መኒ ሄይስት፡ በርካቶች በአንድ ላይ የወደዱት 'መኒ ሄይስት'

በመኒ ሄይስት ተከታታይ ድራማ ተወዳጅ ከሆኑ ገጸ ባህሪት አንዷ የሆነችው ናይሮቢ

የፎቶው ባለመብት, VANCOUVER MEDIA

የምስሉ መግለጫ, በመኒ ሄይስት ተከታታይ ድራማ ተወዳጅ ከሆኑ ገጸ ባህሪት አንዷ የሆነችው ናይሮቢ

የታሪክ መስመሩ የተዘረጋው 'ፕሮፌሰር' እያሉ በሚጠሩት ሰው አዕምሮ ውስጥ ነው።

ዓለም አይቶት የማያውቀው ዓይነት ወንጀል በአእምሮው ውስጥ አውጠንጥኗል።

የድራማው ገፀባህሪያት ማንም ላይ ጉዳት ሳያደርሱ [እንዳሰቡት ባይሳካም]፣ 'ሮያል ሚንት ኦፍ ስፔይን' ተብሎ የሚጠራውን የገንዘብ ማተሚያ ተቋም ሰብሮ በመግባት ቢሊየን የሚቆጠር ዩሮ አትሞ መስረቅ የእቅዱ አስኳል ነው።

ፕሮፌሰሩ ይህንን ህልሙን ለማሳካት ስምንት ሰዎች መልምሏል።

እነዚህ ሰዎች ደግሞ ከጀርባቸው በመሆን የሚያዘናጋቸው ታሪክ የለም፤ አጣዋለሁ ብለው እግራቸውን የሚጎትቱበት የጀርባ ምክንያት የላቸውም።

ይልቅስ ስማቸው በዓለም ላይ የሚገኙ ትልልቅ ከተሞች ስም ነው። ቶኪዮ፣ ሊዝበን፣ ናይሮቢ፣ ዴንቨር፣ . . .

ይህ በኔትፍሊክስ ላይ በአምስት ምዕራፍ እየታየ ያለው ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ተፀንሶ የተወለደው ስፔን ውስጥ ነው።

በስፓኒሽኛ 'ላ ካሳ ዴ ፓፔል' [La Casa de Papel] ይሰኛል። ወደ እንግሊዝ ሲመለስ 'መኒ ሄይስት' [Money Heist] ተብሏል።

እስካሁን ድረስ ያላዩት ከሆነ ከጀመሩት አያቋርጡትም። ተመስጠው ያዩታል፤ ተመስጠው ሳያውቁት ይጠናቀቃል።

በፍጥነት ሴራው ይወሳሰባል፤ ልብ ሰቀላው የተዋጣለት ነው። እያንዳንዶቹን ገፀ ባህሪያት የሚወዱበት ምክንያት አያጡም፤ ዝርፊያን ቢፀየፉም እንዲሳካላቸው በልብዎ ይመኛሉ።

ስምንቱ ወንጀለኞች በባንኩ ውስጥ 67 ሰዎችን አግተዋል። ገፀ ባህሪያቱ በሚገባ የተቀረጹ ናቸው፤ ኔትፍሊክስ በ190 አገራት ለሚገኙ ደንበኞቹ ያሳየዋል።

ተከታታይ ፊልሙ በመጀመሪያ ስፔን ውስጥ 'አንቴና 3' ለተሰኘ የቴሌቪዥን ጣቢያ ቢሰራም የኔትፍሊክስን ቀልብ በመሳቡ እንግሊዘኛ ተናጋሪ ታዳሚያን የበረከቱ ተቋዳሽ ሆነዋል።

ኔትፍሊክስ ከእንግሊዘኛ ቋንቋ ውጪ ከተሰሩ ድራማዎች ሁሉ ከፍተኛ እይታን ያገኘ ሲል ድራማውን ያንቆለጳጵሰዋል።

የመኒ ሄይስት ተዋንያን ቀይ ቱታ ለብሰው እንዲሁም ፊታቸውን በጭምብል ሸፍነው ይታያሉ

የፎቶው ባለመብት, ATRESMEDIA

'ላ ካሳ ዴ ፓፔል' [La Casa de Papel]

ሁሉም ነገር የውል ቋጠሮውን የሚጀምርበት ስፍራ አለው። ለመኒ ሄይስት ደግሞ የፓናማ የባሕር ዳርቻ የጥንስሱ መጀመሪያ ሆኖ አገልግሏል።

በፓናማ የባሕር ዳርቻ ጋደም ብሎ በቀጣይ ምን መስራት እንዳለበት የሚያስበው አሌክስ ፒና አንድ ሃሳብ በአእምሮው ሽው አለ።

በ2016 በወህኒ ቤት ሴት እስረኞች የሚያሳልፉትን ስቃይ እና ጭካኔ የሚያሳው እና ቪሳ ቪ [Vis a Vis] የተሰኘውን ተከታታይ ድራማ አጠናቅቆ ነበር።

ቀጣዩ ድራማ ግን እንደ ቪሳ ቪ ጭካኔ የተሞላበት እንዲሆን አልፈለገም። ደግሞም ከፍተኛ ገንዘብ የሚያስወጣ ባይሆን ይመርጣል።

ስለዚህ ቀረጻው በስቱዲዩ ውስጥ የሚጠናቀቅ፣ ነገር ግን በአራት ግድግዳ ዙሪያው ተቀንብቦ መቆየቱን የሚያስረሳ ተከታታይ ድራማ መጻፍ ፈለገ።

ታዲያ ይህንን ህልሙን ሥጋ ለማልበስ ሲያስብ ወደ አእምሮው የመጣለት 'ዝርፊያ' የሚል ነው።

ፒና የሥራ ባልደረቦቹን ሰብስቦ ሲወያይ ታሪኩ የሚያጠነጥንበት ዝርፊያው በሮያል ሚስት ኦፍ ስፔይን ውስጥ እንዲፈፀም ተስማሙ።

ይህም የፒናን የስቱዲዩ ውስጥ ቀረጻን የማጠናቀቅ ፍላጎት የሚያሟላ ነበር።

ስለዚህ ዘራፊዎቹ የባንክ ቤቱን ሠራተኞች አግተው በመያዝ ለራሳቸው ቢሊዮን ዩሮዎችን ያትማሉ።

ይህንን ዝርፊያ በበላይነት የሚመራው 'ፕሮፌሰሩ' የተሰኘው ገፀባህሪ ነው። ፕሮፌሰሩ ደግሞ በተለያዩ ወንጀሎች ተገልለው የነበሩ ወንጀለኞች መልምሏል።

ሁሉም መለያ ስም ተሰጥቷቸዋል፤ ስማቸውንም በታዋቂ የዓለማችን ከተሞች ሰይሞታል። የተሰየሙት እነዚህ ዘራፊዎች ቶኪዮ፣ በርሊን፣ ሪዮ፣ ሞስኮ፣ ናይሮቢ፣ ሄልንስኪ፣ ኦስሎ፣ እና ዴንቨር ይባላሉ።

የሚለብሱት ቀይ ቱታ፣ ፊታቸወን የሚሸፍኑበት ጭምብል በአድናቂዎቹ ዘንድ ገዝፎ እንዲወጣ አድርጎታል።

ፊታቸውን ለመሸፈን የሚጠቀሙበት ጭምብል አሁን በህይወት የሌለው እና በስፔናውያን ዘንድ ስመ ገናና በሆነው ሰዓሊ ሳልቫዶር ዳሊ የተሰራ ነው።

ይህ በስፔን ቋንቋ የተጻፈው ተከታታይ ድራማ 'ላ ካሳ ዴ ፓፔል' በሚል በስፔን ቲቪ በ2017 ለዕይታ በቅቷል።

ስፔናውያን ወደዱት።

ነገር ግን ሁለት ምዕራፍ እንደሄደ ተቋረጠ። ገፀባህሪያቱ እንዲሁም የፕሮዳክሽን አባላቱ ጓዛቸውን ጠቅልለው ወደ መደበኛ ሥራቸው ተመለሱ።

የመኒ ሄይስት ተዋናዮች

የፎቶው ባለመብት, Tamara Arranz/ Netflix

ከስፓኒሽኛ ወደ እንግሊዘኛ

'ላ ካስ ዲ ፓፔል [La Casa de Papel] በስፔን መታየት እንደ ጀመረ ነበር ከሕዝብ ፍቅር የጎረፈለት።

ታሪኩ በባላንጣዎች መካከል ግልጽ መስመር ስሎ ነው የመጣው፤ ገፀባህሪያቱ ተወዳጆች ናቸው። ወንጀለኛ ቢሆኑም እንኳ የሚታዘንላቸው ዓይነት ነበሩ።

እያንዳንዱ የወንጀሉ እርምጃ የተጠና ነው። የፕሮፌሰሩ አእምሮ የታሪኩን ድር በወጉ አድርቶታል።

ሴራውን በተገቢው መንገድ አሰናስሎታል።

የፖሊስን እርምጃ ቀድሞ አጥንቷል። በድንገቴ ጥቃት አይደናገጥም። ለእያንዳንዱ እርምጃ የተጠና መልስ አለው።

የኔትፍሊክስ የበላይ ኃላፊዎች ድራማውን ወደዱት።

ድራማው በስፔን ቴሌቪዥን ያገኘውን ስኬት ወደ መላው ዓለም ለማጋባት አሰቡ።

ይህም ደራሲው አሌክስ ፒና ከኔትፍሊክስ ጋር አዲስ ውል እንዲፈራረም አድረገው።

ተሰርተው ለተጠናቀቁትም ትርጉም እንዲሰራላቸው እና መጠነኛ ማስተካከያ እንዲያደርግበት አስተያየታቸውን ሰጡት።

ከዚያም ድራማው በድጋሚ ኤዲት ተደርጎ፣ የእንግሊዘኛ ትርጉም ገብቶለት፣ በ2017 የመጨረሻ ወር በኔትፍሊክስ መስኮት ብቅ አለ።

ይህ አዲስ ውል ተከታታይ ድራማው በመላው ዓለም እንዲታይ በሮችን ከፈተ።

ድራማውን ኔትፍሊክስ ከገዛው እና ለዕይታ ከበቃ በኋላ በተለያየ የዓለም ጫፍ ያሉ ተመልካቾች በፍቅሩ ወደቁ።

ኔትፍሊክስ ድራማው በሁለት ክፍል እንዲጠናቀቅ አልፈለገም፤ ፒና ትንሽ ረዘም አድርጎ እንዲጽፈው ጠየቁት።

ፒና ዳግም ተዋንያኑን በ2018 መጨረሻ ላይ ሰብስቦ ሦስተኛውን ምዕራፍ መጻፍ ጀመሩ። አሁን ደግሞ ዩሮ ከማተም የስፔን ባንክን ተቀማጭ ወርቅ ወደ መዝረፍ ሴራው ተሸጋገረ።

ለእንግሊዘኛ ተናጋሪዎች 'መኒ ሄይስት' በሚል ርዕስ ቀረበ።

ርዕሱ ሳቢ ነው፣ ቀላል፣ ውስጡ አንዳች አጓጊ ነገር ይዟል። ልብ ይሰቅላል።

ዘራፊዎቹም ሆነ ታጋቾቹ ቀይ ነው የሚለበሱት፤ ፊታቸውንም በተመሳሳይ ጭምብል ይሸፍናሉ፤ በዚህም የተነሳ ፖሊስ ወንጀለኛውን ከታጋቹ የሚለይበት አንዳች ፍንጭ የለውም።

ድራማው አሁን ከብራዚል፣ አርጀንቲና፣ ኡራጋይ፣ ፈረንሳይ፣ ሕንድ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ቱርክ ተሻግሮ የአፍሪካውያንን ልብ አሸንፏል።

ቶኪዮ

የፎቶው ባለመብት, VANCOUVER MEDIA

ቀዩ ቱታ

የፊልሙ ዳይሬክተር ጄሱስ ኮለሜናር፣ የስታር ዋርስን ገፀባህሪያት ዓለም እንዳወቃቸው ልክ እንደዚያው እርሱም መኒ ሄይስትን በመላው ዓለም እንዲታወቅ ይፈልጋል።

የድራማው ገፀባህሪያት እና ታጋቾች የሚለብሱት ቀዩ ቱታ፣ የፊት ጭምብል በመላው ዓለም ናኘ።

ከዝናው መግነን የተነሳም በመላው ዓለም በሚደረጉ የተቃውሞ ሰልፎች ላይ የሚሳተፉ ቱታውን ለብሰው የሚታዩ በረከቱ።

በግሪክ በሚካሄዱ የእግር ኳስ ጨዋታዎች፣ ጭምብሉን እና ቱታውን ለብሰው የሚታደሙ የእግር ኳስ አፍቃሪያን ተስተዋሉ።

በብራዚል፣ በሕንድና በፈረንሳይ ደግሞ ተመሳሳይ የባንክ ዘረፋዎችን ለመፈፀም ተሞከረ።

የተከታታይ ድራማው የሚጠቀመው ሙዚቃ በ19ኛው ክፍለ ዘመን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በጣሊያናዊው ላቦረርስ የተቀነቀነው የፀረ ፋሺስት ዜማ 'ቤላ ቻው' ዳግም አንሰራራ። በርካቶች በድጋሚ በተለያየ ስልት አቀነቀኑት።

በቲቪ ስክሪኖች ሌቦቹ 'ቤላ ቻው'ን ሲያቀነቅኑ የበርካታ ተመልካቾችን ልብን ማሸነፍ ችለዋል።

የድራማው አምስት ክፍሎች

ከ2018 የኔትፍሊክስ ተከታታዮች ያለመታከት ተመለከተቱት። የኔትፍሊክስን ፊልሞች አንዱ የሚያስወድደው ለማስታወቂያ የሚቋረጥ ደቂቃ አለመኖሩ ነው።

ቀጣዩን ክፍል ለማየት እስከ ሚቀጥለው ቀን ወይንም ሳምንት መቆየትም አይጠበቅም።

ይህ ተከታታይ ድራማ የተወደደበት ሌላ ምክንያት ለሴት ገፀባህሪያት ከወንድ አቻዎቻቸው እኩል ሚና መስጠቱ ነው።

ዓለም በፋይናንስ ኪሳራ ውስጥ በገባበት ወቅት ፀረ ካፒታሊስት አቋም ይዞ የመጣ ተከታታይ ድራማ በመሆኑም ለመወደዱ የፍቅር ቅንጣት አዋጥቷል የሚሉም አሉ።

ይህ ግን የድራማው ስኬት በሁሉም ዘንድ በእኩል ደረጃ አያስማማም።

ለምሳሌ በአንድ ወቅት በቱርክ ዋና ከተማ አንካራ የቀድሞ ከንቲባ ኢብራሂም ሜሊህ ድራማውን "የአመጽ ተምሳሌት" ሲሉ በመጥራት "ፖሊስ ጣልቃ በመግባት ሊከለክለው ይገባል" ብለው ነበር።

የድራማው ገፀባህሪያት፤ ወንጀለኞቹ የተሳሉበት መንገድ በተመልካች ዘንድ እንዲጠሉ ከማድረግ ይልቅ ዕለት ከዕለት እንዲወደዱ አድርጓቸዋል።

የገፀባህሪያቱን የኋላ ታሪክ ተመልካች በተረዳ ጊዜ "ክፉ የሚመስሉት ገፀ ባህሪያት ክፉ አለመሆናቸውን እየተረዳ ይመጣል" ሲሉ አንድ የፊልም ባለሙያ ለቢቢሲ የስፔን ቋንቋ አገልግሎት ተናግረው ነበር።

በዝርፊያ ላይ የተሰማሩት እነ ቶኪዮ፣ ሞስኮ፣ በርሊን፣ ወይም ናይሮቢ ለአገቷቸው ሰዎች የሚያሳዩት ሩህሩህነት በተመልካች ዘንድ ፍቅርን እንዲያተርፉ አድርጓቸዋል ሲሉም ያክላሉ።

ኔትፍሊክስ ስፔናውያን የኮመኮሟቸውን ሁለት ምዕራፎች፣ ሁለት በመጨመር አራት ምዕራፎችን ለዓለም ሕዝብ አቀረበ።

አምስተኛውና የመጨረሻው ምዕራፍ ደግሞ በቅርቡ ተለቅቋል።

እስካሁን የአምስተኛው ምዕራፍ አምስት ክፍሎች ብቻ የተለቀቁ ሲሆን ቀሪዎቹ አምስት ክፍሎች ደግሞ በታኅሣሥ ወር ለዕይታ እንደሚበቁ የኔትፍሊክስ መረጃ ያሳያል።

እስከዚያው ሚሊዮኖች በአንድነት በጉጉት ይጠብቃሉ።