በፊልም ትምህርት ቤቶች ተቀባይነት ያላገኘው ሶማሊያዊው ተሸላሚ

ባልና ሚስት እየደነሱ

የፎቶው ባለመብት, Bufo

በቅርቡ የሽልማት አሸናፊ የሆነው 'ዘ ግሬቭዲገርስ ዋይፍ' (የመቃብር ቆፋሪው ባለቤት) የተሰኘው ፊልም ልምድ ያለው ዳይሬክተር ሥራ ቢመስልም የካዳር አህመድ የመጀመሪያ ፊልም ነው።

ፊልሙን የሰራው ካዳር አህመድ የተወለደው ሶማሊያ ሲሆን የእርስ በርስ ጦርነቱን ሸሽተው ከቤተሰቦቹ ጋር በ16 ዓመቱ ነበር ፊንላንድ የገባው።

ፊልም ትምህርት ቤትም አልገባም ይህም የሆነው በምርጫ አይደለም።

"ፊልም ትምህርት ቤቶች ለመግባት ስንት ጊዜ እንዳመለከትኩ አምላክ ያውቃል። ነገር ግን ማንም ሊቀበለኝ አልቻለም" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

ለአህመድ የሶማሊኛ ቋንቋን፣ ባህልና መሰረቱን በፊልም አማካይነት ማስተዋወቅ ዋነኛ ግቡ ነው።

አህመድ ባለፈው ወር በአፍሪካ ታዋቂ በሆነው የፌስፓኮ የፊልም ፌስቲቫል ከፍተኛ ሽልማት ማግኘቱ በአፍ መፍቻ ቋንቋው ሶማሊኛ የተሰራ ፊልም ድንበር፣ አገርና ባህል ሳይወስነው መሻገር እንደቻለ ማሳያ ነው።

የቦሊውድ ተቃራኒ ሊባል የሚችለው 'ዘ ግሬቭዲገርስ ዋይፍ' አንድ ሰው የሚያፈቅራትን ግለሰብ ለማዳን የሚሄደውን ርቀት መረር ባለ ቀልድ እያዋዛ የሚነግር ታሪክ ነው።

የፊልሙ ዋና ገጸ ባህርይ ጉሌድ ከጓዶቹ ጋር ከሆስፒታል ውጪ ተቀምጦ፣ አካፋውን በእጁ ይዞ ታካሚ እስኪሞት ድረስ ይጠብቃል።

ሟቾች እየተጠባበቀ ገንዘብ ለማግኘት ፈታኝ ሥራ የሚሰራውም የታመመች ሚስቱን ናስራን በህይወት ለማቆየት ነው።

የባለቤቱ ኩላሊት ሥራ በማቆሙ ዲያሊስስ ማድረግ አለባት። የሚወዳትን ባለቤቱን ለማዳን ህክምናው ከፍተኛ ወጪ ስለሚያስፈልገውም ጉሌድ አንዳንድ ጽንፈኛ ውሳኔዎችን እንዲወስድ አስገድዶታል።

ከግሬቭዲገርስ ፊልም የተወሰደ

የፎቶው ባለመብት, Bufo Fims

የምስሉ መግለጫ, ከግሬቭዲገርስ ፊልም የተወሰደ

ቀለል ያለ ታሪክ የሚነግረው ይህ ፊልም ረዥም ፀጥታ፣ መረጋጋት እና ድንቅ መልክዓ ምድር የሚታይበት ሲሆን አህመድ ካደገባት ሶማሊያ ሩቅ ናት።

በሙዚቃ እና በዳንስ ከተሞሉ የቦሊውድ ፊልሞችና ደስተኛ ፍጻሜዎችን ከሚያስታውሱ ፊልሞችም የራቀ ነው።

"ለዚህ ፊልም ምንም ማጣቀሻ አልነበረኝም። የኔን ፊልም የትኛው ጋር እንደማነጻጽረው ስለማላውቅ የራሴን ራዕይ መፍጠር ነበረብኝ" ይላል።

እንዲያውም በየትኛውም ሲኒማ ቤት በፕሮፌሽናል ደረጃ የተሰራ የሶማሌ ፊልም አይቶ አያውቅም።

ፊልሙ 'ዘ ግሬቭዲገርስ ዋይፍ' በካንስ ፊልም ፌስቲቫል ባለፈው ሐምሌ ወር ሲታይ እናቱ በእንባ ታጥበው ነበር።

"ፊልሙን አይታ በቃላት መግለፅ አልቻለችም" ይላል።

"በርካታ ትውልዶች ራሳቸውን የሚመስሉ ሰዎች በሲኒማ ቤት የማየት ዕድሉን አላገኙም። ያንን ዕድል መፍጠር ነበር የፈለግኩት" በማለት ካዳር ያስረዳል።

'የኩራት ስሜት'

'ዘ ግሬቭዲገርስ ዋይፍ' የተቀረጸው የሶማሊያ ጎረቤት በሆነችው ጂቡቲ ቢሆንም በቀጠናው አልታየም።

በቶሮንቶ ዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫል መስከረም ላይ በርካታ ሶማሌዎችና የሶማሌ ዝርያ ያላቸው ሰዎች ተመልከተውታል።

"ሁሉም የኩራት ስሜት ተሰማቸው። ፊልሙን እየተመለከቱ ሲደሰቱ ማየት ከዚያም እየመጡ ሲያዋሩኝ ነበር" ይላል አህመድ።

ዳይሬክተሩ ፊልሙ ከእሱ በኋላ ለሚመጡ ፊልም ሰሪዎችን እንደሚያነሳሳ ተስፋ ያደርጋል።

የፊልም ትምህርት ቤት አልገባም፣ መደበኛ የዳይሬክተርነት ስልጠናም አልወሰደም እንዲሁም ከዚህ ቀደም በትልቅ ፊልም ላይ ተሳትፎ አያውቅም።

የፊልም ጉዞው የጀመረው ከአስር ዓመት በፊት ሲሆን በዚያን ወቅትም ነው የፊልሙን ረቂቅ የጻፈው።

ፊልም ዳይሬክተሩ ሲቀርፅ

የፎቶው ባለመብት, Bufo

ዋናው ነገር የነበረው ጥልቅ የፊልም ፍቅር ቢሆንም ራሱን አስተምሮ እያጠና በሶማሊኛ ቋንቋ ዳይሬክት እንደሚያደርግ ቁርጠኛ ነበር።

ከቦሊውድ የሚወጡ ፊልሞችን ከተመለከተ በኋላ የደቡብ ኮሪያና ኢራንን ጨምሮ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተውጣጡ ፊልሞችን መመልከት እንዲሁም ማጥናት ጀመረ።

ነገር ግን በፊልሙ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳረፉበት በአፍሪካ አህጉር የተሰሩ ፊልሞች ናቸው። በተለይም የፌስፓኮ የፊልም ሽልማት ሊቀመንበር የሆኑት የሞሪታንያው አብደራህማን ሲሳኮ ሥራዎችን ያደንቃል።

የቻዱ ዳይሬክተር ማሃማት ሳሌህ ሐሮን በአህመድ ላይ ተፅእኖ ካሳደሩት ባለሙያዎች አንዱ ነው። 'ስክሪሚንግ ማን' የተሰኘው ፊልሙንም አይቶ አልቅሷል።

እነዚህንም ፊልሞች በጥልቀት ካጠና በኋላ እና ቴክኒኮቹንም ለመረዳት ከሞከረ በኋላ ሁለት አጫጭር ፊልሞችን ዳይሬክት አድርጓል። በፊኒሽ ቋንቋም አንድ የፊልም ፅሁፍ ከፃፈ በኋላ ነው 'ዘ ግሬቭዲገርስ ዋይፍ'ን ወደ መስራት የሄደው።

በአሁኑ ወቅት የፊልም ትምህርት ቤት ቢገባ ኖሮ መጥፎ ወይም ጥሩ ልምድ ይኖረኝ ይሆን በማለት አንዳንዴ ራሱን ይጠይቃል።

"ወጣት አፍሪካውያን ፊልም ሠሪዎች፣ እድል የሌላቸው ፊልም ሠሪዎችን የማበረታታው ጉዳይ ቢኖር ካሜራቸውን አንስተው የራሳቸውን ታሪክ እንዲሰሩ ነው። የራሳቸውን ታሪክ ይፃፉ፣ የየቀኑ ህይወታቸውንም በካሜራ ይቅረጹ፤ እንደ ሌላው ዕድሉን ባያገኙም በራሳቸው መግፋት አለባቸው" ይላል።

እሱም ቢሆን በርካታ ዓመታትን ፊንላንድ ቢያሳልፍም ፊልሙን ግን የሰራው በአፍሪካ ነው።

"የመጣሁበትን አህጉር አስታውሳለሁ። የወደፊት የሲኒማ መዳረሻ አፍሪካ ናት። በምዕራብ አገራት መሰራት የማይችሉና መነገር ያለባቸው በርካታ ታሪኮች አሉ" ይላል።

'ትልቁ ሽልማት ፊልሜ ነው'

በፊልሙ ላይ እንዳሉት ገጸ ባህርይ ሁሉ ህይወት አስጨናቂ የሆነችባቸውና አጣብቂኝ ውስጥ የገቡ ሰዎች ታሪክ በጣም ታላቅ ፊልሞች ይሆናሉ።

የፊልሞቹን ዘውግ በተመለከተ ግን የተለያዩ ዓይነቶችን ማየትና መመራመር ይፈልጋል።

"አስቂኝ፣ ሳይንሳዊ ልብወለድ፣ አስፈሪ ሆነም ማንኛውም አይነት ፊልሞችን መስራት እፈልጋለሁ" ይላል።

ለዓመታት የለፋበትን ራዕዩን ዕውን እንዲያደርግ የፌስፓኮ ሽልማት ረድቶታል ሆኖም ግን ለእሱ ታላቁ ነገር "ፊልሙን መስራቱ ነው።"

"ይህ ሁሉ የተከናወነው በፊልሜ ምክንያት በመሆኑ በጣም ደስተኛ ነኝ" በማለት ተናግሯል።