ፌቨን ፀሐዬ፡ ከኮረሪማ፣ ጥቁር አዝሙድና ኮሰረት ዘይት የምታመርተው ወጣት

ፌቨን ፀሐዬ

የፎቶው ባለመብት, Feven

ፌቨን ፀሐዬ ከኮሰረት፣ ከኮረሪማ፣ ከጥቁር አዝሙድና ኮሰረት መዓዛማ ዘይቶችን ታመርታለች።

ፌቨን በዩኒቨርስቲ ቆይታዋ ዓለም አቀፍ ልማት (International Development) ነው ያጠናችው።

ለረዥም ጊዜ በአነስተኛ እና ጥቃቅን ፋይናንስ ላይም ስትሠራ ቆይታለች።

አዲስ አበባ ተወልዳ ያደገችው ፌቨን፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን አጠናቅቃ ወደ አሜሪካ ከዚያም ደግሞ ወደ ቻይና በማቅናት ትምህርቷን በመከታተል ወደ ኢትዮጵያ ከአምስት ዓመት በፊት ነበር የተመለሰችው።

ፌቨን ቻይና እና አሜሪካ በነበረችበት ወቅት ከትምህርቷ ባሻገር በተለያዩ ሥራዎች ላይ በመሰማራት ልምድ ማካበቷን ትናገራለች።

በሥራዋ ሂደት ኢትዮጵያ ውስጥ በግብርና የተለያዩ ዘርፎች ለመሰማራት ለሚፈልጉ ባለሃብቶች ከገበያ ጥናት ጀምሮ ወደ ተለያዩ ቢሮዎች እየገቡ ጉዳይ እስከ ማስፈፀም መሥራቷን ለቢቢሲ ተናግራለች።

በዚህ ወቅት በግብርና ላይ የተሰማሩ ሰዎችን እንዲሁም ማሳዎቻቸውን ስትጎበኝ እርሷም የተሻለ አስተዋጽዖ የምታበረክትበት ዘርፍ እንደሚሆን ተሰማት።

ማኅበራዊ ተጽዕኖ የሚያሳርፍ፣ አስተዋጽዖውም ከፍ ያለ ኢንቨስትመንት ላይ በመሰማራት አርሶ አደሩ እንዲጠቀም ማድረግ ላይ ማተኮር መፈለጓን ትናገራለች።

አርሶ አደሮቹ ትላለች ፌቨን፣ በዘላቂነት ጥሬ ዕቃዎችን በመሸጥ የዕለት ኑሯቸውን መግፋትም ሆነ በቀጣይነት ማደግ እንደማይችሉ መረዳቷን ከቢቢሲ ጋር በነበራት ቆይታ ወቅት ገልፃለች።

"ከተፈጥሮ ያገኘነውን ለወጥ አድርገን፣ ቀይረን ወይም ደግሞ ጨመር አድርገንበት ለገበያ ማቅረቡ ብዙ የሥራና የእድገት ዕድሎች እንደሚከፍት ተረዳሁኝ።"

ታዲያ ፌቨን ከተለያዩ ባለሃብቶች ጋር ላይ ታች ስትል፣ እንዲሁም ወደ ተለያዩ የገበሬ ማሳዎች ሄዳ ያየችውን በአንድ ላይ በማጣመር 'ጫካ ኦሪጂንስ' የተሰኘውን ድርጅት መሰረተች።

የጫካ ኦሪጂንስ ጅማሬ

ፌቨን የተለያዩ መዓዛማ ዕፅዋትን በመጭመቅ ዘይት ማምረት ከመጀመሯ አራት ወራት በፊት የእፅዋቱን ኬሚካል ይዘት ማጥናት እንደነበረባቸው ታስረዳለች።

ይህም መደረግ የነበረበት "የእያንዳንዳቸውን ባህሪይ ማወቅ ስለነበረብን ነው" የምትለው ፌቨን፤ የሚፈልጓቸውን እፅዋቶች ከለዩ በኋላ ለኮስሜቲክስ በሚሆኑት ለመጀመር መወሰናቸውን ትናገራለች።

እንደ ፌቨን ገለፃ ከሆነ ተክሎቹን በመጭመቅ መዓዛማ ሽታን ለማምጣት የሚውሉ እንደ ሽቶ፣ ኮስሞቲክስ፣ መዋቢያ ቅባቶችና መድኃኒቶችን ለማምረት በግብዓትነት የሚውል መዓዛማ ዘይት ማምረት ይቻላል።

"ለፊት፣ ለፀጉር፣ ለገላ ቅባት ስለሚወጣቸውና ለፊት፣ ለፀጉር፣ ለገላ ሳሙና የሚሆኑ 'ፎርሙሌሽኖች' ላይ እንደ ግብዓት ሊውሉ በመቻላቸው ሰፋ ያሉ አምራቾችንና ሰዎችን ማዳረስ እንችላለን።"

ከዚያም ባለፈ ግን ዘይቱን በሚያወጡበት ወቅት በቆዳ ላይ ብቻ ሳይሆን በአፍም ቢወሰዱ ምንም ዓይነት ተያያዥ ጉዳት እንደማያስከትሉ አረጋግጠው እንደሚያመርቱ ታስረዳለች።

በመሆኑም የመዓዛማ ዘይቶቹን የጤና በረከት የሚፈልጉ በምግባቸው ወይም በሻይና በመሳሰሉት መጠጦች ላይ በማድረግ ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ትገልፃለች።

"ከዚያም ባሻገር ብዙ ሰዎች የማያውቁት ሦስተኛ አጠቃቀም አለው። እሱም ልክ እንደ ቅመማ ቅመም ለማጣፈጫ መጠቀም ነው። ይህን ደግሞ አሁን ካሉን ምርቶች በተጨማሪ ብዙ ሌሎችንም ለማካተት ጥናት እያደረግን እንገኛለን" ስትል ታክላለች።

አዲስ አበባ በሚገኘው እና ምርታቸውን ለገበያ በሚያቀርቡበት ሱቅ ለመግዛት የሚሄዱ ሰዎች "አብዛኛውን ጊዜ ላቨንደር፣ የጠጅ ሣርና የመሳሰሉትን ለምን አትሠሩም ብለው ይጠይቁናል። እኛ ግን ማተኮር የምንፈልገው በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙት እፅዋት ላይ ነው" ትላለች።

ለዚህም ምክንያቷን ስታስረዳ በኢትዮጵያ ብቻ በሚገኙ መዓዛማ እፅዋት ላይ በቂ አለመደረጉን እና ዘመናዊ በሆነ መልኩ ጥቅም ላይ ባለመዋላቸው በጊዜ ሂደት ሊጠፉ ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳላት ትገልፃለች።

በሂደትም " የኢትዮጵያን ተፈጥሮዋዊ እፅዋት በዓለም ደረጃ እንዲታወቁ የማድረግ ዓላማ ነው ያለን" ስትል ሕልሟን ታስረዳለች።

የጫካ ኦሪጂንስ ምርቶች

የፎቶው ባለመብት, Feven T

ጫካ ኦሪጂንስ ለምን ተጀመረ?

ፌቨን ከመዓዛማ እፅዋቶች የሚመረቱ ዘይቶች በመጠቀም ውበትንም ሆነ ጤናን መጠበቅ በጤና ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ማስቀረት እንደሚቻል የማሳወቅ ዓላማን አንግባለች።

ጫካ ኦሪጅንስ የተመሰረተበትን ዓላማንም ስታስረዳ "ዋናው ዓላማ 'ፕላንት ቤዝድ' [ዕጽዋትን መሰረት ያደረገ] ኮስሜቲክስ ሰዎች በቀላሉ እንዲያገኙ" በማሰብ ነው የተጀመረው ብላለች።

ኢትዮጵያ ውስጥ እየተረሱ ያሉ ወይም ባሕላዊ አጠቃቀማቸው ብዙና ከባድ ሥራ የሚጠይቅ በመሆኑ አብዛኛውን ጊዜ የተተዉ መሆናቸውንም ትናገራለች።

ከውጪ የሚመጡት የመዋቢያ ቅባቶች በቀላሉ እንዲሁም በብልቃጥ መገኘት መቻላቸው በማኅበረሰቡ ውስጥ የነበረውን ነባር እውቀት እንዳንፈትሽ ማድረጉን ታዝባለች።

በዚህም የተነሳ ባሕላዊ እውቀትን በመጠቀም በዘመናዊ መልክና አቀራረብ በማዘጋጀት ማቅረብ ሁለት ጥቅሞች እንዳሉት ትናገራለች።

በቀዳሚነት ተፈጥሯዊ የሆኑ ምርቶችን ለውበት ጥበቃ መጠቀም ማስቻሉን ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ባሕላዊ እውቀትን ጠብቆ ማቆየቱ ነው።

አክላም ፌቨን ጫካ ኦሪጂንስ ከገበሬው ጋር የሥራ ስምምነት መመስረቱን እና ይህም ቋሚ የሆነ የአቅርቦት ምንጭ እንደሚሆንላቸው ገልፃለች።

ለአርሶ አደሮቹም ቢሆን ምርታቸው በእርግጠኝነት እንደሚሸጥላቸው መተማመን እንዲችሉ ማድረጉንም ታስረዳለች።

"ማንኛውም ምርት አርሶ አደሮቹ ከሚሸጡበት ዋጋና ከተማ ሄዶ የሚሸጥበት ጋር ሲነፃፀር በጣም ሰፊ ልዩነት እንዳለው ለመገንዘብ ጊዜ አይፈጅም" የምትለው ፌቨን ይህ እንዲሆን የሚያደርገው ደግሞ ምርቶቹ በተለያዩ ሰዎች በኩል ስለሚያልፉ መሆኑን ትገልፃለች።

ለዚህም ጫካ ኦሪጅንስ በቀጥታ ከአርሶ አደሮቹ ጋር የሥራ ውል ማድረጉ ጠቀም ያለ ገንዘብ እንዲያገኙ እንደሚያስችላቸው ትናገራለች።

ይህ ብቻም ሳይሆን፣ ለአርሶ አደሮቹ "የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘገጃጀትና አቀማመጥ፣ የእፅዋት ማባዛት፣ ሳይጎዱ መቁረጥ 'ካቲንግ'፣ የውሃ መጠንና የመሳሰሉትን ምርታቸውን የሚያሻሽሉ ዘዴዎችን እናካፍላቸዋለን" ብላለች።

አርሶ አደሮቹ ከፌቨን ጋር

የፎቶው ባለመብት, Feven T.

እፅዋት ላይ መሰረት ያደረገ የህይወት ዘይቤ

እፅዋት ላይ መሰረት ያደረገ የህይወት ዘይቤ በሰውነታችን ውስጥም ሆነ ሰውነታችን ላይ የምናደርጋቸውና የምንጠቀምባቸው በሙሉ ከእፅዋት በተገኙ ምርቶች መተካት ማለት ነው።

በርካታ ኢትዮጵያውያን ጉንፋን በሚያዙበት ወቅት ባሕር ዛፍ ይታጠናሉ።

እንዲህ ዓይነት ነባር እውቀቶችን ኪስ በሚገባ መልኩ በሁሉም ዘንድ እንዲደርስ ከማድረግ ባሻገር የኢኮኖሚ ምንጭ ማድረግ እንደሚቻልም ትናገራለች።

"ለምሳሌ በሕንድ አገር አዩርቬዳ የሚሉት ሴክተር አላቸው። እነርሱም ለውበት ከሚጠቀሙበት አንስቶ ማጣፈጫቸው፣ ቅመማ ቅመሞቻቸው፣ ከሚበሉት ምግብ፣ ከሚጠጡት ሻይ እናም ሌሎች ሌሎችንም አካትቶ በተፈጥሮዋዊ ንጠረ ነገሮቻቸው ዙሪያ ራሱን የቻለ ኢኮኖሚውን የሚያንቀሳቅስ ሴክተር ነው።"

ፌቨን ሥራዋን ለማስፋት በማሰብ እንደ ጤና አዳምና ኮረሪማ ያሉ እፅዋትን በቋሚነት ተጠቃሚው እጅ ለማድረስ ሳታሰልስ ላለፉት ሁለት ዓመታት ስትሠራ ቆይታለች።

"ያሉንን ተፈጥሮዋዊ እውቀቶች ባሉበት እንጂ ቀይረን መጠቀምን ገና አልለመድንም። ባሉበት ስል እንደ ቅጠልነታቸው ማለቴ ነው፤ ለምሳሌ ጤና አዳምን በሻይ ወይም በቡና ውስጥ ቅጠሉን እንከታለን እንጂ ከቅጠሉ ዘይት አውጥተን ለሌላም ሌላም ጥቅም እንዲውል አናደርግም" ስትል ትዝብቷን ለቢቢሲ አካፍላለች።

"ተሳክቶልን ከተወስኑ ዓመታት በኋላ እኛም ጤና አዳምንና ኮሰረትን ለምሳሌ በሻይ መልክ እያደረግን ማቅረብ ብንችል ምኞቴ ነው። አንዳንዶቹን ለጣዕም ብቻ ነው የምንፈልጋቸው። እኔ ኮሰረት በሻይ እጠጣለሁ ጣዕሙን ስለምወደው ግን ሌሎቹ ደግሞ የጤና ጥቅም ያላቸው አሉ እብጠትን የሚከላከሉ፣ ለጉበት፣ ለኩላሊት ንፅህና የሚጠቅሙ. . . " ትላለች ፌቨን።