በማህበራዊ ሚዲያ ውሃ አጣጭን ለማግኘት የሚረዱ ሰባት ነጥቦች

በቡዳፔስት ከተማ ወጣት ሴት ስልክ ይዛ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አጣማሪዎን እናገናኛለን የሚሉ መተግበሪያዎች ላይ ውሃ አጣጭ መፈለግ ነውር አይደለም። ነገር ግን ፍለጋውን እርስዎ ሊወዱት ይገባል

ዛሬ፣ በፍቅረኞች ቀን፣ ሁሉም ጥንድ ጥንድ ሆኖ ሲሄድ እያዩ እርስዎ ግን ብቻዎን በመሆንዎ ቆዝመዋል? የፍቅር አጋርዎን ማግኘት ይፈልጋሉ?

እንደ ስታስቲስታ ግምት ከሆነ 240 ሚሊዮን የሰዎች ጎርፍ ወደ የፍቅር አጋር አገናኝ ድረ ገጾች ይተማሉ። ነገር ግን ሁሉም 'ያሰብኩት ተሳካ ያለምኩት ደረሰ፤ ሐሳቤም ተሟላ መንፈሴ ታደሰ' ብሎ አይመለስም።

ለዚያም ነው የፍቅርና የትዳር ግንኙነቶች አማካሪና የበርካታ መጽሐፍት ደራሲ የሆነችው ሱዚ ሄይማንን ምክር ልናካፍላችሁ የወድነው።

1. የፍቅር አጋር ለማግኘት ብለው ብቻ ቀጠሮ አይቀበሉ

ወጣት ሴት ስልኳን እየተመለከተች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ደንብ አንድ፡ ካልፈለጉ አያድርጉት

"መሞከር" አድካሚ ነው፤ ያሰለቸናል፣ ስሜታችንን ያደፈርሰዋል፤ ስለራሳችን ያለንንም ግምት ዝቅ ያደርግብናል። ስለዚህ ካልፈለጉ፤ ልብዎን ደስ ካላለው አያድርጉት። በማህበራዊ ሚዲያ የተዋወቁትን ሰው ልብዎን ካላሞቀው፣ ቀልብዎን ካልሳበው አያግኙ።

2. ደመ ነፍስዎን ይመኑ

ወጣቶች በመናፈሻ ስፍራ ቡና እየጠጡ ሲጨዋወቱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ደስ ካላለዎት ወይንም ሊያገኙ የቀጠሩትን ሰው ካላመኑት ወዲያውኑ ይወስኑ

በማንኛውም ሰዓት አደጋ የሚመስል ነገር ከሸተትዎት ወዲያውኑ እርምጃ ይውሰዱ። አንዳንዴ አእምሮ ውስጥ 'እንዲሁ ተጠራጣሪ ሆኜ' ነው የሚል ቀጭን ሐሳብ ሰበዝ መጥቶ ወይንም ሌላ ሰበብ ሰጥተው ወደ ቀጠሮዎ ሊሄዱ ይችላሉ።

ይህ ግን በማህበራዊ ሚዲያ ለተዋወቁት ሰው አይመከርም። ከተጠራጠሩ ደመ ነፍስዎን ይመኑ።

3. በማህበራዊ ሚዲያ መልዕክት ሲቀባበሉ ቁጥብ መሆን ብልህነት ነው

ተቃቅፈው በስልካቸው ላይ መልዕክት የሚጽፉ ወጣቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በማህበራዊ ሚዲያ የመልዕክት ናዳ ከማዝነብ ይልቅ ቁጥብና ወደ ነጥቡ የሚያተኩር መልዕክት መለዋወጥ ይመከራል

በማህበራዊ ሚዲያ ለተዋወቁት ሰው የመልዕክት ዶፍ ከማዝነብ ይልቅ፤ ልብዎን የሚያሞቅ ገንቢ የሆነ ጥቂት መልዕክት በቂ ነው (ከብዛት ይልቅ ጥራት)።

በፌስቡክ፣ ኢንስታግራም፣ ቲውተር፣ ቴሌግራም... ለተዋወቁት ሁሉ መልዕክት መጻፍ፣ ለተጻፈልዎት መመለስ የእርስዎንም ልብ ማፍሰሱ፣ ስሜትዎንም ማጎሹ አይቀርም። ስለዚህ ለተመረጠ ብቻ የተቀነበበ መልዕክት መላክ ብልህነት ነው።

በተለይ ሲያወሯቸው ደስ የሚልዎትን ሰው ብቻ ቢያዋሩ ጠቃሚ ነው። ያ ማለት የወደፊት አጋር የመሆን እድል ካላቸው ሰዎች ጋር መልዕክት መለዋወጥ ጥሩ ነው።

4. የፍቅር አጋርን በማበራዊ ሚዲያ ለማግኘት ከወሰኑ በርካታ ተጠቃሚ ያላቸውን መተግበሪያዎችን ይጠቀሙ

ሰው በሚተራመስበት ጎዳና መካከል ስልኳን እያየች የቆመች ወጣት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በርካታ ተጠቃሚ ያላቸው ማህበራዊ ሚዲያዎችን የሚጠቀሙ ከሆነ በርካታ ምርጫ ይኖርዎታል። ብዙም ሰው የማያውቃቸው ማህበራዊ ሚዲያዎችን ያርቁ

ልፋት ብቻ የሚያደርግዎ ተጣማሪ አገናኞችን አልያም ማህበራዊ ሚዲያዎችን ያስወግዱ። በርካታ ሰዎች ወደሚጠቀሟቸው ድረገፆች ወይም መተግበሪያዎች ጎራ ይበሉ።

በማህበራዊ ሚዲያ የፍቅር አጋር የማግኘት ጉዳይ የምርጫ ጉዳይ ነው። ምርጫ ደግሞ ካለ በርከት ያለ የሚመረጥ አጋር መኖር አለበት። ስለዚህ ከበርካታ ራሳቸውን ቀባብተው ብቅ ከሚሉ አማላይ የፍቅር አጋር ፈላጊዎች መካከል የእርስዎን እንቁ (የሚኮሩበትን) ለማግኘት ይትጉ።

5. በቅድሚያ ጓደኝነት

ወጣት ሴት ጓደኛሞች ተቃቅፈው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ከሁሉም በላይ ጓደኝነት ይቀድማል

በትዳር ረዥም ዓመት በስኬትና በደስታ የቆዩ ሰዎች፣ የትዳር አጋር ብቻ ሳይሆን ጓደኛቸውን እንዳገኙም ሲናገሩ ይደመጣል። እርስዎም የልብዎን ፍላጎት፣ በክፉ ቀን ምርኩዝ የሚሆን፣ በደስታ በሐዘን የማይለይዎትን የትዳር አጋር ለማግኘት ሲጀምሩ ከጓደኝነት ቢሆን መልካም ነው።

ግንኙነት ለትዳር ተብሎ እንደማይጀመር በፍለጋዎ የመጀመሪያው ምዕራፍ የመጀመሪያ ገጽ ላይ ማወቅ ጠቃሚ ይሆናል። ደግሞ የወደፊት ውሃ አጣጭዎን በጥሩ ጓደኛዎ በኩልም ሊተዋወቁ እንደሚችሉ ማስታወስ ተገቢ ነው።

6. ምርጫዎትን አይገድቡ

ከሰው የሚወዱትን ነገር በቀላሉ እንደሚለዩና ምን እንደሚፈልጉ የሚያውቁ ሊመስልዎት ይችላል። ነገር ግን ይህ ሰው ምኑም እኔ የምፈልገውን አይመስልም ካሉት ጋር ተጣምረው የሕይወት ዘመንዎን በደስታና በተድላ ሊኖሩ ይችላሉ።

ስለዚህ የሚፈልጉትን ለማግኘት መስፈርትዎን አያጥብቡት። ምርጫን ሳይገድቡ ግራ ቀኝ ማየት ጥሩ ነው።

ቀይ ልብ በኮምፒውተር መተየቢያ ላይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በማህበራዊ ሚዲያ ሕይወቴ ሕይወት የሚሉትን ሰው ሊያገኙ ይችላሉ፤ ያ ማለት ግን መጠናናት፣ የመምረጫ መስፈርትዎን ሁሉ አሽቀንጥረው ይጥላሉ ማለት አይደለም

7. ጥንቁቅ ይ

በኢንተርኔትና በማህበራዊ ሚዲያ የፍቅር አጋርን መተዋወቅ ግንባር ቀደም ድክመቱ የጋራ የሚሉት ሰው፣ ወዳጅ አለማወቅዎ ነው። ስለሚያገኙት ሰው ተሟላ መረጃ የሚሰጥ ማንም የለም።

ከሚያገኙት ሰው አጠራጠጣሪ ነገር በገጠመዎ ወቅት ቸል አይበሉ። በተዋወቁ ሰሞን ገንዘብ የሚጠይቁ፣ በተደጋጋሚ ሚይዙትን ቀጠሮ የሚሰርዙ፣ ስለራሳቸው በሚገባ ማይገልጽ እና ሌሎች አጠራጣሪ ነገሮች ሲፈጠሩ ይጠንቀቁ።

በስሜት አበላ አይዘፈቁ። ጥንቃቄ...ጥንቃቄ...ጥንቃቄ...