'መኝታ ቤት ስልክ ይዘን አንገባም'

የመጀመርያው 'ትዊት'
...እውነት ለመናገር ምን እንደማስታውስ አላውቅም፤ .... እንደው ሊሆን የሚችለው ግን በአገር ቤት ስላለው የፖለቲካ ሁኔታ ይመስለኛል።
በከፍተኛ ቁጥር የተወደደው 'ትዊት'
እ...(ረጅም ፋታ) ተከታዮቼ ብዙ ጊዜ የፖለቲካ ጉዳዮችን ስጽፍ ይወዱታልም፣ ይጋሩታልም። ስንት ሰው ወደደው ብዬ ግን አልቆጥርም። እንደው በደፈናው ብዙ ውዴታን የሚያገኙት ፖለቲካዊ ጉዳዮች ናቸው ብል ይቀለኛል።
በዝቅተኛ ደረጃ የተወደደ
(ሳቅ) ብዙ ሊሆን ይችላል። በደፈናው ሳይንስ፣ ሃይማኖታዊና፣ዓለም አቀፋዊ የሆኑ ጉዳዮችና ግኝቶች አንዲሁም ፍልስፍና ላይ የምጽፋቸው ነገሮች ብዙ ትኩረት አያገኙም። ምንአልባት ተከታዮቼ ያን ስለማይወዱ ሊሆን ይችላል።
አስቂኙ አስተያየት
እ... ብዙ ጊዜ የሚያስቁ ነገሮችን እጽፋለሁ። ከሰዎች ጋር በርካታ ሐሳቦችን እለዋወጣለሁ። ይቅርታ አሁን ይሄ ብዬ የማስታውሰው የለም።
ወደው የሚከተሉት
አሁን በጣም ወድጀው የምከተለው አካውንት የሪቻርድ ዶውኪንስን ነው። አንዳንዶች 'ወዴት እንደምሄድ አታውቁምና አትከተሉኝ!' ቢሉም ደስ የሚል ሳገኝ ከመከተል ወደ ኋላ አልልም።
አወዛጋቢው 'ትዊት'
በቅርብ ጊዜ ከማስታውሰው የጣይቱ ሐውልት ለመገንባት ከተጣለው የመሠረት ድንጋይ ጋር በተያያዘ የለጠፍኩት ጽሑፍ ላይ ሰዎች ሲወዛገቡበት ነበር ። እኔ የርሳቸው አድናቂ ነኝና መገንባቱን ደግፌ ነበር የጻፍኩት።

የፎቶው ባለመብት, SITNA NURI
ያልተጠበቀ የውስጥ መስመር መልዕክት
እ... አሁን አሁን ላይ ደርሰውኝ አያውቁም፤ ምን አልባት በፊት ያላገባሁ መሆኔን የሚያውቁ ሰዎች የፍቅር ጥያቄ በሥውር ይልኩልኝ ነበር። ግን የትዊተር ሥሪቱ በራሱ ይህንን ለማድረግ አይፈቅድም። ሙገሳም፣ አንዳንዴ ስድብ ይደርሰኛል፤ ማስፈራሪያ ግን ደርሶኝ አያውቅም።
ትዊተር ሳያዩ የቆዩበት ረዥሙ ጊዜ
ወልጄ የነበረበት ጊዜ ነው፤ወደ ስድስት ወር ገደማ ይሆናል። ጀማሪ እናትም ስለነበርኩ ሙሉ ጊዜዬን ለልጄ መስጠት ስላለብኝ ነበር የጠፋሁት።
ከማኅበራዊ ሚዲያው ያገኙት ትርፍ
ማኅበራዊ ሚዲያ ድምጽ ለሌላቸው ሰዎች ድምፅ ማሰሚያ መድረክ ነው። በተለይ አንደኛ አገር ነጻ ሚዲያ መሬት ላይ በሌለበት ሁኔታ ማኅበረሰቡን እያገለገለ ያለ መሣሪያ ብዬ አስበዋለሁ።
ከትዊተር ጡረታ የሚወጡበት ዘመን
እኔ እንጃ እንግድህ ...በሕይወታችን የሚያጋጥሙን ነገሮች ያልተጻፉና ያልታቀዱ ነገሮች ናቸው። ሕይወቴ ላይ ምን እንደሚያጋጥመኝ አላውቅም። ለእኔ አንደ ሐሳብ መድረክ ስለምቆጥረው መቼ አንደምሰናበት አላውቅም፤ ለመሰናበትም ጊዜው ገና ነው።
በ70ዓመትዎ 'ትዊት' ሊያደርጉት የሚችሉት
እ... በ70 ዓመቴ? ( ሳቅ) ምኞቴ... ለኦቲዝም መድኃኒት ቢገኝለትና 'ተገኘ' ብዬ ትዊት ባደርግ ደስ ይለኛል።
ትዊት የሚያደርጉበት ፍጥነት
እንደ ሁኔታው ይወሰናል... በቀን አንዴ ወይ ሁለቴ ልጽፍ እችላለሁ። በአማካይ በቀን አራት ጊዜ 'ትዊት' አደርጋለሁ።
ባልተጠበቁ ቦታዎች ትዊት
እኛ ቤት ማታ መኝታ ቤት ከገባን በኋላ ስልክ ይዘን ስለማንገባ ሌሊት ላይ 'ትዊት' አድርጌ አላውቅም። ማኅበራዊ ሚዲያም አንከፍትም።ለቅሶ ላይ ግን የሆነ ሐሳብ ብልጭ ሲልልኝ ልለጥፍ እችላለሁ። አንድ ጊዜ የእኛ አገር የለቅሶ ሥርዓት ቀለል ያለ ቢሆን ብዬ ጽፌያለሁ። ሴቶች ላይ የሚያሳርፈው ጫና አሳስቦኝ ነው የጻፍኩት።












