድንበር አካባቢ ወታደር ያሰባሰብኩት ለራሴው ደኅንነት በመስጋት ነው ትላለች።












