ኔትፍሊክስ የይለፍ ቃል መዋዋስን ለመግታት አዲስ ዘዴ ቀይሻለሁ አለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የተለያዩ ፊልሞችን በበይነ መረብ በማሳየት ዝናን የተጎናፀፈው ኔትፍሊክስ ከሰሞኑ የይለፍ ቃል የሚዋዋሱ ደንበኞችን የሚቆጣጠርበትን መንገድ እንደዘየደ አስታውቋል።
አንዳንድ ደንበኞች በቴሌቪዥን ወይም በሌሎች የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ወደ ኔትፍሊክስ ድረ ገፅ ሲያመሩ "አሁን እየተጠቀማችሁ ካላችሁበት አካውንት ባለቤት ጋር በአንድ ቤት ውስጥ የማትኖሩ ከሆነ የራሳችሁ አካውንት አውጥታችሁ ፊልሞቹን መመልከት ትችላላችሁ" የሚሉ መልዕክቶችን አግኝተዋል።
የኔትፍሊክስ ቃለ አቀባይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት " ይሄ ሙከራ ዲዛይን የተደረገው የኔትፍሊክስ አካውንት ያላቸው ደንበኞች ብቻ የሚጠቀሙበትን መንገድ ለመቀየስ ነው" ብለዋል።
በዚህ ሙከራ ወቅትም የኔትፍሊክስ አካውንታቸውን የራሳቸው መሆኑን ለማረጋገጥ ሌላ የይለፍ ቃል በስልክ መልዕክት ወይም በኢሜይል ይላክላቸዋል።
ኔትፍሊክስ እንደሚለው ይህንን መመሪያ ለማውጣት ያስገደደው በርካታ ደንበኞች የይለፍ ቃላቸውን በአንድ ቤት ውስጥ ለማይኖሩ ላልከፈሉ ደንበኞች በማዋሳቸው መሆኑንም አስታውቋል።
ኔትፍሊክስን ጨምሮ በበይነ መረብ ፊልም የሚያሳዩ ኤችቢኦ ጎ፣ አማዞን ፕራይምና ዲዝኒ በተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች በርካታ አካውንቶችን መክፈት የሚያስችል ሁኔታ ቢኖራቸውም ይህ ግን በአንድ መኖሪያ ቤት ውስጥ ብቻ ነው መጠቀም የሚቻለው።
ከዚህ ቀደም የኔትፍሊክስ አንደኛው መስራችና ዋና ስራ አስፈፃሚ ሪድ ሃስቲንግ ከዚህ በተቃራኒው "የይለፍ ቃሎችን መዋዋስን ልንታገሰው የሚገባ ጉዳይ ነው። በርካቶች የይለፍ ቃሎችን በመዋዋስ እንደሚያዩ እናውቃለን። ሆኖም በጥሩ ሁኔታ እየሰራን ነው" ብለው ነበር።
ዋና ስራ አስፈፃሚው ይህንን ያሉት በአውሮፓውያኑ 2016 ሲሆን ከሶስት አመት በኋላ የኩባንያው የምርቶች ኃላፊ ግሬግ ፒተርስ ኔትፍሊክስ የይለፍ ቃል መዋዋስ ጉዳይን እንደገና እያጤነው ነው ብለው ነበር።
በወቅቱም " እስካሁን ባለው ድረስ ከምንሰራበት አሰራር ውጭ ሌላ መመሪያ የማስተዋወቅ እቅድ የለንም" ብለው ነበር።
በአውሮፓውያኑ ያለፈው አመት ኔትፍሊክስ አዲስ 37 ሚሊዮን ደንበኞችን የመዘገበ ሲሆን በአጠቃላይ በአለም ደረጃ 200 ሚሊዮን ደንበኞች አሉት።
በተለይም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ የወጡ የቤት መቆየት መመሪያዎች ምርቃት የሆነለት ኔትፍሊክስ ትርፉ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል ተብሏል። ኔት ፍሊክስ 25 ቢሊዮን ዶላር አስገብቻለሁ ያለ ሲሆን ከዚህም ውስጥ 2.8 ቢሊዮን ዶላር ማትረፉን አስታውቋል።












