ናይጂሪያዊው ኮሜዲያን ከአሻንጉሊት ጋር ትዳር ሊመሠርት ነው

ቤንጃሚን ዋቹኩ ከፍቅረኛው አሻንጉሊት ጋር
የምስሉ መግለጫ, ሹጋ ሻ በሚል የመድረክ ስም የሚታወቀው ናይጄሪያዊው ኮሜዲያን ከአሻንጉሊት ጋር ሦስት ጉልቻን አልሟል

ቤንጃሚን ዋቹኩ ይባላል። ብዙዎች ሹጋ ሻ በሚለው የመድረክ ስሙ ነው የሚያውቁት።

ዕውቅ ተዋናይና ኮሜዲያን ሲሆን እጅግ ቆንጆ ከሚላት ሴት አሻንጉሊት ጋር ኮስተር ያለ ፍቅር መጀመሩን ይፋ አድርጓል።

ይህንን ተከትሎ የናይጄሪያ ማኀበራዊ ሚዲያ በጉዳዩ ላይ ለሁለት ተከፍሏል። ጉዳዩን እጅግ አስቀያሚ ድርጊት ሲሉ የሚኮንኑና፣ ነገሩ ፌዝ ነው ልጁን ተዉት በሚሉ ወገኖች ሚዲያው እየተናጠ ነው።

አሻንጉሊቷ እስትክክል ያሉ ጥፍሮች ያሏት፥ ውድ ጌጣጌጦች የምታደርግ ሲሆን የምትቀባቸው ሽቶዎች ብዙ ዋጋ የወጣባቸው እንደሆኑ ተነግሯል።

ኮሜዲያኑ ታዲያ ከዚች ቀበጥ አሻንጉሊት ጋር ገበያ ሲሄድ፣ ሲኒማ ሲመለከት፣ በመኪና ሽው እልም ሲል ታይቷል።

አንዳንድ አድናቂዎቹ "ታስጠላለህ' ሲሉት ሌሎች "ቀውሰሀል" ለይቶልሀል እያሉት ነው።

ኮሜዲያኑ ለቢቢሲ እንደተናገረው ከሆነ ከአሻንጉሊቱ ጋር ስለጀመረው ፍቅር ለወላጅ እናቱ ማሳወቁንና እናቱ ብዙም ቅር እንዳልተሰኙበት ተናግሯል።

በመሆኑም ሽማግሌ ለመላክና ትዳሩን እውን ለማድረግ መዘጋጀቱን ጠቆም አድርጓል።

ቶንቶ እያለ የሚያቆላምጣት አሻንጉሊቱ መልከ መልካም ሴት ናት ተብሏል።

"ሰላም ትሰጠኛለች፣ አታስመስልም፣ ደግሞም ልታስቀየመኝ አትችልም።" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።