አሜሪካ ከእስር ቤት በስህተት የተለቀቀውን የግድያ ወንጀል ተጠርጣሪ እያደነች ነው

የራይከርስ አይላንድ ማረሚያ ቤት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የአሜሪካ ፓሊሶች ከኒውዮርክ እስር ቤት በድንገት በስህተት የተለቀቀውን ታራሚ እያደኑ መሆኑ ተነግሯል።

ግለሰቡ በግድያ ወንጀል ተጠርጥሮ በእስር ላይ ይገኝ የነበረ ሲሆን በስህተት የተለቀቀውም በያዝነው ሳምንት ሰኞ ነው።

የ26 አመቱ ክርስቶፈር በግስ በአውሮፓውያኑ 2018 በሽጉጥ ሰው ገድሏል በሚል ነው ለእስር የተዳረገው።

ለሶስት አመታት ያህል በራይከርስ አይላንድ እስር ቤትም ቆይቷል።

ከሰሞኑ ግን በማረሚያ ቤት ሰራተኞች ዘንድ በተሰራ ስህተት በነፃ ወጥቷል።

በአሁኑ ወቅት ጥምር ግብረ ኃይል ተዋቅሮ ታራሚውን በቁጥጥር ስር ለማዋል እየተሞከረ ነው።

ባለስልጣናቱ የታራሚውን ግለሰብ ፎቶ በየቦታው ከመበተን በተጨማሪ የአካባቢው ማህበረሰብ እንዳይቀርበው ማስጠንቀቂያ ተላልፏል።

"ክስተቱ እንደተፈጠረ ተረድተናል። በምን መንገድ ግለሰቡ ሊለቀቅ ቻለ የሚለው ላይ ምርመራ ከፍተናል" በማለት የማረሚያ ቤቶች የህዝብ ግንኙነት ምክትል ኮሚሽነር ፒተር ቶርን መናገራቸውን ሲቢኤስ መግለጫቸውን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

የኒውዮርክ ከተማ ከንቲባ ቢል ደ ብላሲዮ በበኩላቸው ስህተቱ የተፈፀመው ግለሰቡ ተደራራቢ ክሶች መኖሩ በመዘንጋቱ ነው ብለዋል።

በአንደኛው ክስ የተመሰረተበት ብያኔ ሰላሳ ቀናት ሲሆን ነገር ግን የግድያ ወንጀሉ የፍርድ ሂደቱ አልተጠናቀቀም። ይህንን ያላወቀቱት የማረሚያ ቤት ሰራተኞች በነፃ አሰናብተውታል በማለት ከንቲባው ማብራሪያ ሰጥተዋል።

"ከዚህ በኋላ እንዲህ አይነት ድጋሜ ስህተት እንዳይፈጠር ጠንካራ ቁጥጥሮችንና መመሪያዎችን እናወጣለን። የተፈጠረው ክስተት የሚያበሳጭ" ነው በማለት ከንቲና ቢል ደ ብላሲዮ በያዝነው ሳምንት ረቡዕ ተናግረዋል።

ባለስልጣናቱ ታራሚውን በአጭር ወቅት በቁጥጥር ስር እንደሚያውሉት በሙሉ መተማመን ላይ ናቸው በማለት ከንቲባው አክለው ተናግረዋል።

ክርስቶፈር በግስ በአውሮፓውያኑ 2016 በብሩክሊን፣ ኒውዮርክ አንድ ግለሰብን በሽጉጥ ገድሏል በሚል ወንጀል ነው በእስር ላይ ያለው።