ኮሮናቫይረስ፡ የአውሮፓ ሕብረት አስትራዜኔካ የተሰኘው ክትባት የደም መርጋት አያመጣም እያለ ነው

የአስትራዜንካ ክትባት

የፎቶው ባለመብት, EPA

ኮቪድ-19 እንዲከላከል ተብሎ የተሠራው የኦክስፎርድ-አስትራዜኔካ ክትባት የደም መርጋት አደጋን ይጨምራል የተባለው ሃሰት ነው ሲል የአውሮፓ ሕብረት አስታወቀ።

መግለጫውን ያወጣው የአውሮፓ ሕብረት የመድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ነው።

ባለሥልጣኑ እንደሚለው የደም መርጋት የታየባቸው የተከተቡ ሰዎች ቁጥር ካልተከተቡ ሰዎች ቁጥር ጋር ተመሳሳይ ነው።

የአውሮፓ ሕብረት ይህን ማለት ያሻው ዴንማርክና ኖርዌይን ጨምሮ አንዳንድ ሃገራት ክትባቱን ለዜጎቻቸው መስጠት ማቆማቸውን ተከትሎ ነው።

ሃገራቱ ክትባቱን መስጠት ያቆሙት ጥቂት ሰዎች ከተከተቡ በኋላ የደም መርጋት ምልክት አሳይተዋል ተብሎ ነው።

አንድ የ50 ዓመት ጣልያናዊ ክትባቱን ከወሰደ በኋላ 'ዲፕ ቬይን ትሮሞቦሲስ' [ከደም መርጋት ጋር ተያያዥነት ያለው] የተሰኘ በሽታ ታይቶበት ሞቷልም ተብሏል።

"በአሁኑ ወቅት ክትባቱና የደም መርጋት ግንኙነት እንዳላቸው የሚያሳይ ነገር የለም። የደም መርጋትም የክትባቱ ጎንዮሽ ጉዳት አይደለም" ብሏል የአውሮፓ መድኃኒት ኤጀንሲ።

"ክትባቱ ከጉዳቱ ጥቅሙ ያመዝናል። ስለዚህ ታዩ የተባሉትን ጉዳቶች እየመረመርን ክትባቱን መስጠት እንቀጥላለን" ብሏል ኤጀንሲው።

ኤጀንሲው እንደሚለው አውሮፓ ውስጥ ክትባቱን ከወሰዱ አምስት ሚሊዮን ሰዎች መካከል 30 ሰዎች የደም መርጋት ምልክት ታይቶባቸዋል።

አስትራዜኔካ በቃል አቀባዩ አማካይነት የክትባቱ ደህንነት በብዙ ምርምርና ፈተና የተረጋገጠ ነው ብሏል።

በዩናይትድ ኪንግደም የመድኃኒት ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን ክትባቱን ከደም መርጋት ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚያሳይ ምንም መረጃ የለም ብሏል።

ስለዚህ ሰዎች በተጠየቁ ጊዜ ሄደው ክትባቱን እንዲወስዱ እንመክራለን ይላል።

"የደም መርጋት ክትባት ባይኖርም የሚከሰት ነገር ነው። አዲስ ነገር አይደለም። እስካሁን ድረስ 11 ሚሊዮን የአስትራዜኔካ ክትባቶች ዩኬ ውስጥ ተሰጥተዋል" ይላሉ የባለሥልጣኑ ሠራተኛ የሆኑት ፊል ብራያን።

በክትባት መዘግየት ምክንያት ችግር ላይ የነበረው የአውሮፓ ሕብረት አሁን ደግሞ አስትራዜኔካ ክትባትን በተመለከተ የሚሰራጩ ያልተረጋገጡ ዜናዎች ማነቆ ሆነውበታል።

የአውሮፓ ሕብረት አሁን ፊቱን ወደ ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ወደተሰኘውና አንድ ጊዜ ብቻ ወደሚሰጠው ክትባት ማዞር የፈለገ ይመስላል።

"ደህንነታቸው ይበልጥ አስተማማኝ የሆኑ ክትባቶች ወደ ገበያው እየመጡ ነው" ብለዋል የአውሮፓ ሕብረት ኮሚሽን ፕሬዝደንት ኧርስላ ቮን ደር ለየን።

ከዚህ አልፎ ኖቫክስ የተሰኘው ክትባት ዋናውን የኮቪድ ዝርያ በመከላከል ረገድ 96 በመቶ አዲሱን ዝርያ ደግሞ 86 በመቶ ውጤታማነት ማሳየቱ ተነግሯል።

ዴንማርክና ናሮዌይ የአስትራዜኔካን ክትባት መስጠት ሙሉ በመሉ ሲያቆሙ ኦስትሪያና ጣሊያን ደግሞ አንዳንድ ብልቃጦችን ማስወገድ ይዘዋል።

ኢስቶኒያ፣ ላትቪያ፣ ሊቱኔያ እንደ ላግዘምበርግ ልክ እንደ ኦስትሪያ ለጊዜው የተወሰኑ የአስትራዜኔካ ክትባቶችን መስጠት አቁመዋል።