' በ70 እና 17 ዓመት ሴት መካከል ልዩነት አለ ብለህ ነው?' ማርሊታ ተመስገን

ከማኅበራዊ ሚዲያ ምን አተረፍሽ?
የገንዘብ ጥቅም የለውም። ሰዎችን ለማስደሰት ብቻ ነው የምሠራው። በርካታ ሰዎች ቀልዶቼን አስቂኝ ሆነው ያገኟቸዋል። 'ጥቂት ደቂቃዎችን መስዋእት አድርጌ በርካቶችን ፈገግ ማድረግ ከተቻለኝ ለምን በቋሚነት አላደርገውም' ብዬ አስቂኝ ቪዲዮዎችን መለጠፍ ጀመርኩ። ሰው በገንዘቡ ወይም በዕውቀቱ ይረዳል። የኔም ቀልዶች በሰዎች ውስጥ የደስታ ስሜት የሚፈጥሩ ከሆነ ለምን አላደርገውም ብዬ ነው ይህን እየሠራሁ ያለሁት።
የተከታዮች ምላሽ፡
ተስፋ የሚያስቆርጡ በርካቶች ናቸው። አሁን በደንብ የገባኝ ነገር አንድ ሰው የኔን ፖስት ከወደደው ዐይቶት ዝም ይላል። ካልወደደው ግን ከጊዜው ቀንሶ አስተያየት መስጫው ላይ ድርሰት ነው የሚተውልኝ።
• 'መኝታ ቤት ስልክ ይዘን አንገባም' ፡ ሲቲና ኑሪ
• "የመሰለህን ተናግሮ ከመኖር በላይ ጸጋ የለም" ፡ ዳንኤል ብርሃነ
• 'ደራሲ ያደረገኝ ማኅበራዊ ሚዲያው ነው'፡ ሕይወት እምሻው
በውስጥ መስመር የሚመጡ መልዕክቶች፡ -
ሐሳብ የሚሰጡ ሰዎች አሉ። በዚህ ጉዳይ ላይ በርካቶች እያደሩ ሲሄዱ ግን ወደድኩሽ ይላሉ። ዝም ስላቸው ሜሴንጀሬን የስድብ ሜኑ ያደርጉታል።
የምታደንቂው ፌስቡከር፡
ቪዲዮቻቸውን መመልከት ከሚያስደስተኝ ፌስቡከሮች መከካል ሚኪ ዓለም አንዱ ነው። ስታይሉ ለየት ያለ ስለሆነ ያስደስተኛል።

የፎቶው ባለመብት, Marlita Temesgen
ከፌስቡክ ጡረታ የምትወጪው መቼ ነው?
አሁን ፌስቡክ ላይ የምሠራው ሥራ ምንም ዓይነት የገንዘብ ጥቅም አያስገኝልኝም። ሰዎችን ለማስደስት ብቻ ብዬ የምሠራው ሥራ ነው። ወደ ፊት ይህንኑ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን ማዘጋጀት እሻለሁ።
የ70 ዓመት ሴት ሆንሽ ብለን እናስብ። ያኔ ምን 'ፖስት' ልታደርጊ ትችያለሽ?
በአሁን ጊዜ በ70 እና 17 ዓመት ሴት መካከል ልዩነት አለ ብለህ ነው? እኔ በ70 ዓመቴም እንደ የ70 ዓመት አዛውንት የማስብ አይመስለኝም። አሁን የማደርጋቸውን ነገሮች የማደርግ ነው የሚመስለኝ። በዛ ዕድሜዬም ከልጅ ልጆቼ ጋር ኮሜዲ መሥራቴ አይቀርም።
በብዛት የተወደደልሽ፡-
በብዛት የታየው የድምጽ መልዕክትን በማስመልከት የሠራሁት ቪዲዮ ነው። የሚገርመው ይህን ቪዲዮ ስሠራው ያን ያህል አስቂኝ ይሆናል ብዬ አላሰብኩም። ግን በብዛት የታየው ቪዲዮ እሱኛው ነው።
ማኅበራዊ ሚዲያ በመጠቀምሽ አጣሁት የምትይው ነገር አለ?
አጣሁት የምለው ነገር የለም። ይሁን እንጂ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መቆየት ከባድ ነው። አብሮኝ የጀመረው ወጣት ከሰዎች ይሰጠን በነበረው አዎንታዊ ባልሆኑ አስተያየቶች ጫና ነው ሥራውን ያቋረጠው። ይህን መሰል አስተያየቶች ተቋቁሞ መቆየት ከባድ ነው። ብዙ ሰዎች ሁለት ወይም ሦስት ቪዲዮ ይሠሩና ይጠፋሉ። እኔ ግን ይህን ሁሉ ተቋቁሜ መቆየት መቻሌ በራስ የመተማመን አቅሜን አጎልብቶታል።












