ለቀኝ አክራሪ ናዚዎች ሲሉ በጀመሩት ጁዶ ስድስተኛ ዳን የደረሱት ኢትዮጵያዊው ዶክተር

ፀጋዬ ደግነህ (ዶ/ር) ወደ ጀርመን ያቀኑት ለትምህርት ነበር።
አውሮፓ ከከተሙ ከሦስት አስር ዓመታት በላይ ሆናቸው።
ጀርመን የደረሱት ትኩረታቸውን ትምህርት ላይ አድርገው ነበር።
ቆይተው ደግሞ ዋና መማር ፈለጉ።
ለመመዝገብ ሲሄዱ ግን ቀልባቸውን የገዛ ሌላ ነገር ተመለከቱ። ጁዶና ጁቲትሱ።
ስፖርቱ ወዲያው ነበር ውስጣቸው ያደረው።
ፍቅር ያደረባቸው ስፖርቱ ራስን መከላከልን እና የምት ቴክኒክን በመያዙ ብቻ አልነበረም።
"ጎረምሶች እያለን ቀኝ ዘመም አክራሪ ናዚዎች ያባርሩን ነበር። ራስን ለመከላከል ብዬ ገባሁ" ይላሉ ወደ ስፖርቱ የሳባቸውን ሌላ ምክንያት ሲያስረዱ።
አሁን ለደረሱበት ደረጃ ስለመድረሳቸው ግን አስበውትም አልመውትም አያውቁም።
በተለይ ስፖርቱን እንደጀመሩ 'የጀርመኖቹ ጠንካራ መሆን ጥለህ ውጣ ጥለህ ውጣ' አሰኝቷቸው ነበር።
"ጀርመኖቹ ከልጅነታቸው ጀምሮ [ጁዶ] ሲሠሩ ስለኖሩ ከእኔ የበለጠ ጥንካሬ ነበራቸው። ያስደነገጠኝም እሱ ነበር" ሲሉ ያስታውሳሉ።
ፀጋዬ ኢትዮጵያ እያሉ ከአባታቸው የመንግሥቱ ለማ 'የካራቴ ሚስጥር' የምትል መጽሐፍ፣ ተበርክቶላቸው ነበር። ።
መጽሐፉን እያነበቡ ከጓደኞቻቸው ጋር ካራቴ ለመሥራት ሞክረው ነበር።
መጽሐፍ እያነበቡ መሥራቱ ከባድ ቢሆንም ስፖርቱ ለነፍሳቸው ይበልጥ ቀረበ።
ከስፖርቱ መለየትም ከባድ ሆነባቸው።

"ለኢትዮጵያ መወዳደር እመኝ ነበር"
"ጁዶ ለእኔ 'ሆቢ' ከመደበኛ ሰዓት ውጭ ለመዝናኛ ሲባል የሚተገበር እንደማለት ነው" ይላሉ።
"ስፖርቱ ትልቅ ሥነ ምግባር ያስተምራል" ይላሉ ፀጋዬ "ትህትና፣ ድፍረት፣ ልበ ሙሉነት፣ ታማኝነት፣ ቁም ነገረኛነት ያስተምራል" ሲሉ ያክላሉ።
ስፖርቱ የማጥቃት ሳይሆን የመከላከል ነው የሚሉት ፀጋዬ ራስን ለመቆጣጠር እና ለማግኘት እንደሚያግዝም ያምናሉ።
"የጀርመን ህይወት መጀመሪያ ላይ ጠጣር ነው። ጠጣሩን መንገድ ለማሸነፍ [ጁዶ] የአዕምሮ ብርታት ይሰጣል። አካል ግንባታ፣ ጤንነት እና ማህበራዊ ትስስርን ያሳድጋል" ይላሉ ጊዜውን አስታውሰው ሲናገሩ።
"ዕድሜዬ በ20ዎች እና 30ዎቹ መጀመሪያ እያለ ለኢትዮጵያ መወዳደር እመኝ ነበር" ሲሉ የነበራቸውን ፍላጎት ያስታውሳሉ።
የኢትዮጵያ ፓስፖርት ይዘው ለጀርመን መወዳደር አይችሉም።
እንደ ውጭ ዜጋ ግን በክለብ ደረጃ ተወዳድረዋል።
እና አሸነፉ?
"ማሸነፍም መሸነፍም አለ። ከጀርመኖች ጋር መጋጠም ከባድ ነው። እዚህ ስመጣ በጣም ቀጭን ነበርኩ። የዩኒቨርሲቲ ትምህርት እየተከታተልኩ ነበር ስፖርት የምሰራው። ጡንቻ አዳብረህ፣ ኃይል፣ አቋም፣ ትንፋሽ ይዘህ ነው መወዳደር ያለብህ። መጀመሪያ ወጣት እያለሁ የመወዳደርም ግዴታ አለ። በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ግን አልችልም። ቢሆንም ያሸነፍኩባቸውም የተሸነፍኩባቸውም ግጥሚያዎች ነበሩ" ብለዋል።
ትምህርት ከዚያም፣ ሥራ ቀጥሎ ደግሞ ትዳር በኋላም ልጆች መጡ። ጁዶው አሁንም አልተቋረጠም።
"መሰበር፣ መታመም ሊኖር ይችላል። ይህ ግን የሚያስቆም አይደለም። ለ21 ዓመታት በሳምንት አንድ ቀን በዩኒቨርሲቲ [ስለጁዶ] አስተምራለሁ። ያንን እቀጥላለሁ" ብለዋል።
በጀርመን ብሔራዊ ፌደሬሽን ፈታኝ በመሆን ያገለግላሉ። ስፖርተኞችን እና ፖሊሶችን በየጊዜው ይፈትናሉ።
ህጻናትን ሰብስበው ጁዶ ያስተምራሉ። አጋጣሚው የኢትዮጵያን ሙዚቃ እና ቋንቋን አልፎ አልፎ ለማስተማር በር ከፍቶላቸዋል።
በሙዚቃ ስፖርት ከማሠራት በተጨማሪ በየመሃሉ የተወሰኑ ቃላትን ይወረውሩላቸዋል።
"በእረፍት ሰዓቴ ጭምር ለመሥራት እገደድ ነበር"
ጊዜው እየገፋ ፀጋዬ (ዶ/ር ) ጁዶ እየሠሩ በክብር ላይ ክብር እየደራረቡ ነው።
ፀጋዬ ስድስተኛ ዳን ጥቁር ቀበቶ ደርሰዋል።
ጁዶ በተለያዩ የቀበቶ ቀለሞች የሚሰጡ ደረጃዎች አሉት።
በነጭ ቀበቶ ይጀምራል። ቢጫ፣ አረንጓዴ፣ ቀይ እና ጥቁር እያለ ይቀጥላል። እነዚህን ቀበቶዎች ለማግኘት የተለያዩ ስልጠናዎችን ማጠናቀቅ ግድ ይላል።
ቀጥሎ ደግሞ በዲግሪ የሚገለጹ እና ዳን የሚባሉ ደረጃዎች አሉ።
ባለቀለም ቀበቶዎች በአሰልጣኝ የሚሰጡ ይሆናል።
የዳን ደረጃዎች ደግሞ ገለልተኛ በሆኑ ዳኞች ታይቶ በብሔራዊ የጁዶ ማኅበር የሚሰጡ ይሆናል። ደረጃው እውቅና እንዲሰጠውም በብሔራዊ የጁዶ ማኅበር መመዝገብ አለበት።
በጁዶ ዓለም ትልቁ ዳን፣ 10ኛ ዲግሪ ጥቁር ቀበቶ ሲሆን ፀጋዬ ስድስተኛ ደርሰዋል።
ስድስተኛና ከስድስተኛ ዳን በላይ ያላቸው ሰዎች ቁጥር አነስተኛ ነው።
ከመጀመሪያው ዳን እስከ ስድስተኛው ዳን ለመድረስ ዓመታት እንደሚጠይቅ የሚገልጹት ፀጋዬ "ለምሳሌ 4ኛውን ዳን ለማግኘት በብሔራዊ ማስ ስፖርት 120 ሰዓት ግልጋሎት መስጠት ያስፈልጋል። ይህን ለማሳካት በእረፍት ሰዓቴ ጭምር ለመጠቀም እገደድ ነበር" ይላሉ።
5ኛውን ዳን እአአ በ2014 ነበር ፈረንሳይ አገር ውስጥ ያገኙት።
ከሰባት ዓመት በኋላ ደግሞ 6ኛውን ዳን አገኙ።
"ስድስተኛው ዳን በፈተና የሚሰጥ አይደለም። ላደረከው ተሳትፎ፣ ስፖርቱን ለማስፋፋት እና ባስመዘገብከው ውጤት የሚሰጥ ነው። ልዩ ነገር ማድረግ አለብህ።"
"ትልቅም ክብር የሚሰጠው ነው። ክብርን የተጎናጸፈ የአመራር ደረጃም ጭምር ነው" ይላሉ ስለ አዲሱ ክብራቸው ሲገልጹ።
ከዚህ ቀጥሎ ያለውን ሰባተኛ ዳን ለማግኘት ዓመታትን መጠበቅ ግድ ይላል።
ቴዎዶር ሩዝቬልት፣ ዊሊያም ሄግ፣ ፒየር ቴሩዶ፣ ስቴቨን ሴጋል እና ቸክ ኖሪስ በቴኳንዶ እና ጁዶ ስፖርትን ከሚያዘወትሩ ታዋቂ ሰዎች መካከል ተጠቃሾች ናቸው።
ከፀጋዬ በላይ ዳን ካላቸው መካከል የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ይገኙበታል።
ፑቲን 8ኛ ዳን እንዳላቸው ሮይተርስ ዘግቦ ነበር። 8ኛ ዳናቸውን በ2012 ነበር ያገኙት። የዓለም አቀፉ ጁዶ ፌደሬሽን የክብር ፕሬዝዳንትም ናቸው።
ፀጋዬ ደግሞ በዓለም አቀፉ ፌደሬሽን ውስጥ የሥነ ምግባር ኮሚሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ።
ፀጋዬ በጀርመን ፕሬዚዳንት የሚሰጠውን ከፍተኛ የክብር ኒሻንም ተበርክቶላቸዋል።
በበርሊን የተረከቡትን ሽልማት ያገኙት ሕዝቦችን በማቀራርብ፣ የክህሎት ግንባታና በስፖርት ዘርፍ ለማኅበረሰቡ ባበረከቱት አስተዋጽኦ ነው።
ኒሻኑን በጀርመን የኢፌዴሪ አምባሳደር ሙሉ ሰለሞን በክብር እንግድነት በተገኙበት ነበር የተረከቡት።

"ዘመናዊ ጁቲትሱን በ2007 ወደ ኢትዮጵያ አመጣሁ"
ፀጋዬ ጁዶና ጁቲትሱን ወደ ኢትዮጵያ በማስገባት ቀዳሚ ሚና ነበራቸው።
"በስፖርት ደረጃ [ጁዶ] እንዲመጣ ያደረኩት እኔ ነኝ። ዘመናዊ ጁቲትሱን በ2007 ወደ ኢትዮጵያ አመጣሁ። ጁዶን ደግሞ ከአንድ ጀርመናዊ ጓደኛዬ ጋር በ2010 አመጣነው" ይላሉ።
ጁዶ ቀደም ሲልም ኢትዮጵያ ውስጥ ይዘወተር እንደነበር ግን አልሸሸጉም።
ይህንን የሚያስረዳ ማስረጃ ባይኖርም ስለመዘውተሩ መስማታቸውን አጫውተውናል።
"ከዓመታት በፊት ፈረንሳዊያን በምድር ባቡር እና በዙሪያቸው ለሚገኙ ሰዎች ስልጠና ይሰጡ ነበር ይባላል" ብለዋል።
"ግን ብዙም አልተሠራበትም" በማለት ወደ ስፖርቱ ለመግባት የሚፈልጉትን ከጀርመን ኢትዮጵያ ድረስ በመጓዝ አሰልጥነዋል። የጁዶና ጁቲትሱ ማኅበርም እንዲመሠረት አድርገዋል።
አዲስ አበባ፣ ድሬ ዳዋ እና ሐዋሳን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የስፖርቱ እንቅስቃሴ አለ።
"በአጠቃላይ በዕውቀት ሽግግር ላይ ነን" ሲሉ ይገልጻሉ።
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ማኅበርም የበላይ ጠባቂ ናቸው።
ለማኅበሩ ከስልጠና ጎን ለጎን ብዙ ድጋፎች በማድረግም ላይ ይገኛሉ።
ጁዶን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፕላስቲክ የነጻ ስፖርት ለማድረግ እየተሠራ ይገኛል። ፀጋዬ ለዚህም ደፋ ቀና ይላሉ።
ስፖርተኞችን በማስተባበር ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ ችግኝ ተከላ ላይ በተደጋጋሚ ተካፍለዋል።
"የጀርመን አቋም አሁን ከኢትዮጵያ ጋር እየሆነ ነው"
ፀጋዬ ከጁዶው እና ከመደበኛ ሥራቸው ጎን ለጎን በሕዝባዊ ዲፕሎማሲም እየሠሩም ነው።
የመጀመሪያው ትኩረታቸው ደግሞ አባይ እና የሕዳሴው ግድብ ነው።
ብዙ ጀርመናዊያን መጀመሪያ ላይ አባይ መነሻው ግብፅ ይመስላቸው ነበር ይላሉ።
ለዚህም ነው እነዚህ ሰዎች እንዴት ኢትዮጵያ ግድቡን ትገነባለች ብለው የሚጠይቁት።
ሌላው ደግሞ "ስለግብፅ ታሪክ ስለሚማሩ ቱሪስቶች ከኢትዮጵያ ይልቅ ግብፅን እንዲመርጡ አድርጓቸዋል" ይላሉ።
ይህንን ለመቀየር እነ ፀጋዬ የበኩላቸውን ጥረት እያደረጉ ነው።
"ግድቡ እነሱን [ግብፆች] ሳይጎዳ ለመጠቀም የሚገነባ እንደሆነ ለጀርመን ቻንስለር እና ወደ 60 ለሚጠጉ ሚዲያዎች እና ሚኒስትሮች ደብዳቤ ጽፈናል" ሲሉ ይገልጻሉ።
"የጀርመን አቋም አሁን ከኢትዮጵያ ጋር እየሆነ ነው። የአፍሪካ ሕብረትን አደራዳሪነት እንደሚቀበሉ ነግረውናል" ብለዋል።
ለግድቡ ቦንድ እንዲገዛ እና ብር እንዲዋጣም በማስተባበር ላይ ይገኛሉ።
ወደ ኢትዮጵያ ሲመላለስ ጁዶ ብቻ አይደለም ትኩረታቸው። ፕሮጀከት ማናጅመንት እና የሥራ ባህል ላይ ስልጠና ይሰጣሉ።
"በቅርቡ እንኳን ከ20 ሚኒስትር መስሪያ ቤቶች የተወጣጡ ዳይሬክተሮችን አሰልጥኛለሁ" ብለዋል።
የኢትዮጵያን ስፖርት ለማሳደግ የሚረዳ ጽሑፍም ለሚመለከታቸው አካላት ማስገባታቸውን ነግረውናል።
የስፖርቱ አደረጃጀት ላይ ትኩረት መሰጠት አለበት ይላሉ።
"ኢትዮጵያ ውስጥ አዲስ ስፖርት ማምጣት ይከብዳል። ሁሉም ነገር 'እንደ እግር ኳስ ይሁን' ይላሉ። ስፖርቱ ለባለሙያዎች መሰጠት አለበት።"
ከኢትዮጵያዊያን በተጨማሪ ትውልደ ኢትዮጵያውያንም መካተት እንዳለባቸው ያምናሉ።
"ዲያስፖራም ማሳተፍ አለብን። ጥምር ዜግነት ያላቸውም ቢሳተፉም ጥሩ ነው።"
"መርዳት ብቻ ሳይሆን መብትም ሊኖር ይገባል" ይላሉ።
"በቦክስ አፍንጫዬን ተሰብሬያለሁ"
ፀጋዬ ኑሯቸውን ጀርመን ካደረጉ ከሠላሳ ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል።
በኦልስቴት ኢንሹራንስ ኩባንያ ውስጥ የቢዝነስ ተንታኝነት የመጀመሪያ ልምዳቸውን አግኝተዋል።
ሃያ ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ በመርሴዲስ ቤንዝ ዳይምለር በተለያዩ ክፍሎች ያገለገሉ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በኩባንያው የጀርመን ገበያ ዘርፍ በሰው ኃይል የሕዝብ ግንኙነት እና የብዝሃነት ሥራ አስኪያጅ በመሆን እያገለገሉ ነው።
ፀጋዬ ባለትዳር እና ሁለት ሴት ልጆች አባት ናቸው።
ባለቤታቸው ጀርመናዊት ሲሆኑ ልጆቻቸው ሊያና ሳሮን ይባላሉ።
ሳሮን በተለያዩ ፊልሞች እና ቲያትሮች ላይ በመካፈል ወደ ኪነ ጥበቡ ገብታለች።
ፀጋዬ ከቢቢሲ ጋር የነበራቸው ቆይታ ከመጠናቀቁ በፊት ሁለት ጥያቄዎችን ወረወርንላቸው።
ቢቢሲ፡ ተደባድበው ያውቃሉ?
ፀጋዬ፡ [ሳቅ] ጁዶ ከመጀመሬ በፊት ናዚዎች ዲስኮ ስንሄድ ያሯሩጡን ነበር። ስፖርቱን ከጀመርኩ በኋላ አንዴ ዕቃ ለመግዛት ሄጄ ግርግር ነበር በቦታው። ቀኝ አክራሪዎች ነበሩ። ትከሻዬን ነኩት። ሰው ፈልጎኝ መስሎኝ ስዞር በቦክስ አፍንጫዬን ተሰብሬያለሁ። በኋላ ላይ ራሴን ጥሩ መከላከል ችያለሁ። አትቀደም [ሳቅ]። ረዥም ዓመት ቢሆነውም ጥሩ ልምድ ሆነኝ። አሁን እንዳልደባደብ ሆኜ ነው የምቀርበው። አታካራ ውስጥም አልገባም። ሌሎችንም ቢሆን በጣም አስጊ ከሆነ መንገድ ቀይሩ እላለሁ። በቃልም ሰዎችን መመለስ ይቻላል።
ቢቢሲ፡ ትምህርትዎን እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ድረስ ተከታትለዋል። የተለየ አስተያየት ደርስዎት ያውቃል?
ፀጋዬ፡ አንዴ ስለእኔ በአንድ ሚዲያ ፌስቡክ ላይ ተጽፎ አንድ ሰው 'የድብድብ ዶክተር ነው ወይ?' ብሎ አስተያየቱን ጻፈ። መቼም ወታደር ወታደር የሚሆነው ሰው ሊገድል ነው አይባልም።
በጁዶ መጀመሪያ ራስን መከላከል ነው የምትማረው። ማርሻል አርት ተምሮ ሰውን ማጥቃት ጀርመን ውስጥ ከባድ ቅጣት ያስከትላል። ከተደባደብክ ከሰውየው በላይ አቅምህን አለመጠቀመህን ማሳየት አለብህ። ካልሆነ [ቅጣቱ] ከባድ ነው።












