ከአውሮፕላን ወርደው በሸሹ ተሳፋሪዎች ምክንያት የስፔኑ አየር ማረፊያ ተዘጋ

ኤይር አረቢያ ማሮክ አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, EPA

በስፔን ውስጥ በመንገደኞች ከሚጨናነቁ አየር ማረፊያዎች መካከል አንዱ ተሳፋሪዎች በህገወጥ መንገድ ወደ አገሪቱ ለመግባት ሙከራ ማድረጋቸውን ተከትሎ ለሰዓታት ያህል መዘጋቱ ተገለጸ።

ከሞሮኮዋ ካዛብላንካ ወደ ቱርክ መዲና ኢስታንቡል ይበር የነበረ አውሮፕላን በድንገተኛ ህክምና ምክንያት የበረራ አቅጣጫውን ለመቀየር ተገዶ ወደ ወደ ስፔኗ ፓልማ ዴ ማሎርካ እንዲቀይር ተደርጎ ነበር።

አውሮፕላኑ በስፔኗ ከተማ በሚያርፍበት ወቅት 21 ተሳፋሪዎች ማኮብኮቢያውን አቋርጠው በቆሙ አውሮፕላኖች በመከለል ተደብቀው ወደ ከተማዋ መግባታቸውም ተነግሯል።

ፖሊስ የተወሰኑትን በቁጥጥር ስር ቢያውልም 12ቱ አሁንም በሽሽት ላይ ናቸው።

ቡድኑ ከአውሮፕላን አምልጠው የሮጡት በድንገት ነው ወይስ ከመጀመሪያ ታቅዶ የተደረገ ሰፊ ሴራ ነው የሚለውን ፖሊስ እየመረመርኩ ነው ብሏል።

የባሊያሪክ ደሴቶች ከፍተኛ የስፔን መንግስት ባለስልጣን አይና ካልቮ ሁኔታው በስፔን አየር ማረፊያ ታይቶ የማይታወቅና ያልተጠበቀ ነው ብለዋል።

ከሞሮኮ ተነስቶ ወደ ቱርክ እየበረረ የነበረው የኤይር አረቢያ ማሮክ አውሮፕላን ተሳፍሮ የነበረ ሞሮካዊ መንገደኛ በስኳር ህመም ምክንያት ራሱን በመሳቱ የድንገተኛ አደጋ ሰራተኞች ህክምና መደረግ አለበት በሚልም ነው ቀረብ ባለው ወደ ስፔን አውሮፕላን ያረፈው።

ግለሰቡን ከአውሮፕላን ለማስወጣት እየተደረገ ባለ ሂደት ሌሎች 21 ተሳፋሪዎች ወርደው በቆሙ አውሮፕላኖች በመከለል ተደብቀዋል ተብሏል።

የታመመው ግለሰብ በሆስፒታል በተደረገ የጤና ምርመራ ጤናው በመልካም ሁኔታ እንዳለ በመገኘቱ ከሆስፒታል እንዲወጣ ተደርጎ ስፔን በህገወጥ መንገድ ለመግባት ሞክሯል በሚልም ክስ በቁጥጥር ስር መዋሉን የስፔኑ ኢፌ የዜና አገልግሎት ዘግቧል።

ግለሰቡን አጅቦ ወደ ሆስፒታል የሄደውም ተሳፋሪ መጥፋቱ ተነግሯል።

በቁጥጥር ስር ከዋሉት አብዛኞቹ አምልጠው የተገኙት በጋርዲያ ሲቪል ከተማ ነው ሲል የአገሬው ማጆርካ ዴይሊ ቡሌቲን ዘግቧል፣ "አንድ ሰው ወደ ማናኮር በሚወስደው መንገድ ሲሄድ ተይዟል" ብሏል።

በአውሮፕላኑ ውስጥ ያልተገባ ባህርይ በማሳየቱ በቁጥጥር የዋለው ግለሰብን ጨምሮ 24 ተሳፋሪዎች በዚህ ጉዳይ ተሳታፊ ነበሩ ተብሏል።

በዚህ ክስተትም ምክንያት ወደ 60 የሚጠጉ የሀገር ውስጥ እና አለም አቀፍ በረራዎች አቅጣጫቸውን ቀይረዋል እንዲሁም እንዲዘገዩ ሆነዋል።

የኤር አረቢያ ማሮክ አይሮፕላን ወደ መዳረሻው ቱርክ ከቀሩት መንገደኞች ጋር ጉዞውን መቀጠሉም ተዘግቧል።