የሶማሊያዊቷ ሰላይ መጥፋት ፕሬዝዳንቱንና በጠቅላይ ሚኒስትሩን አፋጧል

ፕሬዝደንት ፎርማጆ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝደንት ፎርማጆ

በሶማሊያ ፕሬዝደንት ሞሐመድ አብዱላሂ ፋርማጆ እና በአገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ሞሐመድ ሁሴን ሮብሌ መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ተከትሎ ፕሬዝደንቱ የጠቅላይ ሚንስትሩን ስልጣን ማገዳቸውን አስታወቁ።

ፕሬዝደንቱ ፋርማጆ ጠቅላይ ሚንስትር ሮብሌ፤ "ፖለቲካዊ እና የደኅንነት ቀውስ ሊያስከትል የሚችል ጥንቃቄ የጎደላቸው እርምጃዎችን ወስደዋል" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ በበኩላቸው የፕሬዝደንቱ ውሳኔ ሕገ-መንግሥታዊ አይደለም በማለት ውሳኔውን እንደማያከብሩ አስታውቀዋል።

በሶማሊያ ሕግ መሠረት ፕሬዝደንቱ ከጠቅላይ ሚንስትሩ የበለጠ ከፍተኛውን የመንግሥት ስልጣን ይይዛሉ።

በፕሬዝደንቱ እና በጠቅላይ ሚንስትሩ መካከል የነበረው አለመግባባት የተካረረው የአገሪቱ የስለላ ተቋም ሠራተኛ የነበረችው ሴት ሰላይ ምስጢራዊ በሆነ ሁኔታ ከጠፋች በኋላ ነው።

የ25 ዓመቷ ኢክራን ታህሊል ለመጨረሻ ጊዜ የታየችው ሰኔ ወር አጋማሽ ላይ ከመኖሪያ ቤቷ በመንግሥት መኪና ስትወጣ ነበር።

መንግሥት ታህሊል በአል-ሸባብ ታፍና ከተወሰደች በኋላ ተገድላለች ይላል። አል-ሸባብ በበኩሉ በወጣቷ ሰላይ ግድያ እጄ የለበትም ይላል።

ከአል-ቃይዳ ጋር ግንኙነት ያለው አል-ሸባብ በርካታ የሶማሊያን ገጠራማ አካባቢዎችን ተቆጣጥሮ የሚገኝ ሲሆን ተደጋጋሚ ጥቃቶችንም በመንግሥት መዋቅር ላይ ሲሰነዝር ቆይቷል።

የ25 ዓመቷ አከራን ታህሊል

የፎቶው ባለመብት, .

የምስሉ መግለጫ, የ25 ዓመቷ አከራን ታህሊል

የሰላይዋ መጥፋትን ተከትሎ ጠቅላይ ሚንስትር ሮብሌ የደኅንነት ኤጀንሲ ኃላፊ የሆኑትን ፋያድ ያሲንን ከሥራ አግደው ነበር።

ጠቅላይ ሚንስትሩ የደኅንነት ኃላፊውን ከሥራ ያገዱት ታህሊል ስለመጥፋቷ እና ስላጋጠማት ነገር በ48 ሰዓታት ውስጥ ሪፖርት አላደረጉም በሚል ምክንያት ነው።

ይሁን እንጂ ፕሬዝደንት ፋርማጆ ጣልቃ በመግባት የደኅንንት ኃላፊውን መልሰው ሹመዋል። ፋርማጆ ጠቅላይ ሚንስትሩ የደኅንነት ኃላፊውን የማባረር ስልጣን የለውም ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚንስትሩ የደኅንነት ሚንስትሩን ከስልጣን የማንሳት ውሳኔን ፕሬዝደንቱ ሽረዋል።

ፕሬዝደንት ፋርማጆ የወጣቷን ሰላይ መጥፋት በተመለከተ የሚያጣራ ኮሚሽን አቋቁመዋል። ይሁን እንጂ ይህ በወጣቷ ቤተሰቦች ዘንድ ተቀባይነትን አላገኘም።

የታህሊል እናት ቃሊ ሞሐሙድ በኮሚሽኑ ምርመራ ላይ እምነት እንደሌላቸው እና ጉዳዩ በወታደራዊ ፍርድ ቤት እንዲጣራ ፍላጎታቸው መሆኑን ተናግረዋል።

የፕሬዝደንቱ ጽ/ቤት ትናንት ባወጣው መግለጫ እስከቀጣዩ የሶማሊያ ምርጫ ድረስ የጠቅላይ ሚንስትሩ ስልጣን በተለይም ደግሞ የሹምር ሽር ኃላፊነት ተገፏል ይላል።

ሶማሊያ ከመስከረም መጨረሻ እስከ ኅዳር አጋማሽ መካከል ምርጫ ለማከናወን እቅድ ይዛለች።

የፕሬዝደንቱ ጽ/ቤት መግለጫን ተከትሎ ጠቅላይ ሚንስትር ሮብሌ፤ የፕሬዝደንቱ ውሳኔ "ሕጋዊ አይደለም" በሚል ለውሳኔው ተገዢ እንደማይሆኑ አስታውቀዋል።

የፕሬዝዳንቱን እርምጃ ተከትሎ ሮብሌ ባወጡት በመግለጫ፤ "ጠቅላይ ሚንስትሩ በመንግሥት ተቋማት ውስጥ የስልጣን ክፍፍል ሕገ-መንግሥታዊ መርሆችን እንዲጠብቅ ፕሬዝደንቱን ያስታውሳል" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ሞሐመድ ሁሴን ሮብሌ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚንስትር ሞሐመድ ሁሴን ሮብሌ

ከቀናት በፊት የተባበሩት መንግሥት ምክትል ዋና ጸሐፊ ናይጄሪያዊቷ አሚና ሞሐመድ ፕሬዝደንቱን እና ጠቅላይ ሚንስትሩን አነጋግረው ነበር።

አሚና ሁለቱ መሪዎች ግጭት አልያም ቀጣዩ ምርጫ ላይ አሉታዊ ውጤትን ሊያስከትል ከሚችል ተግባር እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።

ፕሬዝደንቱን እና ጠቅላይ ሚንስትሩ ምርጫን በማራዘም ጉዳይ ከዚህ ቀደምም ሲወዛገቡ ነበር። ፕሬዝደንቱ ስልጣን ዘመናቸውን በማራዘም ምርጫ የሚካሄድበትን ጊዜ በወራት ወደፊት ገፍተው ነበር።

የፋርማጆ የስልጣን ጊዜ ባለፈው ዓመት የካቲት 2013 ላይ አብቅቷል።

line

የቢቢሲ ሶማሊኛ አርታኢ ሙሄዲን ሮብሌ በሁለቱ መሪዎች መካከል የተፈጠረው ውዝግብ እጅጉን ተካሯል ይላል።

የአገሪቱ የደኅንነት ኃላፊዎች ለሁለት ተከፍለዋል ይላል። ብሔራዊ የመረጃ እና ደኅንነት ኤጀንሲው በፕሬዝደንቱ እና በጠቅላይ ሚንስትሩ የተሾሙ ሁለት መሪዎች አሉት።

ምንጮች እንደሚሉት ከሆነ በፕሬዝደንቱ የተሾሙት ኃላፊ የኤጀንሲውን ዋና መሥሪያ ቤት እየመሩ ይገኛል።

በጠቅላይ ሚንስትሩ የተሾሙት ደግሞ የኤጀንሲውን ፋይናንስ በመያዝ ከዋና መሥሪያ ቤት ውጪ ያሉትን እንቅስቃሴዎች ይቆጣጠራሉ።

ሮብሌ እንደሚለው ክፍፍሉ አስከ ሶማሊያ ጦር እና ፖሊስ ኃላፊዎች ድረስ ይወርዳል።

በደኅንነት ተቋማት መካከል የተከሰተው ውጥረት አገሪቱን ዳግም ወደ ግጭት እንዳይወስዳት ስጋትን ፈጥሯል።

በዚህ ውጥረት መካከል ጽንፈኛው ቡድን አል-ሸባብ አጋጣሚውን በመጠቀም ጥቃቶችን ሊሰነዝር ይችላል የሚል ስጋት በሶማሊያ ሰፍኗል።