የፈጠራ ችሎታ እንዴት ይጎለብታል?

ጥናቶች እንደሚያሳዩት አንዳች አይነት ገደብ ሲቀመጥልን ለፈጠራ እንነሳሳለን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሰው ልጅ ለፈጠራ ሥራ የሚነሳሳው በምን አይነት ሁኔታ ውስጥ ሲሆን ነው ብለው ያስባሉ? ምናልባት ነጻነት ሲሰማው?

ነጻነት ፈጠራን ያጎለብታል ብለው የሚያምኑ ብዙ ናቸው። ጥናቶች እንደሚያሳዩት ግን አንዳች አይነት ገደብ ሲቀመጥልን ለፈጠራ እንነሳሳለን።

ፕ/ር ካትሪናል ትሮምፕ በኦፕን ዩኒቨርስቲ የሥነ ልቦና ባለሙያ ናቸው። ሰዎች ያሻቸውን የማሰብ፣ የመከወን ነጻነት ሲሰጣቸው የፈጠራ ችሎታቸው ይገደባል ይላሉ።

ምሳሌዎች እንመልከት። ኒውተን የካልኩለስ ንድፈ ሐሳብን ያገኘው ውሸባ (ኳረንታይን) ውስጥ ሳለ ነበር። ዶ/ር ሱውስ የልጆች መጽሐፍ በ50 የተለያዩ ቃላት ለመጻፍ ተወራርዶ ተሳክቶለታል።

ምሳሌዎቹ አንዳች ጫና ወይም አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ መግባት የፈጠራ ክህሎትን ያሳድጋል ወደሚለው ድምዳሜ ይወስዱናል።

የፈጠራ ችሎታ ላይ ምርምር የሚሠሩት ባርኖርስ ሱዛን ግሪንፊልድ፤ ሰዎች አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ሲገቡ የፈጠራ ችሎታቸው ሊያድግ እንደሚችል ይገልጻሉ። በእርግጥ አስገዳጅ ሁኔታዎች ለፈጠራ አዳጋች የሚሆኑበትም ጊዜ አለ።

አስገዳጅ ሁኔታዎች ሳይኖሩ ሲቀሩ ስልቹ እንሆናለን። በተቃራኒው ደግሞ ጫና ሲበዛብን ጭንቀት ይገጥመናል። ስለዚህም በሁለቱ ጽንፎች መካከል ያለውን አማራጭ መከተልን ባርኖርስ ይመክራሉ።

ፈጠራ ምንድን ነው?

ፈጠራ የእለት ከእለት ሕይወትን በተለየ መንገድ የሚገልጽና ለሰዎች ሌላ እይታ የሚፈጥር እንደሆነ ባርኖርስ ይናገራሉ።

የሥነ ልቦና መምህሩ ዶ/ር ቮልከር ፓተንት ደግሞ ፈጠራ የሚባለው "ከዚህ ቀደም ያልታየ ነገር ሲሠራ ነው" ይላሉ።

ፈጠራን የታቀደ እና የድንገቴ በሚል ለሁለት የሚከፍሉ አሉ።

አርቲስት ኩዊላ ኮንስታንስ ፈጠራን ከሚገድቡ መካከል ፓለቲካዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ሁኔታን ትጠቅሳለች።

ከሠርቶ አደር ጥቁር ቤተሰብ የተገኘች አርቲስት፤ መካከለኛ ገቢ ባላቸው ነጭ ወንዶች ቁጥጥር ሥር የሆነ የጥበብ ዓለምን ሰብሮ መግባት ሊፈትናት ይችላል።

አርቲስቷ እንደ ምሳሌ የምትጠቅሰው ፌዝ ሪንጎልድ የተባችውን አርቲስት ተሞክሮ ነው። አርቲስቷ በጣም ትልቅ ሸራ ወጥራ መሥራት ብትፈልግም ቤቷ ጠባብ ስለነበረ አልቻለችም። ይህ መሰናክል ግን ግቧን ከማሳካት አላገዳትም።

አርቲስቷ እንደ አማራጭ የወሰደችው በጨርቅ ላይ እየሳሉ ወደተለያዩ ጋለሪዎች መውሰድን ነበር። ሠዓሊዋ ችግር ፈጠራን እንደሚያነሳሳት፣ ብልሀት እንደሚያስተምርም ማሳያ ናት።

የፈጠራ ችሎታን ማሳደግ

ጸሐፊ ነዎት እንበል። ግጥም መጻፍ እምቢ ቢልዎ ልብ ወለድ በመሞከር ራስዎን ለፈጠራ ማነሳሳት እንደሚችሉ ባለሙያዎች ይመክራሉ። ሙዚቀኛ ከሆኑ ደግሞ ከሚያዘወትሩት የሙዚቃ መሣሪያ ውጪ ያሉ መሣሪያዎችን መሞከር ይችላሉ።

በቀን ውስጥ የተወሰነ ሰዓት የፈጠራ ችሎታን ለማዳበር መመደብ አንድ አማራጭ ነው። በመደቡት ሰዓት ሌላ ነገር ማድረግ አቁመው ለፈጠራ ጊዜ መስጠት ይጠበቅብዎታል።

ለፈጠራ ሥራዎ የጊዜ ገደብ መስጠትም አንዱ መንገድ ነው። የተለያዩ ሐሳቦችን ለመተግበር መሞከርም ይመከራል።

ሠዓሊ ከሆኑ በተለያዩ ቀለማት የተለያየ ስልት መሞከርን የምትመክረው አርቲስቷ ኩዊላ ናት።

"የተለያየ ሐሳብ እያፈለቁ ሙከራ ማድረግ የፈጠራ ችሎታን ያሳድጋል። የአስተሳሰብ አድማስንም ያሰፋል" ትላለች።