በፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ ተጽፎ የተዘጋጀው 'ሳንኮፋ' ፊልም ኔትፍሊክስ ላይ ሊታይ ነው

የፎቶው ባለመብት, ALBERTO PIZZOLI
በኢትዮጵዊው የፊልም ባለሙያ ኃይሌ ገሪማ የተዘጋጀው 'ሳንኮፋ' በኔትፍሊክስ ሊታይ መሆኑ ተገለጸ።
እአአ 1993 የዕይታ የበቃው ሳንኮፋ ፊልም አሬይ በተሰኘ ኩባንያ በኩል ከመስከረም 14 ጀምሮ ኔትፍሊክ ላይ ለዕይታ ይበቃል።
በጥቁር የፊልም ባለሙያዎች የተሰሩ ፊልሞችን በማዘጋጀት እና በማከፋፈል የሚታወቀው አሬይ፤ ሳንኮፋ ፊልምን በኔትፍሊክስ በኩል ለተመልካቾች ለማቅረብ በመመረጤ ኩራት ተሰምቶኛል ብሏል።
በኃይሌ ገሪም ተጽፎ የተዘጋጀው ሳንኮፋ፤ ከምዕራብ አፍሪካዊቷ ጋና ተነስታ በሰሜን አሜሪካ በሚገኝ የእርሻ ቦታ ስፍራ ባሪያ ስለሆነች ሴት ውጣውረድ ያስቃኛል።
ሳንኮፋ ኔትፍሊክ ላይ ከዛሬ ሳምንት ጀምሮ ለዕይታ የሚቀርበው ወደ 4ኬ ምስል ጥራት ከፍ ካለ በኋለ ነው።
በኔትፍሊክስ ፊልሙን በአሜሪካ፣ ካናዳ፣ ዩናይትድ ኪንገድም፣ አውስትራሊያ እና ኒው ዚላንድ ለሚገኙ ተመልካቾቹ እንደሚያቀርብ በስፋት ተዘግቧል።
ለዕይታ ከቀረበ በኋላ በርካታ ሽልማቶችን ማግኘት ችሎ የነበረው ሳንኮፋ፤ አከፋፋይ በማጣቱ ኃይሌ ገሪማ በ35 አገራት ራሳቸው በመዞር ማሳየታቸው ይነገራል።
በኃይሌ ገሪማ የተዘጋጀው እና እአአ 1982 የተለቀቀው "አሽስ ኤንድ ኤምበረስ" የተሰኘ ፊልም ከዚህ ቀደም በኔትፍሊክስ አማካኝነት ለተመልካቾች ቀርቧል።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ
የ75 ዓመቱ ኃይሌ ገሪማ ተወልደው ያደጉት ጎንደር ከተማ መሆኑን ይናገራሉ።
ኃይሌ ገሪማ እናታቸው የመጀመሪያ ደረጃ መምህርት፣ አባታቸው ገሪማ ተፊካ ደግሞ የተውኔት አዘጋጅ እንደነበሩ በተለያዩ ጊዜያት በሰጡት ቃለምልልስ ላይ ተናግረዋል።
እርሳቸውም የአባታቸውን ፈለግ በመከተል የአባታቸውን ቴአትር ይለማመዱ ነበር።
ከዚያ በኋላም ኃይሌ ገሪማ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርስቲ በፈጠራ ማዕከል ውስጥ ለአጭር ጊዜ ከቆዩ በኋላ ድራማ ለማጥናት ወደ አሜሪካ ተጉዘዋል።
ኃይሌ ገሪማ ከትውልድ አካባቢያቸው ጎንደር ለከፍተኛ ትምህርት ወደ አሜሪካ የተጓዙት ከዓመታት በፊት ነበር።
ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ካሊፎርኒያ ሎስ አንጀለስ በፊልም ሙያ የማስተርስ ዲግሪያቸውን ከያዙ በኋላ በሆዋር ዩኒቨርሲቲ የፊልም ሙያን ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ አስተምረዋል።
ኃይሌ ገሪማ ከሰሯቸው በርካታ ስራዎች መካከል አወር ግላስ፣ ቻይልድ ኦፍ ሬነሰንስ፣ ሃርቨስት 3000፣ አድዋ፣ ቡሽማማ፣ ሳንኮፋ እና ጤዛ ይገኙበታል።
















