ኢንስታግራም የዕድል በር የከፈተላቸው ኢትዮጵያውያን

የፊልም ባለሙያዋ ሃናን ታሪክ

የፎቶው ባለመብት, Hanan

ብዙዎች ወደ ኢንስታግራም ጎራ ብለው ፎቶዎችን ወይም አጫጭር ቪዲዮችን ይመለከታሉ። አሊያም በተቃራኒው - የእነሱን ያጋራሉ።

ሌሎች ደግሞ ከዚህ ተሻግረው ኢንስታግራም የፈጠራቸውን እድሎች 'ሳይባዝኑ' ይጠቀማሉ።

ይህም ለአንዳንዶች 'ወደ ኪስ' የሚገባ በረከት ይዞ ሲመጣ ለሌሎች ደግሞ ዓለም አቀፍ የሥራ ግንኙነት ዕድልን ጀባ ብሏቸዋል።

በኢንስታግራም በቀላሉ የሥራቸውን ውጤት ለአስር ሺዎች እያጋሩ ገበያቸው ከደራላቸው ጀምሮ ዓለም አቀፍ ምርቶችን ለማስተዋወቅ የበቁ ኢትዮጵያውያን አሉ።

እናም ይህ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ የዕድል በር ከከፈተላቸው አራት ኢትዮጵያውን እንስቶች ጋር ቢቢሲ ቆይታ አድርጓል።

ኢንስታግራምን እንዴት የገቢ ምንጭ ማድረግ ይቻላል?

በኢንስታግራም አማካኝነት ገንዘብ የሚሰሩ በርካታ ሰዎች አሉ። አንዳንዳንዶቹ በጥቂቱ የጀመሯቸውን ሥራዎች በገጹ አማካኝነት በተከታታይ በማጋራት ደንበኞችን ለመሳብ ይጠቀሙበታል።

ሌሎች ደግሞ በማኅበራዊ የትስስር መድረኩ ላይ ያላቸውን ተጽዕኖ ትኩረታቸው ወጣትና ሴቶች በሆኑ ተቋማት ተፈላጊ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። የአራቱ ኢንስታግራም ተጠቃሚ ሴቶች ተሞክሮ ለዚህ ምስክር ነው። እንዴት?

የሜካፕ ባለሙያዋ ፍፁም ይልማ ወይም ጃፒ 'ሜካአፕ ባይ ጃፒ' የተሰኘውና ከ70 ሺህ በላይ ተከታዮች ባሉት የኢንስታግራም ገጿ የሥራዎቿን ውጤቶች ታጋራለች።

ሥራዋን 'በትንሽ' መሳሪያ ከስድስት ዓመታት በፊት የጀመረችው ባለሙያዋ ያስዋበቻቸውን ሰዎች ፎቶዎች የምታጋራበት ይህ ገጽ 'ገበያዋን እንዳደራው' ትገልጻለች። "ብዙ ሰው ኢንስታግራም አይቶ ነው የሚያገኘኝ።"

ዘጠና በመቶ የሚሆነው ሥራዋ በኢንታግራም አማካኝነት የሚመጣ ነው የምትለው ጃፒ በተለያዩ ዓለማት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጭምር ሥራዎቿን በማየት ወደ'ሷ እንደሚመጡ ታስረዳለች።

'እንቁ ዲዛይን' በሚለውና ከ118 ሺህ በላይ ተከታዮች ባሉት ገጿ አማካኝነት የምታዘጋጃቸውን ባህላዊ አልባሳት 'ፖስት' በማድረግ በርካታ ደንበኞች እንዳፈራች የምትገልጸው ደግሞ ዲዛይነሯ እንቁጣጣሽ ክብረት ነች።

እንቁጣጣሽ እንደሠርግ ባሉ ሁነቶች ላይ የሚለበሱ አልባሳትን በማዘጋጀት ዘጠኝ ዓመታት ቆይታለች። ሆኖም ከአምስት ዓመታት በፊት የኢንስታግራም ገጽ በመክፈት ሥራዎቿን ማጋራት ከጀመረች በኋላ የደንበኞቿ ቁጥር ከፍ እያለ መጥቷል።

"[ኢንስታግራም] በጣም ነው ገበያው እንዲደራ ያደረገው ከአገርም አልፎ ውጪ ያሉት በደንብ እንዲያውቁትና የምንሰራውን ሥራ በደንብ እንዲከታተሉት ትልቅ አስታዋጽኦ አድርጎልናል" የምትለው ዲዛይነሯ በኢንስታግራሟ አማካኝነት ደንበኞች ዋጋና ሌሎች መረጃዎችን ከመጠየቅ ጀምሮ ግብይት እስከመፈጸም እንደሚደርሱ ትናገራለች።

ባለሙያዎቹ አገልግሎታቸውን ያገኙ ታዋቂ ሰዎችን ምስሎች በሚያጋሩበት ወቅት የተከታዮቻቸውና የደንበኞቻቸው ቁጥር ከፍ እንደሚልም ይጠቅሳሉ።

ዮዳን ኤፍሬም

የፎቶው ባለመብት, Yaoadan Ephrem

በሌላ በኩል በገነቡት ስምና በኢንስታግራም ባለቸው ተከታዮች ምክንያት ማኅበራዊ ገጹ የተለያዩ ዕድሎች የሚያመጣላቸውም አሉ።

ከ290 ሺህ የሚልቁ ተከታዮች ያሏት የፊልም ባለሙያዋ ዮዳን ኤፍሬም ኢንስታግራም አንዱ የገቢ ምንጯ እንደሆነ ገልጻለች። የተለያዩ ተቋማትን መልዕክቶች በገጿ አማካኝነት ፎቶዎችን ወይም አጭር ቪዲዮችን በመለጠፍ ገንዘብ ታገኛለች።

"ኢንስታግራም ለኔ ገንዘብ ለማግኘት በደንብ አግዞኛል። ካሉኝ ሥራዎች አንዱ የተለያዩ ምርቶችን ገጼ ላይ ማስተዋወቅ ስለሆነ በደንብ ገንዘብ ለማግኘት ረድቶኛል።"

ከዚህም ባሻገር ዮዳን ያላትን የሥራ ግንኙነት አድማስን እንድታሰፍ ማኅበራዊ ገጹ እድል እንደፈጠረላት ታስረዳለች።

በቅርቡ የኢንስታግራም ተከታዮቿ ቁጥር አንድ ሚሊዮን የደረሱላት የፊልም ባለሙያዋ ሃናን ታሪክ ከሰባት ዓመታት ለሚልቅ ጊዜ በኢንስታግራም ላይ ተሳትፎ የነበራት ቢሆንም ያለፉት ሁለት ዓመታት ግን 'ወደ ገንዘብ የተቀየረ ጥቅም' ይዞ የመጣበት ነበር።

ተዋናይቷ ከወሊድ በኋላ 'ሥራ በጠፋባቸው ጊዜያት' ኢንስታግራም ፎቶዎችንና ቪዲዮዎችን ከማጋራት ባሻገር 'ቢዝነስ ለመስራት' ያለውን ጥቅም እንድትገነዘብ እንዳስቻላትም ገልጻለች።

ኢንስታግራም 'በየቀኑ ከአድናቂዎቼ ጋር እንድገናኝ' እድል መስጠቱ ከማኅበራዊ ገጹ ያገኘሁት የመጀመሪያ ጥቅም ነው ስትል የምታስረዳው ሃናን በሌላ መንገድ ደግሞ "መነሳሳት የሚፈጥሩላትን ከአገር ውስጥም ይሁን ከውጪ ያሉ ሰዎች በየቀኑ ለመከታተልና ይበልጥ እድል ፈጥሮልኛል" ትላለች።

በተጨማሪም ደግሞ ከፋሽንና መሰል ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ወቅታዊ ሁኔታዎችን ማወቅም ከኢንስታግራም ከምታገኘው ጥቅሞች መካከል መሆኑን ትጠቅሳለች።

"ኢንስታግራም የገቢ ምንጬ ነው" ነው ስትል የምትጠቅሰው ሃናን የተለያዩ ተቋማት ምርቶችንና አገልግሎቶችን በተለያየ መንገድ ታስተዋውቃለች።

"ኢንስታግራም ላይ ፖስት እንዳደርግላቸው ከፈለጉ ለእሱ የሚከፍሉት ብር ይኖራል . . . በዚህም አሪፍ ብር አገኝበታለሁ" ብላለች።

ለሃናን ኢንስታግራም በዓለም በአቀፍ ደረጃ እውቅና ያላቸው ምርቶችን እንድታስተዋወቅም እድል ፈጥሮላታል።

"በፊት ራሳችንን የምናስተዋውቀው መጽሄት እና በቲቪ ላይ ነበር። አሁን ራሳችንን ያለማንም ኤጀንት [ወኪል] ኢንስታግራምን ብቻ በመጠቀም ለዓለም የምናስተዋውቅበት እድል ነው ብዬ አምናለሁ" ስትል አስረድታለች።

እናም በዚህ 'ዕድል' አማካኝነት ለሦስት ዓለም አቀፍ ድርጀቶች ምርቶችን ለማስተዋወቅ ተፈራርማለች።

"እነዚህ ሥራዎች ሞራልና ተስፋ ሆነውኛል። ሁለተኛ ደግሞ ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጀቶች ወደእኔ አይናቸውን እንዲያዞሩ ይረዳኛል ብዬ አስባለሁ።"

በኢንስታግራም እንዴት ውጤታማ መሆን ይቻላል?

እንደ ሃናን ገለጻ በኢንስታግራም ውጤታማ መሆን የሚፈልግ ሰው የመጀመሪያው እርምጃ የሚፈልገውን ማወቅና ችሎታን መለየት ነው።

"ሁሉንም ነገር ከመነካካት አንድ የሚፈልጉበትና የሚያምኑበት ነገር ላይ ትኩረት ቢያደርጉ ውጤታማ ይሆናሉ ብዬ አምናለሁ።"

ማንኛውም ሰው ያለውን አቅምና ችሎታ ለማሳየት እንዲሁም ከፈላጊዎቹ ጋር ለመገናኘት ኢንስታግራም ምቹ መድረክ ስለመሆኑ ያነሳችው ተዋናይቷ ማኅበራዊ ትስስር ገጹ ማንኛውም ሰው በቀላሉ ሊጠቀምበትና የስኬቱ መንገድ ሊያደርገው ይችላል ትላለች።

ይህንን ሀሳብ ዮዳን ኤፍሬምም ትጋራዋለች። "ሁሉም ሰው የየራሱ ተሰጥኦ አለው። መጀመሪያ ያንን መረዳት ያስፈልጋል። በምን በኩል ለውጥ መፈጠር እንደምንችል ካወቅን በኋላ በዚያ መግፋት ያስፈልጋል" ስትል ትገልጻለች።

ዮዳን በኢንስታግራም ውጤታማ የሚያደርገው መሰረታዊ እርምጃ የነቃና ተከታታይ ተሳትፎ መሆኑንም ታስረዳለች።

"በምን በኩል ተከታዮቻችንን ማሳደግ፣ በምን በኩል ሥራችንን ማስተዋወቅ፣ ራሳችን ማስተዋወቅ እንደምንችል አንዴ ካወቅን በኋላ ጊዜን በማይሻማ መልኩ 'አክቲቭ' መሆን ያስፈልጋል" ብላለች።

በተለያዩ ሥራዎች የተሰማሩ ሰዎች በኢንስታግራም ሥራዎቻቸውን በማስተዋወቅ 'ሞቅ ያለ ገበያ' ማግኘት እንደሚችሉ የምትጠቅሰው እንቁጣጣሽ፤፤ ማኅበራዊ ገጹ የፈጠራ ሥራዎችን ወይም ሌላ 'ቢዝነስን' በየዓለም ዙሪያ ላሉ ሰዎች የማስተዋወቅ ዕድል እንደሚሰጥ ታነሳለች።

ይህ ግን ሳይታክቱ መስራትን ይጠይቃል። "ሥራው ላይ ትኩረት አድርጎ በየጊዜው አዳዲስ ነገሮችን ፓስት ማድረግ ያስፈልጋል። በተከታታይ ፖስት ማድረግ ያስፈልጋል። ይህ ከተደረገ ገበያውን ያነቃቃዋል። ለመተዋወቅም እድል ይሰጣል" ስትል ታብራራለች።

ዲዛይነሯ "ማንኛውንም የፈጠራ ሥራ ይዞ ኢንስታግራም ላይ መውጣት ትልቅ አስተዋፅኦ ያደርጋል። ሥራን በቀላሉ ለማስተዋወቅ ይረዳል" ስትልም ገልጻለች።

ቀደም ብሎ ሥራዎችን ለማስተዋወቅ የነበረውን ልማድ ኢንስታግራም ቀይሮታልም የምትለው እንቁጣጣሽ "ቲቪ ላይ ወይም ሬዲዮ ላይ ቢሆን ገንዘብ ተከፍሎ ለተወሰነ ጊዜ ነው የሚተዋወቀው። ይህ ግን በተፈለገው ሰዓት እየተለቀቀ ለደንበኞች በዓለም አቀፍ ደረጃ ላለው ገበያ ማሳየት ይቻላል" ስትል ትናገራለች።

በኢንስታግራም አማካንኝነት የሚደርሷትን መልዕክቶች "በተቻላት አቅም" ለመከታተልና ምላሽ ለመስጠት እንደምትሞክር የምትጠቅሰው ጃፒ ተከታታይ ተሳትፎ በኢንስታግራም ውጤታማ እንደሚያደርግ ትገልጻለች።

ይህንንም ስታስረዳ የኮሮናቫይረስ ውረርርሽኝ በተከሰተበት ወቅት በማኅበራዊ መድረኩ ላይ ብዙም ስላልሰራች የተከታዮቿ ቁጥር ባለበት ቆሞ ነበር።

በዚህም መድረኩ 'ኢንጌጅመንት' [ተሳትፎ] ይፈልጋል። ሁልጊዜ አንድ አይነት ነገር ሳይሆን የተለያዩ ይዘቶችን በማካተት 'ሃሽታግ' [#] በመጠቀምና በማያያዝ ውጤት ማግኘት እንደሚቻል ጠቅሳለች።

ኢንስታግራም የዕድል በር የከፈተላቸው እነዚህ የማኅበራዊ መድረኩ ተጠቃሚዎች ተከታታይ ተሳትፎ ማድረግና 'ሥራዬ ብሎ' መያዝ በቀላሉ አቅምን ለማሳየትና ከሰፊው የዓለም ገበያ ጋር ለመገናኘት ቁልፉ እርምጃ መሆኑን ይስማሙበታል።

ስለኢንስታግራም የምናውቃቸው ጉዳዮች?

የምስሎችና ተንቀሳቃሽ ቪዲዮዎች ማጋሪያ የሆነው ኢንስታግራም እንደ አውሮፓው የዘመን ቀመር በ2010 ወደ ሥራ ሲገባ ኢላማ ያደረገው የአይፎን ተጠቃሚዎችን ብቻ ነበር።

ሆኖም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ለአንድሮይድ ተጠቃሚዎችም ቀርቧል። የኮምፒውተር ፕሮግራመሩ አሜሪካዊው ኬቨን ሳይስትሮምና የብራዚልና የአሜሪካ ዜግነት ያለው ማይክ ክሬገር በጋራ የመሰረቱት ኢንስታግራም እንደ አውሮፓውያኑ በ2012 በ1 ቢሊዮን ዶላር ለፌስቡክ ኩባንያ ሽጠውታል። ሆም ኬቨን ሳይስትሮም አሁንም የኢንስታግራም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ነው።

በዓለም ዙሪያ ከአንድ ቢሊዮን የሚልቁ የኢንስታግራም ተጠቃሚዎች ያሉ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 33 በመቶ የሚሆኑት ከ25 እስከ 34 የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው።

ቢቢሲ ከሳምንታት በፊት ባወጣው መረጃ ኢንስታግራም እንደ ጃፒና እንቁጣጣሽ ባሉ የ'የቢዝነስ' ሰዎች ተመራጭ እየሆነ ስለመምጣቱ ዘግቧል።

ኢንስታግራም ከፍተኛ ተጠቃሚዎች ያሉት በአሜሪካና በሕንድ ሲሆን አገራቱ በተናጠል ከ120 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የኢንስታግራም ተጠቃሚዎች ናቸው።

የማኅበራዊ መድረኩ አንዱ መገለጫ የሆነውና ለ24 ሰዓታት ብቻ የሚቆይ ምስል የሚጋራበት 'ስቶሪ' የተሰኘውን አገልግሎት 500 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በየቀኑ እንደሚጠቀሙት ኩባንያው ያወጣው መረጃ ይገልጻል።

በሌላ በኩል በወር 800 ሚሊዮን ንቁ ተጠቃሚዎች [active users] አሉት።

ኢንስታግራም በራሱ መስፈርት ከፍተኛ ተከታይና ተጽዕኖ ላላቸው ተጠቃሚዎች ክፍያ ይፈጽማል። ይህ ሥርዓት በኢትዮጵያ እስካሁን ባይጀመርም ማኅበራዊ ገጹ ከወዲሁ የገቢ ምንጫቸው የሆኑ ኢትዮጵያውያን እየተበራከቱ ነው።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, "በቲክቶክ የገቢ ምንጭን ጨምሮ ሦስት ዕድሎች አግኝቸበታለሁ" የትናየት ታዬ