የኢራቁ ጠቅላይ ሚኒስትር አል-ካዲሚ ከተቃጣባቸው 'የግድያ ሙከራ' ተረፉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኢራቁ ጠቅላይ ሚኒስትር ሙስጠፋ አል-ካዲሚ በዋና ከተማዋ ባግዳድ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በደረሰ ጥቃት ጉዳት ሳይደርስባቸው ማምለጣቸውን ገለጹ።
በዋና ከተማው ግሪን ዞን የሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በፈንጅ በተሞላ ድሮን (ሰው አልባ በራሪ) ኢላማ መደረጉን ባለስልጣናቱ ተናግረዋል። ይህም በህይወታቸው ላይ የተቃጣ እንደነበርም ተገልጿል።
ቀደም ሲል መገናኛ ብዙሃን አል-ካዲሚ ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትዊተር ገጻቸው "ለኢራቅ ሲባል ሁሉም ሰው እንዲረጋጋ እና እንዲታቀብ" ጥሪ አቅርበዋል።
ስድስት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህንነት ሰዎች መቁሰላቸውን ም ባለስልጣናቱ ተናግረዋል።
በከተማዋ በርካታ የመንግሥት እና የውጭ ኤምባሲዎች ባሉበት አካባቢ ለደረሰው ጥቃት ኃላፊነቱን የወሰደ አካል የለም።
አሜሪካ ድርጊቱን አውግዛ ለምርመራው እገዛ አደርጋለሁ ብላለች።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ በሰጡት መግለጫ "ይህ በጽኑ የምናወግዘው የሽብር ተግባር በኢራቅ ግዛት እምብርት ላይ ተደርጓል" ብለዋል።
የቀድሞ የስለላ ኃላፊ የነበሩት አል-ካዲሚ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ነው ቃለ መሃላ የፈጸሙት።
ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ከኢራን ጋር ቁርንት ያላቸው የፖለቲካ ቡድኖች ደጋፊዎች በግሪን ዞን አቅራቢያ ሰልፎችን አድርገዋል።
ባለፈው ወር የተካሄደው አጠቃላይ ምርጫ የድምፅ አሰጣጥ ተጭበርብሯል አለበት ሲሉ የምርጫ ውጤቱን ተቃውመዋል።
በዚህ ሳምንት ከጸጥታ ሃይሎች ጋር በተፈጠረ ግጭት ከ100 በላይ ሰዎችም ቆስለዋል።












