እንዴት የእንቁላል ምስል ኢንስታግራም ላይ 46 ሚሊዮን 'ላይክ' አገኘ ?

እንቁላሉና ኬሊ ጄነር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, እንቁላሉና ኬሊ ጄነር

እንደው የኢንተርኔት ነገር ድንቅ አይሎትም?

ከ46 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ኢንስታግራም ላይ የተለጠፈ የእንቁላል ምስልን ወደውታል ወይም 'ላይክ' አድርገውታል።

የዚህ እንቁላል ባለቤት ማን እንደሆነ፣ ፎቶው መቼ እንደተነሳ፣ እንቁላሉ ጫጩት ይሁን ወይም ተጠብሶ አሊያም ተቀቅሎ ይበላ የሚቃወቅ ነገር የለም። የሚታወቀው ከ46 ሚሊዮን በላይ ሰዎች 'ላይክ' እንዳደረጉት ብቻ ነው።

የእንቁላሉ ፎቶ ከመለጠፉ በፊት፤ የቴሌቪዥን መሰናዶ አዘጋጇ ኬሊ ጄነር አምና የተወለደ ልጇን ያስተዋወቀችበት ዜና 18 ሚሊዮን 'ላይክ' በመሰብሰብ ሪከርዱን ይዞ የነበረው።

ከቀናት በፊት ማለትም ታህሳስ 26፤ ማንነቱ ያልተወቀ የኢንስታግራም ተጠቃሚ፤ ዎርልድ_ሪኮርድ_ኤግ ("world_record_egg") የሚል የኢንስታግራም ገጽ በመፍጠር የእንቁላሉን ፎቶ በመለጠፍ 46.8 ሚሊዮን 'ላይክ' ማግኘት ችሏል።

ከእንቁላሉ ጋር አብሮ የተለጠፈው ጽሁፍ ''በኢንስታግራም ገጽ ላይ ብዙ 'ላይክ' በማስገኘት የዓለም ሪኮርድን አብረን እናስመዝግብ'' ይላል።

እንደተባለውም ሆነ። ከሁለት ቀናት በፊት ሪኮርዱ ተሰብሯል።

የኢንስታግራም ገጹን ማን እንደሚያስተዳድረው አይታወቅም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የኢንስታግራም ገጹን ማን እንደሚያስተዳድረው አይታወቅም

ሪኮርዱን የተቀማችው ኬሊ ጄነር፤ እንቁላል ስትሰብር የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል ''ይህን ደቃቃ እንቁላል አንሳው/ሺው'' ከሚል ጽሁፍ ጋር በኢንስታግራም ገጿ ላይ ለቃለች።

ኬሊ ጄነር በኢንስታግራም ገጿ ላይ በስፖንሰር ለምትለጥፈው አንድ ማስታወቂያ አንድ ሚሊዮን ዶላር ታስከፍላለች።