65ሺህ ኢትዮ-ኤርትራዊያንን ያዋደደው 'የፍቅር አሰናኝ' መተግበሪያ

የጀበና ድረ-ገጽ የፊት ገጽታ

የፎቶው ባለመብት, JEBENA

የፍቅር አጋሮች በሰርጋቸው ቀን ነበር የሚተዋወቁት አሉ። ድሮ!

ዘንድሮ ግን በ"ደብል ክሊክ" ሆኗል። ሲንግልነት በ'ሲንግል ክሊክ' የሚጠፋበት ዘመን።

ይሄኔ'ኮ የነገ አጋሮቻችንን ምናልባት በስልካችን መተግበሪያ ይዘናቸው እየዞርን ይሆናል። ማን ያውቃል?

በእርግጥ ጀበና ያውቃል።

ጀበና የፍቅር ትውውቆሽ ማሳለጫ ነው። በአያሌው እየተመነደገ ያለ የስልክ መተግበሪያ ነው። ትኩረቱን በዳያስፖራ ሐበሾች ላይ ያድርግ እንጂ ተግባሩ የፍቅር አጋርን ማገናኘት፣ ማጣመር፣ ማስተዋወቅ፣ አንዳንዴም ማጋባት ነው።

በተለይ ሐበሾችን ያዋድዳል። ያፋቅራል፣ አንዳንዴም ያጋባል።

በሱ ተዋውቀው የተጋቡ ሁሉ አሉ።

ጀበና ራሱ ለሠርግ ተጠርቶ ያውቃል፡- "እስከነ አፕሊኬሽንዎ….እንዲገኙልን ስንል አክብረን ጠርተንዎታል!" ተብሎ ተጋብዞ ሁሉ ያውቃል።

ለምን ለሐበሾች ብቻ?

በዚህ ዘመን፣ አወዳጅ መተግበሪያዎች (Dating apps) የዋዛ አይደሉም። የቢሊዮን ዶላር ቢዝነሶች ናቸው።

ከማኅበራዊ ሚዲያ በዝግመተ ለውጥ የመጡ ሐሳቦች ይመስላሉ። ሰዎች በማኅበራዊ የትስስር መድረክ እየተዋወቁ ሲመጡ አዲስ ሐሳብ ተወለደ።

የፍቅር ግንኙነትን ብቻ የተመለከተ መተግበሪያ አማራጭ ሆኖ ቀረበ።

በዓለም ላይ በዚህ ረገድ ቲንደር (Tinder) እና በምብል (Bumble) በዘርፉ 'ቅድመ አያቶች' ናቸው።

ሁለቱም መተግበሪያዎች በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ደንበኞች አሏቸው። የወንዶችና ሴት አባላት ቁጥርም ይነስም ይብዛ ተመጣጣኝ ነው።

በምብል ከቲንደር የሚለየው ለሴቶች ምርጫ ቅድሚያ መስጠቱ ነው። በበምብል መተግበሪያ ደንብ ሴቶች ብቻ ናቸው ቀድመው መውደዳቸውን መግለጽ የሚችሉት።

በጀበናስ? "ሐበሻ ሴት ፍቅሯን ቀድማ አትገልጽም" የሚለው ባሕል ቀረ ወይስ አለ?

ለመሆኑ ጀበና ከነ ቲንደር ምን ይለየዋል?

ከጀበና ፈጣሪዎች አንዱ የሆነው ሔኖክ ወልደሚካኤል 'ሁለቱ ግዙፍ የጾታ ፍቅር አሰናኝ መተግበሪያዎች የተሠሩት ለሁሉም የዓለም ሕዝብ፣ የተለየ ማኅበረሰብን ሳያማክሉ፣ ጥቅል (Generic) ሆነው ነው' ይላል።

ከእነዚህ የተወለዱት ሌሎች አዳዲስ የፍቅር አሰናኝ መተግበሪያዎች ግን የተለየ ገጽታን እየያዙ መጡ።

ለምሳሌ ለሙስሊሞች ብቻ ወይም ለክርስቲያኖች ብቻ ተከሽነው የተፈጠሩ መተግበሪያዎች ቀስ በቀስ ተወልደዋል።

ጀበና ደግሞ ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያንን ማዕከል አድርጎ የተፈጠረ ነው።

ጀበናን ከፈጠሩት መካከል አንዱ የሆነው ሔኖክ ወልደሚካኤል

የፎቶው ባለመብት, Henok Woldemichael

የምስሉ መግለጫ, ጀበናን ከፈጠሩት መካከል አንዱ የሆነው ሔኖክ ወልደሚካኤል

ጀበና መተግበሪያን ማን ፈጠረው?

ጀበናን የፈጠሩት ትውልደ ኢትዮ-ኤርትራያዊያን የሆኑ አራት ወዳጆች ናቸው። ዳያስፖራዎች ናቸው።

ለጀበና ገል ካቀበሉት አንዱ ሔኖክ ወልደሚካኤል ነው።

ሔኖክ ኤርትራ ተወልዶ፣ አሜሪካ አድጎ፣ ኑሮውን በኒው ዮርክ ያደረገ ወጣት ነው።

በኦሃዬ ሲቲ ዩኒቨርስቲ፣ (ኮሎምቦስ ኦሃዬ) ኮምፒውተር ሳይንስና ምህንድስናን አጥንቷል።

ሔኖክ 'ጀበና እንዴት ተጸነሰ?' ለሚለው ምላሽ ሲሰጥ እንዲህ ይላል፤ "ውጭ አገር ባይገርምህ፣ በቃ ሐበሻ ሴት ለመተዋወቅ ወይ ሠርግ፣ ወይ ምርቃት መጠራት አለብህ። አለበለዚያ የት ትገናኛለህ?" ሕይወት እንደሆን ሩጫ ነው።

የሔኖክ ትዝብት ሐቅ አለው። ብዙ ሐበሾች በአሜሪካ የፍቅር ጓደኛ አደን የሚወጡት ሔኖክ ከጠቀሳቸው ሠርግና ምርቃት በተጨማሪ በዓመታዊ የስፖርት ፌስቲቫሎች ነው።

በአውሮጳም እንዲሁ ነው።

በዓመት አንዴ በሚሰናዱ የኢትዮ-ኤርትራዊያን የኳስ ውድድሮች፣ የኳስ ይምሰሉ እንጂ ውስጥ ውስጣቸው የሚንከባለለው ድቡልቡል ፍቅር ነው።

እነዚህ መድረኮች ከስፖርት ባሻገር የፍቅር ጥምረት የሚጠነሰስባቸው ናቸው።

'ጀበና የፍቅር አሰናኝ' እንዴት ተፈጠረ?

እርግጥ ነው፣ ሐበሾች የሚገናኙባቸው መድረኮች ውስን ናቸው። ነገር ግን ይህ ችግር በቀጥታ ጀበናን አልወለደም።

ጀበና የተጸነሰው በሌላ አጋጣሚ ነው።

የሐበሻ ባልሆነው አቆጣጠር፣ በጥቅምት 2019፣ ትዊተርና ኢንስታግራም ላይ በሩቅ የሚተዋወቁ ሐበሾች ያወራሉ። እንደው እንደዋዛ ይጻጻፋሉ። አንዱ ለሌላው መልስ በመስጠት ይቀላለዳሉ።

‹‹እንትና ግን ከእንትና ጋ ብናጣብሳቸው…። እንትናና እንትና ቢገናኙ ግን ቀውጢ ነበር…›› እየተባባሉ ጨዋታው ይደራል። የት? ትዊተርና ኢኒስታግራም ላይ።

በዚህ የዋዛ በሚመስል በይነ መረብኛ የወሬ ጋጋታ (Thread) ውስጥ ግን አንዳንድ ልጆች ከሥር ሐሳብ መስጫ ላይ ሐሳብ እንደዋዛ ሰጡ።

"የሐበሻ የፍቅር ዴቲንግ አፕ ቢኖር ግን አሪፍ አልነበረ?!" አሉ።

ሔኖክና ሦስቱ ሸሪኮቹ ይህን ሐሳብ እንደዋዛ አልወሰዱትም።

ለምን አንሞክረውም ተባባሉ። ነገሩን አምርረው ያዙት። ጥናት ማድረግ ጀመሩ። ሆኖም አራቱም የሙሉ ጊዜ ሥራ ነበራቸው። አሜሪካ ፋታ የለም።

ስለሆነም ቶሎ ሐሳቡን ወደ መሬት ማውረድ ተቸገሩ።

በመኸር 2020፣ በአፕል የመተግበሪያ ማከማቻ ውስጥ (ISO) ጀበናን በጥንቃቄና በወጉ አስቀመጡት። በ200 በጎ ፈቃደኞች ላይ 'የሙከራ ሥርጭት' ጀመሩ።

በሚያዚያ ወር፣ 2020 ላይ በይፋ ጀመሩት። ኮቪድ ሲመጣ ጀበና ተጀመረ።

'ብዙ ሰዎች ሆን ብለው በዚያ ወቅት ያስተዋወቅነው ይመስላቸዋል። ነገሩ አጋጣሚ ብቻ ነው' ይላል ሔኖክ።

በእርግጥ በእንቅስቃሴ ገደቡ ጊዜ የተጠቃሚዎች ቁጥር እንደተመነደገ አይክድም። ሆኖም የአጋጣሚ ነገር ነው።

አሁን ጀበና 65ሺህ ተጠቃሚዎች አሉት።

አሁን ጀበና 160ሺህ ኢትዮ-ኤርትራዊያን ዕውቂያና መጠናናት (matches) አድርገውበታል። እስከዛሬ ጀበና ከ1.8 ሚሊዮን በላይ የፍቅር መልእክቶችን አለዋውጧል።

በጀበና ፍቅር እንዴት ነው የሚፈላው?

ጀበና ከፕሌይስቶር ወይም ከአፕልስቶር የስልክ መተግበሪያ መጋዘን የሚራገፍ መተግበሪያ ነው።

ደንበኞች መተግበሪያውን በነጻ ወደ ስልክ ከጫኑ በኋላ እውነተኛ ማንነትን የሚገልጽ ስምና ፎቶን ማያያዝ ይገባቸዋል። ሐሰተኛ ማንነት ከአባልነት ያስባርራል።

ከዚህ ወዲያ የደንበኛው ድርሻ ነው። ጀበና እንደ ፈረስ ነው። ያደርሳል እንጂ አይዋጋም። ፍቅር አፍልቶ የመጠጣቱ ድርሻ 'የቡና ጠጪዎች' ይሆናል።

ከዚህ ወዲያ ሙሉ አባልነት ይገኛል። ከዚህ ወዲያ ‹ጠይም፣ የቀይ ዳማ፣ ጠምበለል፣ ደንዳና፣ ጎራዳ፣ ኮረዳ፣ ሎጋ፣ ሸጋ…› እያሉ ማሰስ ነው፣ ፍለጋ!

አንዲት ኮረዳ የጀበና አባል፣ ቀልቧ ያረፈበትን ጠምበለል የመውደድ ምልክት ካሳየችውና እሱም ምላሽ ከሰጠ፣ በያ ትውልድ ቋንቋ፣ ‹ጠቀሳት፣ ፈገግ አለችለት› እንደማለት ነው።

በ90ዎቹ ቋንቋ ደግሞ ‹ስልክ ተቀበላት›› እንደማለት ሊሆን ይችላል።

ሔኖክ የጀበና መተዳደሪያ ደንብ ለሴቶች ደኅንነት የተመቸ ነው ይላል።

ጋጠ ወጦችን በፍጹም አንታገስም ይላል። በሚኖርበት አገር ቋንቋ ነገሩን ሲገልጸው "Zero tolerance policy" ነው ያለን ይላል።

ሴቶችን ያልተገባ ነገር የሚናገር፣ ያልተገባ ምሥል የሚልክ ካለ ወዲያውኑ ከጀበና ይባረራል።

ሐሳዊ ማንነትን ተላብሶ የጀበና መታወቂያ ደብተር መክፈት አይቻልም። በታዋቂ ሰዎች ፎቶ፣ በግኡዝ ነገር ምሥል ራስን መከለል፣ ማታለል አይፈቀድም።

እንዲህ ደንብ በሚጥሱ ላይ ጥቆማ ሲቀርብ ‹ወዲያውኑ የማያዳግም እርምጃ ይወሰድባቸዋል› ይላል ሔኖክ።

እንደማንኛውም የድረ-ገጽ ዓለም ሰዎች አባላት፣ በአንድ ሌላ አባል ላይ ደጋግመው ክስ ፋይል ከከፈቱ የጀበና ፓስፖርቱ ይነጠቃል።

አሜሪካ የማይኖር ሐበሻ በጀበና መፋቀር አይችም?

ይህ መተግበሪያ ለሐበሻ እንዲመች ተብሎ ታስቦበት የተሠራ ነው ይላል ሔኖክ። እንዴት?

ለምሳሌ በዓለም እጅግ ገናና የሆኑት ቲንደርና በምብል መሠረት የሚደርጉት ጂኦግራፊን ነው።

ይህ ዘዴ ግን ለሐበሻ አይሠራም ይላል ሔኖክ።

መጠነ መክብብ (Radius)ን መሠረት አድርጎ የሚሠራ መተግበሪያ ለሐበሻ ብዙም የማይመቸው ሐበሾች ብዙውን ጊዜ በተወሰኑ ቦታዎች ብቻ ሰብሰብ ብለው ስለሚኖሩ ነው።

"ለምሳሌ እኔ ኒው ዮርክ ነው የምኖረው፤ ቲንደር ወይም በምብል ብጠቀም፣ በ5፣ በ10 እና በ15 ማይል ራዲየስ ያሉ ሰዎችን ነው የሚያገናኘኝ፡፡

"ጀበና ግን እንደዚያ አይሠራም። ማንሃታን ካለች ሐበሻ ጋር አገናኘኝ ብል ሐበሻ የማግኘት ዕድሌ አነስተኛ ነው የሚሆነው" ይላል።

በዚህ የተነሳ እነ ሔኖክ መላ ፈለጉ። መተግበሪያው ሐበሻን ታሳቢ ያደረገ እንዲሆን ኢትዮ-ኤርትራዊያን በብዛት የሚኖሩበትን አካባቢ ነጥሎ ማሰስ እንዲችል አደረጉት።

"ሐበሾች ሰብሰብ ብለው የሚኖሩባቸው ግዛቶችና አውራጃዎች የት የት እንደሆኑ አጠናን። ከዚያ ከስተም ማፕ አዘጋጀን፡፡

በዚህ መሠረት ዲሲ ሜሪላንድ ቨርጂኒያ (DMV) አካባቢ ዋናው የሐበሻ መናኸሪያ ተደርጎ ተቀመጠ። አንድ የጀበና ማዕከል (Hub) ሆነ። ሚድዌስት ሌላኛው፣ ሳውዝ ኢስት ሌላኛው። አውሮፓና ካናዳም እንዲሁ።

‹‹አሁን ይህ መተግበሪያ ከአሜሪካ ባሻገር በዩኬ፣ በስዊድንና ኖርዌይ በሐበሾች ዘንድ ተመራጭ ሆኗል››

በስልክ ማሽኮርመም ባሕላችን ነው?

የጀበና ፈጣሪዎች ይህ ጉዳይ ገና ከጅምሩ ሲያሳስባቸው ነበር። ሐበሻ ጠበቅ ያለ ባህል ያለው ሕዝብ ነው።

በተለይ ሔኖክ መጀመርያ መተግበሪያው ሥራ እንደጀመረ ሰሞን ወላጆቹን እንዴት እንደነገራቸው ያስታውሳል። ፈራ ተባ ማለቱ አልቀረም።

"ሰዎች የሚተዋወቁበት ነገር ነው የፈጠርኩት ስላቸው ደስ ነው ያላቸው" ይላል።

ያም ሆኖ እንደዚህ ዓይነት መተግበሪያዎች እንደ ነውር መታየታቸው አልቀረም።

ሔኖክ ነገሩን የምንጠቀምበትና የምናስተዋውቅበት መንገድ ይወስነዋል ይላል።

"እኛ ጀበናን የተፈጠረው ‹ለቁም ነገር› ነው"

እንዳለውም ለቁም ነገር የበቁ ሰዎች ለምስክርነት አልታጡም። ያውም በዚህ አጭር ጊዜ።

ሔኖክ አንዳንድ ሰዎች በዚህ አጭር ጊዜ ለቁም ነገር መብቃታቸው አስደስቶት፣ ለማመን የሚቸገረውም ለዚህ ነው።

‹‹እኔ የሶፍትዌር ሰው ነኝ። አብዛኛው ትኩረቴም እዚያ ላይ ነው። በብዛት የሚታየኝ ኮድ እንጂ ሰው አይደለም። የሥራዬ ባህሪ ሆኖ ብዙ ጊዜ ሰውኛ ገጽታው ይዘነጋኛል። አንዲት ልጅ 'ዘምዘም እባላለሁ፤ ላገባ ነው። በጀበና መተግበሪያ ነው ባለቤቴን ያገኘሁት' ስትለን ተደነቅኩ።››

"ይህ የማይታመን ነው። ወደፊት የሚወለዱ ልጆች እናትና አባቶቻቸው በጀበና እንደተዋወቁ ሲያውቁ ብዬ ለራሴ ሳስብ በራሴው ሥራ ተደነቅኩ›› ይላል።

ሔኖክ በቅርብ ጊዜ የእሱና የሸሪኮቹን ፈጠራ ተጠቅመው፣ ተዋውቀው ለቁም ነገር የበቁ ሁለት ሦስት ሰዎችን ታሪክ በመተግበሪያው የፊት ገጽ ላይ አጋርቷል።

እንዲያ በማድረጉ ጀበና ለቧልት ሳይሆን ለቁም ነገር መፈጠሩን ሰዎች ይረዳሉ ይላል።

ለቁም ነገር ከበቁት መሀል አንዱ ጋብቻውን የፈፀመው ባለፈው ነሐሴ ወር በዲሲ ነው። ሌላኛው ሠርግ ደግሞ በቴነሲ (Tennessee) ውስጥ ነው የሆነው።

‹‹ለቁም ነገር የበቁ በጣም ብዙ ናቸው። በውስጥ መልእክት ይልኩልናል። የግል ሕይወታቸውን ለሕዝብ ይፋ ማድረግ ስለማይፈልጉ ነው›› ይላል።

"…ሠርግ ሁሉ ተጠርተን ነበር። እኔ አጋጣሚ ጉዞ ላይ ስለነበርኩ መገኘት አልቻልኩም።"

ለመሆኑ ወጣቱ ሔኖክ ራሱ በፈጠረው ጀበና ውስጥ አለ? ውሃ አጣጪውን አግኝቷል? ሰምሮለታል? ወይስ አሁንም ፍለጋ ላይ ነው?

ከቢቢሲ ይህን ጥያቄ በተሰነዘረለት ቅጽበት ወጣቱ ሔኖክ እየሳቀ እንዲህ አለ፤ በኒው ዮርክኛ!

"Sorry, I am taken!"