ኪነ ጥበብ፡ በ40 ተከታታይ ክፍል የተጠናቀቀው የእግር እሳት ድራማ

የፎቶው ባለመብት, ABRICOM MULTIMEDIA
የእግር እሳት ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ በ40 ተከታታይ ክፍል ሲተላለፍ ቆይቶ ባሳለፍነው ሳምንት ተጠናቋል።
የእግር እሳት በተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን አድርጎ ፍትህን ፍለጋ በሚኳትኑ ገጸ ባህርያት ልብ አንጠልጣይ ድርጊቶች የተሞላ ነበር።
በዚህም የበርካቶችን ዐይንና ልብ መያዝ እንደቻለ ይነገራል።
የድራማው ደራሲና ዳሬክተር አብርሃም ገዛኸኝ በአንድ ወቅት ለሥራ ወደ ለንደን አቅንቶ በነበረበት ወቅት ያነበበው መጽሐፍ ለድራማው መነሻ እንደሆነው ይናገራል።
መጽሐፉ ኒኮላስ ቤሌክ በሚለው የብዕር ስሙ የሚታወቀው ጸሐፊ የሴሲል ደይ ልዊስ 'ዘ ቢስት መስት ዳይ' ነው።
"መፅሐፉን ሳነበው በመጀመሪያዎቹ አራት ገጾች ውስጥ የድራማው ተዋንያኖቹ ምን እንደሚሆኑ፤ ምን እንደሚፈልጉ አወቅኩኝ" ይላል አብርሃም።
የድራማው አፅመ ታሪክም በሚገባ ተዋቅሮ፤ አጓጊ እና ኢ-ተገማች በሆኑ የታሪክ ፍሰቶችና ሁነቶች ተሰናስሎ ነበር ለተመልካች የቀረበው።
አብርሃም እንዳለው ድራማው ከታሪኩ ጥንስስ ጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ድረስ አራት ዓመታትን ፈጅቷል።
አራት ሚሊየን ብር ገደማም ወጥቶበታል ብሏል።
የእግር እሳት በታሪኩ፣ በዳሬክቲንጉ፣ በቀረጻውም ሆነ በተዋንያኑ ብቃት በርካቶች አወድሰውታል።
ይህ ግን በቀላሉ የመጣ አልነበረም።
አብርሃም ወትሮም ቢሆን ተከታታይ ድራማዎችን ሲመለከት "ቢሻሻል" ሲል የሚያወጣቸውና የሚያወርዳቸው ሃሳቦች ነበሩት።
አሁንም ግን "በውስጤ ያሰብኩት ከዚህ የተሻለ ነበር። ያንን ማውጣት አልቻልኩም " ይላል፤ የገንዘብ እና የአቅም እጥረት ባሰበው ልክ እንዳይሰራ ተግዳሮት እንደነበሩበት በመግለፅ።
ሆኖም ድራማው "በአቀራረቡና በአተራረኩ የተለየ ነበር" ብሏል።
የእግር እሳት ድራማ ታዋቂና አዳዲስ ተዋንያንን ያሳተፈ ነው።
የተዋንያንን መረጣ በተመለከተም ዋናው ገጸ ባሕርይ [አንተነህ] ከተመረጠ በኋላ ታሪካዊ ዝምድና ያላቸውን በመልክ እና በፊት አገላለጻቸው መመሳሰል እንደመረጣቸው አብረሃም ይናገራል።
መረጣው ዋናው ገጸ ባሕርይ ከሌሎች ገጸባህርያት ጋር ባለው ታሪካዊ ትስስር መመሳሰል ላይ የተመሰረተ ነው።

የፎቶው ባለመብት, ABRICOM MULTIMEDIA
'የእግር እሳት' መሪ ተዋንያንምን ይላሉ?
በድራማው ላይ ዋና ገጸ ባህርይውን አንተነህን ወክሎ የተጫወተው ብርሃኑ ድጋፌ፤ "የእግር እሳት ሲጀመር አልቆ ነው የተሰራው" ይላል።
እርሱ እንደሚለው ማን ምን እንደሚሰራ እስከመጨረሻው ታውቆና በቂ ዝግጅት ተደርጎበት የተሰራ ነው።
ታሪኩም ቀድሞውኑ በወረቀት ላይ ጥንቅቅ ብሎ በማለቁ ድራማውን የተለየ እንደሚያደርገው ገልጿል።
ብርሃኑ በድራማው የተሳተፉ ባለሙያዎችም ሥራቸውን ጠንቅቀው መሥራታቸው ድራማው በተገባው ጊዜና ሁኔታ እንዲጠናቀቅ አድርጎታል ይላል።
ብርሃኑ ድጋፌ በአብርሃም ገዛኸኝ ድርሰት ላይ ሲሰራ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። "ትውልድን የሚያስተምሩ ታሪኮች ላይ መስራት ፍላጎቴ ነው" የሚለው ብርሃኑ፤ ከእዚህ ቀደም 'የነገን አልወልድም' በተሰኘው የአብርሃም ድርሰት በሆነው ፊልም ላይም ተውኗል።
በድራማው የልዕልናን ገጸባህርይ ወክላ የተወነችው ተዋናይት መስከረም አበራ በበኩሏ፤ የእግር እሳትን "ምዕራፉ አጭር የሆነ፣ ሴራው በአቀራረፅና በታሪኩ ለየት ባለ በድርጊት የተሞላ ድራማ ነው" ስትል ትገልጸዋለች።
ገጸ ባህሪዋ ልዕልና የተለያዩ ገጸባህርያትን ወክላ የምትጫወት በመሆኗም ፈታኝ እንደነበር ትናገራለች።
"የታሪኩ አካሄድ ያልተጠበቀ ነበር። መልዕክቱም ጥሩ ነበር" ትላለች።
መስከረም የእግር እሳት ድራማ የተለያዩ የቴሌቪዥን ማስታወቂያዎችን ለመስራትም እድል ፈጥሮልኛል ብላለች።

የፎቶው ባለመብት, ABRICOM MULTIMEDIA
ደራሲና ዳሬክተር አብርሃም፤ ከዚህ በፊት የውጭ የባህል ተፅእኖ ያለባቸው ተከታታይ ድራማዎች በአንድ ማኅበረሰብ ባሕል ላይ የሚፈጥረው ለውጥ ላይ ያተኮረ የሁለተኛ ዲግሪ የመመረቂያ ጽሁፍ ሰርቷል።
በዚህ ጥናቱም ማኅበረሰቡ ከተከታታይ ድራማዎች የወደዳቸውንና የጠላቸውን ነገሮች መለየት መቻሉን አስረድቷል።
የጥናቱ ተደራሾች፤ ልዩ ገፀ ባህሪያትን፣ የተጎዱ ሰዎች ታግለው ሲያሸንፉ፣ ፍትህ ሲከበር ማየት እንደሚሹ ከመመረቂያ ጽሁፉ መረዳት ችሏል።
ይህም በተወሰነ መልኩ ለድራማው ግብዓት እንደሆነው ጠቅሷል።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ መገኘቱ የተረጋገጠው ድራማው በእረፍት ላይ በነበረበት ጊዜ በመሆኑና በርካታ ክፍሎች ቀድመው በመዘጋጀታቸው ወረርሽኙ በድራማው ላይ እምብዛም ተፅዕኖ አላደረሰበትም።
በእርግጥ ሁለት ተዋንያን በወረርሽኙ ተይዘው ከበሽታው አገግመዋል።
'የአስከሬን ሰብሳቢው' ታሪክ
በ1969 ዓ.ም [እአአ1977] በኢትዮጵያ የሆነ ነው።
ወጣቶች በአደባባይ በየቦታው በግፍ በሚገደሉበት የቀይ ሽብር ዘመን። የታሪክ ድርሳናት እንደሚያስረዱት በዚህ ዘመን የሰው አስከሬን በየቦታው እንደዘበት ተጥሎ እየተለቀመ ይነሳ ነበር።
ታሪኩም አስከሬን የሚያነሱ የአምቡላንስ ሹፌር የሆኑ አባት ታሪክ ነው።
የሌሎችን አስከሬን ሲያነሱ የልጃቸው ሬሳ አግኝተው ማንሳት ያቃታቸው የእኝህ ሹፌር ታሪክ ቀጣዩ የአብርሃም ገዛኸኝ "መሃል ሰፋሪ" የተሰኘው ፊልም ማጠንጠኛ ነው።
አብርሃም እንደገለፀልን ይህን ሥራውን፤ ፊልሞች ታሽተውና አድገው የሚወጡበት አፍሪካዊና ዓለም አቀፋዊ የፊልም ቤተሙከራዎች ተቀብለው አሳድገውታል።
ፕሮዲዩሰሮችም ፍላጎት እያሳዩ ነው ብሏል።
የዚህ ሥራው ፕሮዲዩሰሮች ካናዳዊያን እንደሆኑም ፍንጭ ሰጥቷል።
ከዚህም ባሻገር ከወራት በኋላ አስቂኝ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ [ሲትኮም] በኢቢኤስ ቴሌቪዥን ለዕይታ ለማብቃት በዝግጅት ላይ መሆኑን ገልጿል።
















