ከአንድ አመት ጦርነት በኋላ የህዝቡን ሰቆቃ እንዴት ለማስቆም ይቻላል?

አንደኛውን የትግራይ ጦርነት አስመልክቶ እያለቀሰች ያለች ሴት

የፎቶው ባለመብት, EPA

    • ፀሐፊ, በካትሪን ባያሩሃንጋና በየማነ ናግሽ
    • የሥራ ድርሻ, ቢቢሲ ኒውስና ቢቢሲ ትግርኛ

ከአንድ ዓመት በፊት በሰሜን ኢትዮጵያ በተቀሰቀሰው ጦርነት የትግራይ አማፂ ኃይል የበላይነት ይዟል።

በፖለቲካ ማሻሻያዎቻቸው ምክንያት ከትግራይ ገዢ ፓርቲ ጋር ፍጥጫ ውስጥ የገቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሰሞኑ በአገር አቀፍ ደረጃ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጀዋል። በአገሪቱም ውስጥ ፍራቻና ጥርጣሬዎች ሰፍኗል።

አማጺያኑ ወደ ዋና ከተማው እየገሰገሱ ባሉበት በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እንዲታጠቁና አካባቢያቸውን በንቃት እንዲጠብቁ ጥሪ አቅርቧል።

በህወሓት የሚመራው የትግራይ ኃይሎች በአማራ ክልል የሚገኙትን የደሴን እና ኮምቦልቻ ከተሞችን ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ተቆጣጥረዋል።

ተዋጊዎቹ በትግራይ በትግራይ አጎራባች አማራ ክልል ውስጥ ከመዲናዋ አዲስ አበባ ወደ 375 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ይገኛሉ።

የደሴ ከተማ በደቡብ በኩል አዲስ አበባ እንዲሁም በምሥራቅ በኩልም ጂቡቲ መድረስ የሚያስችል መስመር መኖሩን ተከትሎ ከተማዋን ለመቆጣጠር የተደረገው ውጊያ ከታዩት እጅግ ፈታኝ ጦርነቶች አንዱ እንደሆነ ይታመናል።

ምግብ በአማራ ክልል ደባርቅ ሲከፋፈል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ደሴን የትግራይ ኃይሎች ከመቆጣጠራቸው በፊት በዋነኛው ሆስፒታል ይሰሩ የነበሩ አንድ ግለሰብ እንዳሉት በክልሉ ጦርነት መዛመቱን ተከትሎ የከተማዋም ሁኔታ ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ ተለውጧል።

ስሜ አይጠቀስ ያሉት እኚህ ግለሰብ ደሴ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ እና የባህል ስብጥር መታያ በመሆኗ "የፍቅር መዲና" የሚል ስያሜ ያገኘች ሲሆን የበለፀገ የኢኮኖሚ ማዕከል እንደሆነችም ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ነገር ግን ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከአማፂያኑ ግስጋሴ ሸሽተው ወደ ከተማዋ ገብተዋል።

"ወደ ሥራ ስሄድ እና ስመለስ ትንንሽ ልጆች ሱሪዬን እየጎተቱ ዳቦ እንድገዛላቸው ይለምኑኝ ነበር" ብለዋል።

የመንግሥት ወታደሮች ከተማዋን ለቀው መውጣታቸውን ተከትሎ ግለሰቡም ከ10 ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ሆስፒታሉን ጥለው ሄዱ። በአሁኑ ወቅትም አዲስ አበባን መኖሪያቸው አድርገዋታል።

በአዲስ አበባ ከተማም የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ቴዎድሮስ ኃይለማርያም ኅብረተሰቡን በማስተባበር ተዋጊዎችን ለመላክና ግስጋሴውን ለማስቆም እንዲሁም ለተፈናቀሉ ወገኖች እርዳታ በማከፋፈል ላይ ይገኛል።

ፓርቲያቸው የህወሓት ዋነኛ አላማ ወደ ስልጣን መመለስ እንደሆነ ያምናል ይላሉ።

ህወሓት በኢህአዴግ ውስጥ አገሪቱን ለ27 ዓመታት መርቶ ከአራት ዓመታት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥት ከማዕከላዊው ስልጣን ወደ ጎን ገሸሽ ተደርጓል።

"ሁለት አማራጮች አሉ፤ ወይ ህወሓት ተሸንፎ የኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት ይድናል ወይም ከሁሉ የከፋው ሁኔታ ህወሓት አዲስ አበባን ተቆጣጥሮ በመግዛት በመላ አገሪቱ የእርስ በርስ ጦርነት ይከሰታል" ብለዋል አቶ ቴዎድሮስ ለቢቢሲ።

የትግራይ ተወላጆች 'እየታፈሱ ነው'

በመዲናይቱ አዲስ አበባ ላሉ የትግራይ ተወላጆች የደሴ መያዝ በከተማዋ ውስጥ የብሔር ውጥረቱ እንዲጨምር አድርጎታል።

በአዲስ አበባ የምትኖር የትግራይ ተወላጅ የሕግ ባለሙያ በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ "የተወለድኩባት እና ያደኩባት ከተማ" አይደለችም ብላለች።

"ፖሊስ በየቤቱ፣ በየካፌው እና በየቡና ቤቱ በሚደረጉ አሰሳዎች እንዲሁም በታክሲዎች እና በአውቶብሶች ውስጥ መታወቂያ ፍተሻ በሚደረግበት ወቅት የትግራይ ተወላጆች እየታፈሱ ይገኛሉ" በማለት ያለውን ሁኔታ ታስረዳለች።

በዚሁ ሳምንትም በአንድ ሬስቶራንት ውስጥ እራት እየበሉ እያሉ ስለታፈሱ የትግራይ ተወላጆች ቢቢሲ ተነግሮት ነበር።

የትግራይ ተወላጅ የሆኑ የንግድ ተቋማት ተዘግተዋል

የፎቶው ባለመብት, AFP

"ትግራዋይ ከሆንክ ምንም አይነት ተስፋ የለህም። ትታሰራለህ። እስሩም የሚደረገው በብሔር ስም ነው" ሲሉ አንድ ነዋሪ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ቃል አቀባይ በበኩላቸው እስር የሚፈጸመው ሕገ ወጥ ድርጊቶችን የሚያሳይ ማስረጃ ከተገኘ በኋላ ነው ብለዋል።

ቃለ አቀባዩ የታሰሩት አብዛኞቹ የትግራይ ተወላጆች መሆናቸውን ቢያረጋግጡም የሌላ ብሔር ተወላጆችም መታሰራቸውን ተናግረዋል።

አማፂያኑ ግስጋሴያቸው በትግራይ ክልል ላይ ያለው እገዳ እንዲያቆም ለማስገደድ ነው ይላሉ። እርዳታ በከፍተኛ ሁኔታ በሚያስፈልግበት በትግራይ ክልል የኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ የመገናኛ ዘዴዎች እና የባንክ አገልግሎት ተቋርጧል።

ከግንቦት ወር ጀምሮም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 400 ሺህ ሰዎች በረሃብ አፋፍ ላይ መሆናቸውን አስጠንቅቋል።

ህወሓት በሰኔ ወር ሠራዊቱን ከትግራይ ዋና ከተማ መቀሌ ካስወጣ በኋላ የረድዔት ድርጅቶች ወደ ክልል የሚወስዱ መንገዶች መዘጋታቻው እንዲሁም በነዳጅ እና ገንዘብ ላይ የተጣለው እገዳ ከአምስት ሚሊዮን በላይ አስቸኳይ እርዳታ የሚሹ ሰዎችን መድረስ ፈታኝ አድርጎታል።

በመጀመሪያ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር ጋር በቅድመ ሁኔታዎች ላይ የተመሰረተ ድርድር ያስቀመጡት የትግራይ ኃይሎች በባለፉት ሳምንታት በአማራ እና አፋር ክልሎች ባገኙት ወታራዊ ድሎች ምክንያት አንደራደርም ብለዋል።

የቀድሞ የአገሪቱ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም እና የትግራይ ኃይሎች ከፍተኛ አዛዥ የሆኑት ጄኔራል ፃድቃን ገብረትንሳኤ ጦርነቱ እያለቀ ነው ቀጣዩ እርምጃም ድህረ ዐቢይ ብሔራዊ ውይይት እንደሚሆን ተናግረዋል።

"ውስብስብ የሆነውን የአገሪቷን ፖለቲካ በራሳችን ፍላጎት ለመፍታት አስበን አናውቅም። ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በአንድ ላይ በማሰባሰብ ስለአገሪቱ የወደፊት እጣ ፈንታ የምንወያይበት መድረክ እንፈጥራለን" ሲሉ ለትግራይ ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

የወላጆች ድንጋጤ

በትግራይ ያለው ሰብአዊ ቀውስ አሁንም አሳሳቢ ነው። በመቀለ አይደር ሪፈራል ሆስፒታል በግሉኮስ ምግብ እየተላለፈላት ያለችው የአንድ ዓመት ጨቅላ የሆነችው ኤደን ገብረፃድቅ ለቅሶ በኮሪደሩ ላይ ሲያስተጋባ ቢቢሲ በደረሰው ቪዲዮዎች ላይ ይታያል።

የ11 ዓመቷ መብርሂት ግድይ በመቀለ አይደር ሪፈራል ሆስፒታል

የፎቶው ባለመብት, Ayder Referral Hospital medic

የምስሉ መግለጫ, የ11 ዓመቷ መብርሂት ግድይ በመቀለ አይደር ሪፈራል ሆስፒታል

"በመጀመሪያ በምግብ እጥረት እየተሰቃየች እንደሆነ አላውቅም ነበር። አሁን የተመጣጠነ ምግብ እጦት እንዳለባት ነግረውኛል" ስትል በሁኔታው የተደናገጠችው እናቷ ህይወት በርሄ ልጇን ልታባብል እየሞከረች ትናገራለች።

ከጦርነቱ በፊት "ባለቤቴ ተቀጥሮ ይሠራ ነበር ። እኔ ደግሞ የቤቱን ሥራ በመሸፈን ልጆቹን ቤት ውስጥ እንከባከብ ነበር። ልጆቻችንንም በጥሩ ሁኔታ እናሳድጋቸው ነበር። ልጆቻችን ምርጥ ምግብ ያገኙ ነበር ሁልጊዜም ጥሩ ልብስ ይለብሱ ነበር" ብላለች።

በሌላ አልጋ ላይ ደግሞ እጆቿ ቅጭጭ ያሉት መብርሂት ግደይ ጋደም ብላለለች። አባቷም ግደይ መረሳ ያለው ገፅታና ከሲታነቱ ከልጁ ጋር ተመሳሳይ ሲሆን ልጁንም ሙዝ እንድትበላ ለማድረግ ቀስ ብሎ ደግፎ ያስቀምጣታል።

እነ ግደይ ከገጠራማ መኖሪያቸው ቆላ ተምቤን ወደ ሆስፒታል ለመድረስ ከ100 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት ተጉዘዋል።

ያለፉበት መንገድም የመንግሥት ወታደሮች በትግራይ ውስጥ በነበሩበት ወቅት ከባድ ውጊያ የተደረገባቸው ስፍራዎችን ይሸፍናል። በርካታ ነዋሪዎችም ቀያቸውን ለቀው ወደ ተራራዎች ለመሰደድ ተገደዋል።

የኢትዮጵያ ወታደሮችና አጋሮቻቸው ከትግራይ ከወጡ በኋላ ነዋሪዎቹ የተመለሱ ሲሆን ቤታቸው ተቃጥሎ በሬዎቻቸውና አህዮቻቸው ተዘርፈውም ነው ቀያቸውን ያገኙት።

"የተከሰተው ነገር በሙሉ ተቀብለነው ነበር። ልጄ ግን በጠና ታመመች፤ ከዚህ በፊት በጣም ጤነኛ ነበረች" ይላሉ።

ዶክተሮች የ11 ዓመት ልጁ የልብ ችግር እንዳለባት ነግረውታል። ምናልባትም በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ምክንያት ሳይመጣ የቀረ እንዳልሆነም ተነግሮታል።

እነዚህን ቃለ መጠይቆች ቢቢሲ ማግኘት የቻለው ከህክምና ባለሙያዎች ሲሆን ተቀርጸው የወጡትም በድብቅ ነው።

የቴሌኮሙኑኬሽን እና የኢንተርኔት አገልግሎት በመዘጋቱ በክልሉ ያሉ ነዋሪዎችን ማግኘት አልተቻለም። ቢቢሲ እንደ ሌሎቹ ሚዲያዎች ወደ ክልሉ እንዳይገባ ታግዷል።

ያልተሳኩ ማስፈራሪያዎች

በቅርቡ ኢትዮጵያን የጎበኙት የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ፕሬዚዳንት ፒተር ሞረር ግጭት ወዳለባቸው አካባቢዎች መሄድ አልቻሉም።

"በአሁኑ ወቅት ምንም አይነት የተስፋ ብርሃን እየፈነጠቀ አይደለም" ሲሉ ፕሬዚዳንቱ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"ለግጭቱ ቀደም ብለን ፖለቲካዊ መፍትሄ ማምጣት ያስፈልጋል። ምክንያቱም መሞኘት የሌለብን ጉዳይ ግጭቱ ነገ ቢቆምም አሁንም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተፋናቃዮች አስቸኳይ እርዳታን ይሻሉ" በማለት ያስረዳሉ።

አሜሪካ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የአፍሪካ ሕብረት ድርድር እንዲደረግ ሲወተውቱ ቆይተዋል።

የማዕቀብ ዛቻም ሆነ አሜሪካ ኢትዮጵያን ከቀረጥ ነፃ ንግድ ተጠቃሚነት እድል አጎዋ ማገዷ የግጭቱን አቅጣጫ መቀየር አልቻለም።

የኢንተርናሽናል ክራይሲስ ግሩፕ ከፍተኛ ተንታኝ የሆኑት ዊሊያም ዴቪሰን፣ የዕርዳታ እግዶችን ማንሳት እና ለትግራይ አስፈላጊ የሆኑትን መሰረታዊ ገልግሎቶች ወደነበረበት እንዲመለሱ ማድረግ ለኢትዮጵያ መንግሥት ይጠቅመዋል ይላሉ።

"የዓለም አቀፍ መሪዎች የጦርነቱ አቅጣጫ እንዲቀየር ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የመጨረሻ እድል መስጠት ብቻ ሳይሆን ወደ አዲስ አበባ በፍጥነት ለመዝመት መሞከር ምናልባት የከፋ ብጥብጥ እና አለመረጋጋት ሊያስከትል ስለሚችል ለትግራይ አመራሮች ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥሪ ማቅረብ አለባቸው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሆኖም ከጥቂት ዓመታት በፊት የኖቤል የሰላም ሽልማትን ያገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከጎረቤት ኤርትራ ጋር የነበረውን ጦርነት መቋጫ እንዲያገኝ ቢያደርጉም በትግራይ ላይ ምንም አይነት መለሳለስ አላሳዩም።

ኢትዮጵያ የጦርነቱን አንድ ዓመት ስታከብር የ45 ዓመቱ መሪ የአገራቸውን ሕዝብ ወደ ጦር ግንባር እንዲያቀኑ ወይም ጦርነቱን እንዲደግፉ አሳስበዋል።

"ይህንን ጠላት በደማችን፣ በአጥንታችን ቀብረን የኢትዮጵያን ክብር ቀና እናደርጋለን" ሲሉ ተደምጠዋል።