'ሁላችንን ሊገድሉን አይችሉም'-የሱዳን መፈንቅለ መንግሥት ተቃዋሚዎች

የሱዳን ተቃዋሚዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሱዳን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ከተካሄደ ከሁለት ሳምንት በኋላ የዋና ከተማዋ ካርቱም ጎዳናዎች በየቦታው በተተከሉ ጊዜያዊ አጥሮች ተጨናንቀዋል።

በአብዛኛዎቹ ቦታዎች ድንጋዮች እና የተቃጠሉ ጎማዎች መኪና እንዲተላለፍ ለማድረግ ተነስተዋል። ምክንያቱ ደግሞ ከመጋረጃ ጀርባ የሚደረገው የፖለቲካ ድርድር መፈንቅለ መንግሥቱን ሊፈታ ይችላል በሚል ነው።

የመንገዱ መዘጋት፣ ተቃውሞዎች እና የሠራዊቱ አጸፋዊ ምላሽ በማንኛውም ጊዜ ሊባባስ ይችላል የሚል ሰፊ እምነት አለ።

በሽግግር መንግሥቱ ውስጥ ሴቶችን እና ህጻናትን ከጥቃት የመጠበቅ ኃላፊነት የተሰጠው ክፍል መሪ የሆኑት ሱሌማ ኤልካሊፋ "ከንግግር እና ከድርድር ውጪ መውጫ መንገድ የለም" ይላሉ።

"ሰዎች አሁን የበለጠ ቆራጥ ናቸው። የበለጠም ፖለቲካዊ ግንዛቤ አላቸው። ከ30 ዓመታት ወታደራዊ አምባገነንነት በኋላ ድጋሚ አንገዛም። ወጣቱ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነውን አገሪቱን ይወክላል። ስለዚህ ይህንን መንግሥት እንደማንፈልግ ግልጽ ነው። ሁላችንንም ሊገድሉን አይችሉም። ይህንን ህልምም መግደል አይችሉም" ብለዋል።

"ወታደሮቹ እንደ እንስሳት ናቸው"

በመፈንቅለ መንግሥቱ ወቅት በወታደሮች ተይዘው በቁም እስር ላይ የሚገኙት የሽግግር መንግሥቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ሰፊ ድጋፍ ያላቸው ይመስላል።

"ሐምዶክ ቃሉን የሚጠብቅ ሰው መሆኑን አሳይቷል። [የኢኮኖሚ ችግር ቢኖርም] ለዚያም ነው ሰዎች በእሱ የሚተማመኑት። ግብፆች፣ ሳዑዲዎች እና ሌሎችም ሃሳባቸውን እንደሚቀይሩ ተስፋ እናደርጋለን" ሲሉ ኤልካሊፋ መፈንቅለ መንግሥቱን እንደሚደግፉ በሰፊው የሚታመኑባቸውን አገራት ጠቁመዋል።

በካርቱም የሚገኘው እና የግል በሆነው የሮያል ኬር ሆስፒታል መፈንቅለ መንግሥቱን ተከትሎ በተፈጠረው የወታደራዊ ምላሽ ጉዳት ደርሶባቸው ህክምና የሚከታተሉትም ተመሳሳይ ቁርጠኝነት አላቸው።

የ18 ዓመቱ ተማሪ ሙሃየድ ፋይሰል በቅርቡ በነበረው ተቃውሞ እግሩ ላይ ሁለት ጊዜ በጥይት ተመትቷል።

የ18 ዓመቱ ተማሪ ሙሃየድ ፋይሰል
የምስሉ መግለጫ, የ18 ዓመቱ ተማሪ ሙሃየድ ፋይሰል

"ከዘጠኝ ሰዎች ጋር በጥይት ተመታሁ። ምንም አይነት የማስጠንቀቂያ ተኩስ አልነበረም፣ በቃ በቀጥታ መተኮስ ጀመሩ። ወታደሮቹ… እንደ እንስሳት ናቸው። ምናልባት እንስሳት የተሻሉ ሊሆኑ ይችላሉ" ብሏል።

በቀኝ እግሩ ላይ ሦስት ቀዶ ህክምና ተደርጎለታል። "ምክንያታችን አልተለወጠም። ወታደሩ አይገዛንም" ሲል ሐኪም እግሩን እየነካካ ሲያክመው ተናገሯል።

በአቅራቢያው ባለ አልጋ ላይ ልብስ ሰፊውና የ54 ዓመቱ ያይር መሐመድ አሊ አብደላ በዘመዶችቹ ተከቧል። በመፈንቅለ መንግሥቱ ወቅት ተቃዋሚዎችን ለመቀላቀል ሱቁን ትቶ ወጣ። በካርቱም ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አካባቢ መኪና ላይ የተጫኑ ወታደሮች ሆን ብለው በመኪና እንደገጩት ተናግሯል።

"ከዚያ በኋላ አምስት እና ስድስት ሰዎች ያለ ርህራሄ ጀርባዬ እና ደረቴ ላይ ደበደቡኝ። ወደ ሰልፉ የሄድኩት ነጻነትን፣ ሰላምንና ፍትህን ለመጠየቅ ነው። ሠራዊቱ ያንን ማድረግ ካልቻለ መወገድ አለበት። መለዮዋችሁን አስረክቡ የሚሉ መጥተው ኃላፊነቱን እንዲወስዱ ያድርጉ" ብሏል።

የ54 ዓመቱ ያይር መሐመድ አሊ አብደላ በዘመዶችቹ ተከቦ
የምስሉ መግለጫ, የ54 ዓመቱ ያይር መሐመድ አሊ አብደላ በዘመዶችቹ ተከቦ

እአአ በ2019 ሱዳንን ለረዥም ጊዜ የመሩትን ኦማር አልበሽርን በመቃወም ከስልጣን እንዲወርዱ ተደረገ። ከዚያ በኋላ ነበር የሽግግር መንግሥት የተቋቋመው።

በጦር ኃይሉ እና በሽግግር መንግሥት ውስጥ በሚሳተፉ የተለያዩ አካላት እና ድርጅቶች መካከል ሊደረግ የሚችለው ስምምነት እና ዕጣ ፈንታ ላይ መላምት አለ።

ነገር ግን በካርቱም የሚገኙ የዲፕሎማቲክ እና ሌሎች ምንጮች ድርድሩ በጠንካራ ዓለም አቀፍ ጫና እየተካሄደ በመሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያሻው በመጥቀስ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም።

መፈንቅለ መንግሥቱን የመሩት አብደል ፋታህ አል-ቡርሐን እንዳሉት ወታደሮቹ የእርስ በርስ ጦርነትን ለማስወገድ ጣልቃ መግባታቸውን ጠቅሰው በ2023 ምርጫ እንደሚካሄድ ቃል ገብተዋል።

ቢሊዮኖች ጠፍተዋል

መፈንቅለ መንግሥቱን ተከትሎ በወታደሮች በፍጥነት የተዘጋው ተቋም በሽግግር መንግሥቱ የተቋቋመው አፍራሽ ኮሚቴ ነው። ኮሚቴው በአሮጌው ሥርዓት ኃያላን ሰዎች ተዘርፏል የተባለውን ንብረት ለመንጠቅ የተቋቋመ ድርጅት ነው።

መፈንቅለ መንግሥቱ ከመደረጉ ከጥቂት ወራት በፊት ከኮሚቴው ከፍተኛ ባለሥልጣናት አንዱ የሆኑት ዋጅዲ ሳሌህ ለቢቢሲ ሥራውን አስጎብኝተዋል። ለወንጀለኝነት ማስረጃ ነው ያሉትንም ክምር አሳይተዋል።

"እነዚህ በዓለማችን ትላልቁን ሕገወጥ የገንዘብ ማሸሽን ያደራጁ ሰዎች ነበሩ። የጠፉትን በቢሊዮኖች እያደነን ነው። የድሮው አገዛዝ [አብዮቱን ለማደናቀፍ] እየሞከሩ ቢሆንም በጭራሽ አይሳካላቸውም" ብለዋል።

እሳቸው በመፈንቅለ መንግሥቱ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን በሽግግር መንግሥቱ ውስጥ ተፅዕኖ ካላቸው በርካታ ሰዎች ጋር በእስር ላይ ይገኛሉ።

"በአፍራሽ ኮሚቴው በቅርቡ የተደረገው ምርመራ በወታደራዊው ከፍተኛ ባለሥልጣናት ዘንድ ጭንቀት መፍጠሩ በሰፊው ይታመናል። ኮሚቴው ከወርቅ ዝውውር እስከ ገንዘብ ሽያጭ እና ኮሚሽኖች ድረስ የተለያዩ ጉዳዮችን በማጣራት ላይ ሲሆን ይህም በከፍተኛ መኮንኖች መካከል ከፍተኛ የሆነ ሙስና መኖሩን ያሳያል" ሲል ከአብዮቱ ጀምሮ ለሱዳን መንግሥት ሲሠራ የነበረው የቀድሞ የቢቢሲ ጋዜጠኛ ሞሃናድ ሃሺም ገልጿል።

ከመፈንቅለ መንግሥቱ በኋላ የቁልፉ ወደብ እገዳ ተነስቷል። ወታደሮቹ እገዳውን ያቀነባበሩት በሽግግር መንግሥቱ ላይ ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመፍጠር ነው ተብሎ በሰፊው ይጠረጠራል።

በዚህም በካርቱም ብዙ የምግብ አቅርቦቶች እንዲኖር እና አንዳንድ ዋጋዎች እንዲቀንሱ ረድቷል።

የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪዎች በወሰዱት ጥንቃቄ ለድርጊታቸው መሰረት ያዘጋጁ ቢመስሉም አብዮቱን ተከትሎ የመጣውን የኢኮኖሚ ችግር ተቋቁመው ለውጡን ለመደገፍ የቆረጡትን "ሰልፈኞች" በተሳሳተ መንገድ የተረዱ ይመስላል።