መፈንቅለ መንግሥት በአፍሪካ፡ ዴሞክራሲ በአፍሪካ አይሠራ ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, AFP
ባለፈው አንድ ዓመት ብቻ በአምስት የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ሥልጣንን በወታደራዊ ኃይል የመቆጣጠር ሁኔታዎች (መፈንቅለ መንግሥቶች) መደረጋቸውን ተከትሎ አንዳንዶች ዴሞክራሲ ለአህጉሪቱ የተሻለ ሥርዓት ላይሆን ይችላል ሲሉ አስተያየታቸውን እየሰጡ ነው።
ነገር ግን እነዚህ ውጣ ውረዶች ቢኖሩም ዴሞክራሲ ለአፍሪካ የወደፊቱ መንገድ ነው ሲሉ ሊዮናርድ ምቡሌ ንዚጌ እና ኒክ ቺዝማን የተባሉ ምሁራን ይከራከራሉ።

በአፍሪካ በቅርብ ዓመታት ውስጥ በርካታ መፈንቅለ መንግሥት መከሰቱን ተከትሎ አህጉሪቷን ወደ 1980ዎቹ ወታደራዊ አገዛዝ ዘመን የሚመልሳት አደጋ ተጋርጦባታል።
ቡርኪናፋሶ፣ ቻድ፣ ጊኒ፣ ሱዳን እና ማሊ መንግሥት በኃይል ሲገለበጥ እና በወታደራዊ ጁንታ ሲተካ አይተዋል።
በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ እና ከጥቂት ቀናት በፊት ደግሞ በጊኒ ቢሳው ያልተሳኩ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎች መደረጋቸው ሁኔታውን የበለጠ አሳሳቢ ሊያደርገው ይችል ነበር።
የከሸፉ መፈንቅለ መንግሥቶችና ሥልጣንን በኃይል የሚቆጣጠሩ አገራት መጨመር ጋር ተያይዞም በአህጉሪቷ ዴሞክራሲ አይሠራም፣ ሊሠራም አይችልም የሚሉ ድምፆችም እየጎሉ ነው።
ለነገሩ በአንዳንድ አገራት የሲቪል ፕሬዚዳንቶች በኃይል ከሥልጣን መውረድን ተከትሎ ዜጎች ደስታቸውን በአደባባይ ሲገልጹ ታይተዋል።
የመፈንቅለ መንግሥት በአህጉሪቷ መበራከት የዴሞክራሲ ማክተሚያ መሆኑን እንደ ማስረጃ አድርጎ ማየቱ የቀለለ ቢመስልም ይህ ስህተት ነው።
መፈንቅለ መንግሥት በተካሄደባቸው አገሮችም ቢሆን አብዛኛው ዜጋ በዴሞክራሲ ሥርዓት ውስጥ መኖርን ይመርጣል፤ አምባገነናዊ አገዛዝንና ጭቆናን አይቀበልም።
ምንም እንኳን የመድብለ ፓርቲ ፖለቲካ ሥርዓቱ ላይ በርካቶች እየጨመረ ያለ ተስፋ መቁረጥ ቢያሳዩም፤ በነዚህ ሥርዓቶች ያለው ዴሞክራሲ ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት ዕድገትን በማስመዝገብና የተሻለ የሕዝብ አገልግሎትን በማስገኘት ረገድ እመርታ የታየበት መሆኑንም በአሜሪካ ኮርኔል ዩኒቨርሲቲ የተደረገ ጥናት አመልክቷል።
በአንፃሩ፣ ወታደራዊ አገዛዞች ለረዥም ዘመናት የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን የሚፈጸምባቸውና የምጣኔ ሀብት ውድቀቶች የሚታዩባቸው ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, AFP
በሌላ መንገድ ብናስቀምጠው አፍሪካ በዴሞክራሲ መንገድ ታብባለች እንዲሁም ትበለፅጋለች።
ነገር ግን ችግሩ የሚመጣው ዴሞክራሲያዊ ናቸው የተባሉ መሪዎች ከሕዝባቸው ፍላጎት ውጭ በሥልጣን ላይ ለመቆየት ሲሉ ኢ-ዴሞክራሲያዊ ስልቶችን መጠቀም ሲጀምሩ ነው።
ይህ ወሳኝ ነጥብ መሆኑን መገንዘብ አለብን። እንደ ጊኒ እና ማሊ ባሉ አገራት መሪዎች ተቀባይነት ያጡት እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በመመሥረታቸው ምክንያትና ይህ የመንግሥት ሥርዓት ከአፍሪካ እውነታዎች ጋር የማይጣጣም ስለሆነ አይደለም።
ይልቁንም ፕሬዚዳንቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመጣው አለመረጋጋት በቡርኪናፋሶ እንዲሁም በማሊ የጂሃዲስት ታጣቂዎችን እንደ ሽፋንንነት በመጠቀም የዴሞክራሲ መርሆችን ስለጣሱ ነው።
በተለይም ከቅርብ ጊዜዎቹ መፈንቅለ መንግሥታት መካከል በአንዳንዶቹ ዜጎቻቸው ለምን በአደባባይ ደስታቸውን ገለጹ? የሚሉ ዜናዎችን ብንመረምር ይህ ግልፅ ይሆናል።
በጊኒ የቀድሞው ፕሬዝዳንት አልፋ ኮንዴ በአውሮፓውያኑ 2020 በአወዛጋቢ ሁኔታ ሕገ መንግቱን አሻሽለው ለሦስተኛ ጊዜ የሥልጣን ዘመን እንዲወዳደሩ አስቻላቸው።
የፕሬዚዳንቱ ውሳኔ በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነትን ያላገኘ ስትራቴጂ ነበር፣ ምክንያቱም ያደረጉት ሕገ መንግሥታዊ ሕዝበ ውሳኔም ሆነ ከዚያ በኋላ ያሸነፉት ጠቅላላ ምርጫ ነፃና ፍትሐዊ አልነበረም።
አልፋ ኮንዴ መፈንቅለ መንግሥቱ ከመከሰቱ በፊት ባሉት ወራት ተቃዋሚዎቻቸውን እና ጸረ-መንግሥት ተሟጋቾች ያሏቸውን በማሰር እና እና የኃይል እርምጃ በመውሰድ የበለጠ አምባገነንነታቸውን አሳይተዋል።
በተመሳሳይ የቀድሞ የማሊ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ቡባካር ኬይታ በአውሮፓውያኑ 2020 የነበረውን የሕግ አውጪ ምርጫን በማጭበርበር ተከሰው ነበር።
ምርጫውን ከማጭበርበር በተጨማሪ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው ሙስና እና የፀጥታ እጦት አሳሳቢነት የነበራቸውን ተቀባይነት አሳጣቸው።
በሁለቱም አገራት የሲቪል መሪዎች ከዴሞክራሲ መርሆች በማፈግፈጋቸው ተቀባይነታቸውን አጡ እንጂ ዜጎች በዴሞክራሲ ላይ እምነት በማጣታቸው ብቻ አይደለም።
የሁለቱም አገራት በርካታ ሕዝቦች ኮንዴን እና ኬይታን ከሥልጣን ያነሱትን መፈንቅለ መንግሥቶችን ቢደግፉም፤ በአፍሮባሮ ሜትር የተደረገ ጥናት 76 በመቶ የጊኒ ዜጎች እና 70 በመቶ የማሊ ዜጎች ወታደራዊ አገዛዝን እንደማይቀበሉ አረጋግጧል።
ተመሳሳይ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የዴሞክራሲ ድጋፍ በጊኒ 77 በመቶ፣ በቡርኪናፋሶ 70 በመቶ እና በማሊ 62 በመቶ ሲሆን ዜጎች ወታደራዊ ጣልቃ ገብነትን የሚደግፉት የበለጠ ውጤታማ ለሆነ የሲቪል መንግሥት መንገድ ይከፍታል ብለው ተስፋ ስለሚያደርጉ እንጂ በአምባገናነዊ አገዛዝ ሥር ለመኖር ስለሚመኙ አይደለም።
ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቶችን ይከተሉ በነበሩ አገራት መፈንቅለ መንግሥት በተደረገበት ወቅት በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት አልነበራቸውም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ለምሳሌ በሱዳን በአውሮፓውያኑ 2019 ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ የገዙት ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር በሕዝባዊ ተቃውሞ ከሥልጣን ተነሱ።
የሳቸውን ከሥልጣን መነሳት ተከትሎ የመጣው የሲቪሊያን መንግሥት ላይ ወታደራዊ ኃይሉ በቅርቡ መፈንቅለ መንግሥት ማካሄዱን ተከትሎ ከፍተኛ አመፅ ተነስቷል።
በነዚህ አመፆች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቢቆስሉም እንዲሁም ቢያንስ 79 ተቃዋሚዎች ቢሞቱም ሱዳናውያን የዴሞክራሲ መብታቸውን ከመጠየቅ ወደኋላ አላደረጋቸውም።
ዴሞክራሲ ለብዙ የአፍሪካ ማኅበረሰቦች (ገና እውን ባልሆነባቸው አገሮችም ቢሆን) ተመራጭ የፖለቲካ ሥርዓት ሆኖ እንዲቀጥል የሚሆንበት አንዱ ምክንያት የፈላጭ ቆራጭ መንግሥታት አፈጻጸም ደካማ መሆኑ ነው።
ሩዋንዳ አንድ "ጠንካራ ሰው" በአፍሪካ አውድ ውስጥ ሊያደርግ የሚችለውን በማሳየት ብዙ ጊዜ በምሳሌነት ትጠቀሳለች። መሪው ሙስናን ቀንሰዋል፣ የምጣኔ ሀብት ዕድገትንም አምጥተዋል ተብለው ይሞካሻሉ።

የፎቶው ባለመብት, AFP
ሆኖም ሩዋንዳ ከሚሊዮኖች አንዷ፣ ከደንቡ የተለየች ናት።
በአጠቃላይ በአምባገነኖችና እና በወታደራዊ ጁንታዎች ስርዓት የሚፈጠረው የተጠያቂነት እጦት ለበለጠ ሙስና እና ስኬታማ ያልሆኑ የምጣኔ ሀብት ፖሊሲዎችን ያስከትላል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ በአማካይ የአፍሪካ ዴሞክራሲያዊ አገራት የሕዝብ አገልግሎት በመስጠት የተሻለ ሥራ ሲሠሩ ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት ዕድገትም አስመዝግበዋል።
እንዲሁም አስከፊ ለሚባሉ የርስ በርስ ጦርነቶች የመጋለጥ እና ሰፊ የሰብአዊ መብት ረገጣዎችን የመፈፀም ዕድላቸው አነስተኛ ነው።
በአፍሪካ ምድር ላይ ያለው የአምባገነን መንግሥታት ደካማ አፈጻጸም እና በራሳችን ሕይወት ላይ በሚደረጉ ውሳኔዎች ላይ አስተያየት የመስጠትና የመሳተፍ ሁለንተናዊ ፍላጎት ለዴሞክራሲ የሚደረገው ድጋፍ ከፍ ያለ እንደሆነ ለማብራራት ይረዳሉ።
ለዚህም ነው ወታደራዊ ጁንታዎች የሕግ የበላይነትን ለማስፈን እና ዴሞክራሲን ለመታደግ ነው መፈንቅለ መንግሥት ያነሳነው የሚል ምክንያት የሚያቀርቡት።
በተጨማሪም ዓለም አቀፍ ውግዘቶችን እና ማዕቀቦችን ለማስወገድ ወደ መድበለ ፓርቲ ምርጫ እና ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር እንደሚመለሱ ቃል ይገባሉ።
መፈንቅለ መንግሥት ያካሄዱ አካላትም ዴሞክራሲን እናሰፍናለን በማለት ሥልጣንን በኃይል መጨበጥ ሕጋዊ ለማድረግ ይሞክራሉ።
ሁሉም ባይሆኑም በአብዛኛዎቹ ሁኔታዎች አዳዲስ ወታደራዊ መሪዎች ወደ ሲቪል አገዛዝ መመለስን ያዘገዩታል።
በአንዳንድ ሁኔታዎች ይህ የሚሆነውም በሥልጣን ላይ ሆነው የግል ጥቅም ስለሚያገኙና እሱም እንዳይቀርባቸው ሲሉ ነው። በተወሰኑት ደግሞ ከሚጠበቀው በላይ ጊዜ የሚፈጅ የፖለቲካ ፕሮጀክቶች ስላሏቸው ነው።
ነገር ግን የተረጋጋና ሁሉን አቀፍ ሥርዓት ለመዘርጋት ቃል ከገቡ በኋላ መዘግየቱ የዴሞክራሲ ደጋፊ ዜጎችን ተስፋ የሚያስቆርጥ ሁኔታ ይፈጠራል።
በመፈንቅለ መንግሥቱ ወደ ሥልጣን የመጡ መሪዎች ራሳቸው ሥልጣናቸውን በኃይል ሊነጠቁ የሚችልበት ስጋት መፈጠሩ የማይቀር ነው።
መፈንቅለ መንግሥት የዴሞክራሲ ተቋማትን በማዳከም እና በምርጫ የሚገኘውን ሥልጣን በጠመንጃ ኃይል መንጠቅ ይቻላል የሚል እሳቤ በመስጠት ሥልጣንን በኃይል መንጠቅ ከዚህ አደገኛ አዙሪት ለመውጣት ውጤታማ መንገድ ሊሆን አይችልም።
በአገራት የሚከሰቱ አለመረጋጋቶችና የፀጥታ ሁኔታዎችን ለማስጠበቅ ለፖለቲካ መሪዎች መጠቀሚያ የማይሆኑ ጠንካራ የዴሞክራሲ ተቋማትን መገንባት ያስፈልጋል።
ዜጎችን ያገለሉና ምኞታቸውን ብቻ የሚከተሉ አምባገኖች አማራጮች አይደሉም።
ጸሐፊዎቹ ሊዮናርድ ምቡሌ-ንዚዬ በአፍሪካ ሪስክ ኮንሰልቲንግ የምርምር ተንታኝ ሲሆኑ ኒክ ቺስማን በእንግሊዝ የበርሚንግሃም ዩኒቨርሲቲ የዲሞክራሲ ፕሮፌሰር ናቸው።












