እውን የፍቅር ወይም የትዳር አጋርዎ ታማኝ የሚባሉ ናቸው?

ሰዎች ለምን ባለንጀራቸው ላይ ይማግጣሉ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝደንት ማይክ ፔንስ ባለቤታቸው ካረን በሌሉበት ከሌላ ሰው በተለይ ደግሞ ከሴቶች ጋር ቁጭ ብለው አይመገቡም።

ይህ ምክትል ፕሬዝደንቱ ለሚስታቸው ካረን ያላቸውን ክብር የሚያሳዩበት መንገድ አንደኛው ነው። ጠንካራ የእምነት ሰው መሆናቸውም ከሚስታቸው ውጪ ቀና ብለው እንዳያዩ እንዳደረጋቸው ይነገራል።

የፔንስ ተግባር ትክክለኛ ነው ብለው ያጨበጨቡላቸው ባይጠፉም፤ 'እንደው የማይሆን ነገር ለእኛ ባይነገር' ሲሉ ምክትል ፕሬዝደንቱን የተቹ በርካቶች ናቸው።

ወጣም ወረደ ማይክ ፔንስ እና ባለቤታቸው ካረን ስለግንኙታቸው ግልፅ የሆነ ሕግ አስቀምጠዋል፤ ባለሙያዎችም የሚመክሩት ይህንኑ ነው። ግንኘነት ውስጥ ያሉ ሰዎች ግልፅ የሆነ ተግባቦት እንዲኖራቸው።

አለመታመን ማለት ምን ማለት ነው? ከግንኙነት ውጭ ካለ ሰው ጋር መተኛት? አብሮ መመገብ? የዚህ ጥያቄ ምላሽ ሊሆን የሚችለው አንድ ነገር ነው - እንደተመልካቹ ነው' የሚል።

በርካታ ሰዎች አለመታመን ወይም መታመን ማለት በግልፅ ምን እንደሆነ ባለማወቃቸው ምክንያት የፍቅር ጓደኛቸው ከእነርሱ ውጭ ሲሄድ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ይጠፋቸዋል።

የሥነ-ልቦና ባለሙያዎች ከፍቅር ጓደኛችን ጋር ውሉ የታወቀ ሕግ ቢኖረን ነገሮች የቀለሉ ይሆናሉ ይላሉ።

ምን ያህል ሰዎች ሳይታመኑ ቀርተዋል ወይም ማግጠዋል? አንድ ጥናት ካናገራቸው ሰዎች መካከል 75 በመቶ ያህል ወንዶችና 68 በመቶ ሴቶች ማግጠናል ሲል አምነዋል። ነገር ግን ይህ ጥናት መሠረት አድርጎ የማጋጭ ሰንጠረዥ መሥራት ከባድ ነው።

የካልጋሪ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልቦና ባለሙያዋ ሱዛን ቡን 'ብዙ ጭንቀት የሌለባቸው ሰዎች የፍቅር አጋራችን ይማግጡብናል ብለው ስለማያስቡ የተሻለ ግንኙት ይኖራቸዋል' ይላሉ።

በተቃራኒው ተጓዳኛቸው ይማግጡብናል ብለው የሚያስቡ ሰዎች ሰላማዊ ሕይወት መኖር ይከብዳቸዋል። አልፎም የፍቅር አጋራቸውን የዕለተ'ለት እንቅስቃሴ ሲከታተሉ ነው የሚወሉት።

እውን የፍቅር ወይም የትዳር አጋርዎ ታማኝ የሚባሉ ናቸው?

የፎቶው ባለመብት, JAY DIRECTO

ስልክዎ ላይ ግንኙነት መመሥረቻ መተግበሪያዎች [ዴቲንግ አፕ] መጫን መማገጥ ይሆን? ቲንደር የተሰኘውን 'ዴቲንግ አፕ' ከሚጠቀሙ መካከል 25 በመቶ ያህሉ የፍቅር ግንኙነት ውስጥ ናቸው።

አንዳንድ ሰዎች ተማግጦብናል ብለው የሚያስቡት አጋሮቻቸው ከሌላ ሰው ጋር ሲተኙ ነው፤ ሌሎች ደግሞ ቀረብ ብሎ ማውራትንም አመኔታን እንደማጉደል ሊቆጥሩት ይችላሉ። ማገጥንም ተማገጠብን አንድ ነገር ሁላችንንም ያስማማናል - ማንኛችንም እንዲማገጥብን አንሻም።

የፍቅር ግንኙነትን የከበደ ከሚያደርጉ ኹነቶች መካከል ሰዎች ከሥራ አጋራቸው ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት ነው።

ዕድሜያቸው ከ30-40 የሚረግጥ፤ ሁሉም በፍቅር ግንኙነት ውስጥ ያሉ ሴቶች የተሳፉበት አንድ ጥናት እንዲህ የሚል ጥያቄ ለሴቶች ሰነዘረ - 'ሥራ ቦታ ላሉ ሰዎች ምን ዓይነት እሳቤ አላችሁ?'

«አልዋሽም፤ አንድ የሥራ ባልደረባዬን እከጅለዋለሁ»፤ አንድ ተጠያቂ የሰጠችው ምላሽ። «በቃ ልክ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ያለሁ ይመስል ሳየው ደስታ ይሰማኛል።»

የጥናቱ ተሳታፊ ሴቶች አካላዊ ቅርርብም ሆነ የሥራ ባልደረባ ስለሆነ ሰው ማሰብ ከመማገጥ እንደማይተናነስ ይስማማሉ።

'ጓደኛህን ንገረኝና. . .' እንደሚለው ብሂል፤ የፍቅር አጋርዎ ጓደኞች ፀባይ ስለ አጋርዎ ብዙ ነገር ሊነግርዎት ይገባል ባይ ናቸው ባለሙያዎቹ። ይህ ሕግ ለእርስዎም ይሠራል፤ ጓደኛዎት የትዳር አጋር/ሯ ላይ ከማገጡ እርስዎም ያንን ወደ ማድረግ ሊያዘነብሉ ይችላሉ።

ይህ የኒውክሌር ሳይንስ አይደለም ይላሉ የዘርፉ ሰዎች። ብዙ ጊዜ ጓደኛችን ያደረገውን ነገር ለማድረግ ድፍረቱ ይኖረናል።

አንድ ለአንድ ግንኙነት [ሞኖጋመስ] ውስጥ ያሉ ሰዎች መማገጥ ይቅርታ የሌለው ሐጥያት እንደሆነ ያምናሉ። የማገጡ ሰዎች ከጭንቀት የሚገላገሉት እውነቱን ሲተንፍሱ ይሆን? በርካቶች ይህን ተጠይቀው ከፍ ባለ ድምፅ 'አዎ' ሲሉ መልሰዋል። እውነቱን መስማት ወይም መናገር እንደ አንድ መፍትሄ ይታያል።

አሜሪካ ውስጥ ለፍቺ እንደምክንያት ከሚቀመጡ ምክንያቶች መካከል ቁጥር አንዱ ዝሙት ነው። 'የእኔ አጋርማ. . .? በፍፁም' የሚለው አስተሳሰብ ደግሞ ሰዎች ሲማገጥባቸው እጅጉኑ እንዲከፋቸው የሚያደርግ ምክንያት ነው።

በትዳር አጋርዎ ላይ ማግጠው ከሆነ እውነቱን መናገርን የመሰለ ነገር የለም፤ ተማግጦብዎ ከሆነም እውነቱን መስማት ይበጃል። ከዚህ ሁሉ በፊት ግን ስለ ግንኙነት እውነቱን በማውራት እና በመተማመን ሰላም ማስፈን ይቻላል፤ ይላሉ ባለሙያዎቹ።