የትግራይ ጦርነት እና ለተደራራቢ ችግር የተጋለጡት ኤርትራውያን ስደተኞች

በትግራይ የሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በትግራይ የሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች

አንድ ዓመት ሊሞላው የተቃረበው ጦርነት መነሻው ትግራይ ክልል ውስጥ ቢሆንም አሁን ግን ወደ አማራ እና አፋር ክለሎች ተስፋፍቷል።

በዚህ ጦርነት በሦስቱም ክልሎች ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሲፈናቀሉ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ በጦርነቱ ምክንያት መሞታቸው ይነገራል።

ጦርነቱ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ሌሊት ከመቀስቀሱ በፊት 100 ሺህ የሚጠጉ ኤርትራውያን ስደተኞች በትግራይ ክልል በሚገኙ አራት የስደተኞች መጠለያዎች [ዓዲ ሐሩሽ፣ ማይ ዓይኒ፣ ሽመልባ እና ህጻጽ] ይኖሩ ነበር።

ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ ግን ለስደተኞቹ ጥበቃ የሚሰጣቸው አካል ስላልነበረ ከተዋጊ ኃይሎች በሚተኮሱ ከባድ መሳሪያዎች የሞትና የመቁሰል አደጋ እንዲሁም የንብረት ውድመት እንደደረሰባቸው የሰብኣዊ ድርጅቶች ባወጧቸው ሪፖርቶች ላይ ጠቁመዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በበኩሉ ከእነዚህ ስደተኞች መካከል በኤርትራ ወታደሮች በግድ ወደ ኤርትራ የተወሰዱ መኖራቸውን በሪፖርቶቹ ላይ አመልክቷል።

ሽረ- አዲስ አበባ- ናይሮቢ

መለስ ሙሉጌታ በትግራይ አማፂያን እና በፌደራል መንግሥቱ መካከል ጦርነት ከመጀመሩ በፊት ኑሮውን ያደረገው በሽመልባ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ነበር።

ጥቅምት 22/2013 ዓ.ም ከጀርመን የመጣ ዘመዱ ሽመልባ የስደተኞች መጠለያ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ቤተሰቦቹን ለማግኘት ወደ ሽረ መሄዱን ያስታውሳል።

የሰባት እና የ11 ዓመት ልጆቹን ሽመልባ ከጎረቤት ጋር ትቶ ዘመዱን ጠይቆ በነጋታው ለመመለስ ነበር የሄደው።

እርሱም እንግዳውን አስተናግዶ ወደ ሽመልባ ለማሳፈር ከመጠለያ ጣቢያው በመውጣት ወደ ሽረ መጥቶ አውቶቡስ አሳፈረው።

". . . በሰጠኝ ገንዘብ ደግሞ ለልጆቼ አንዳንድ ነገሮች ገዝቼ በነጋታው ለመመለስ ወደ ማደሪያዬ ሄድኩኝ" ይላል።

ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ሌሊት ግን፣ ሽረ ከተማ በከባድና ቀላል መሳሪያ ተኩስ ተረብሻ ማደርዋን ያስታውሳል።

"መጀመሪያ ስላልገባኝ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ወታደሮች እየተዋጉ ነው የመሰለኝ፤ ጠዋት ወደ ልጆቼ ለመመለስ ወደ መናኸሪያ ስሄድ ሁሉንም እንቅስቃሴ ቆሞ ከተማዋ በከባድ ስጋት ተውጣ ነበር።"

በዚህ ጊዜ፣ የልጆቹን ሁኔታ ለማወቅ ስልክ ለመደወል ቢሞክርም አልቻለም።

በተለያየ ምክንያት ከመጠለያው ወጥተው የነበሩና በልጆቻቸው ሁኔታ የሰጉ ስደተኞች ወደ መጠለያ ጣቢያው ለመመለስ በእግር ለአምስት ሰዓታት መጓዛቸውን ያስታውሳል።

"ከሩቅ የታጠቁ ሰዎች ስናይ እየተደበቅን እንደምንም ልጆቼ ጋር ደረስኩኝ። መጠለያው በፍርሃት ተውጦ ጠበቀኝ፤ እኔ አላየሁም ግን ብዙ ግፍ እንደደረሰባቸው ሰማሁ። ከዚያ ልጆቼን ይዤ ጎንደር ገባሁ" ይላል።

መለስ፣ በካናዳ ከምትኖረው ባለቤቱ ጋር ለመቀላቀል ነበር በ2016 (እአአ) ከኤርትራ የወጣው።

"ጉዳዩን አዲስ አበባ ላይ ለመጨረስ አስበን ነበር፤ ከዚያ ናይሮቢ እንጂ እዚህ አይፈጥንም ስለተባልን 5000 ዶላር ከፍዬ ልጆቼን ይዤ ወደ ኬንያ መጣሁ" በማለት አሁን ኢስሊ በሚባለው አካባቢ እየኖረ እንደሆነ ይናገራል።

ሑመራ - ገዳርፍ- ካርቱም - ሊ

ፍጹም መብራህቱ፣ መንግሥት የከተማ መኖሪያ ፍቃድ ከሰጣቸው ስደተኞች አንዱ ሲሆን በሑመራ ያረጀ ብረት ድስትና ምድጃ እየጠገነ ኑሮውን ይገፋ ነበር።

የ41 ዓመቱ ፍጹም፣ በከተማዋ ለሦስት ዓመታት ሲኖር አንድ የመጠገኛ ማሽን ገዝቶ ሥራውን ያከናውን ነበር።

"ከሑመራ ከመውጣቴ በፊት በነበረው አንድ ዓመት ከስድስት ወር በቋሚነት የተሰበረ በር፣ መስኮትና ሌሎች ጥገና እሰራ ነበር። ጦርነቱ ሲጀመር ግን ምንም ነገር ሳልይዝ ወደ ሱዳን ተሰደድኩ። እዚያም ግን አንዳንድ ወጣቶች በወንድሞችህ ምክንያት ነው ችግር ውስጥ የገባነው፤ ትሰልልም ይሆናል ይሉኝ ስለነበር በስጋት ተመልሼ ካርቱም ገባሁ" ይላል።

ካርቱም ለሦስት ሳምንታት ብቻ ነበር የቆየው።

ስዊድን አገር የምትኖር እህቱና ሌሎች የላኩለት ገንዘብ በማሰባሰብ እንደገና ወደ ሊቢያ ተሰደደ።

"ከካርቱም ወጥተን ኡምዱርማን የምትባል ከተማ ስንደርስ ነበር የደላሎቹ ግፍ የጀመረው፤ ሁሉም እስኪሰባሰብ በሚል ለስምንት ቀናት ብስኩትና ውሃ እየሰጡን ቆየን።"

ከዚህ በኋላ ለ13 ቀናት በመኪና ተጉዘው ሊቢያ ቤንጋዚ ደረሱ። ከሱዳን ሲነሱ በመርከብ እንደሚጓዙ የተነገራቸው ተረስቶ መንገላታት ጀመሩ።

ፍጹም እንደምንም ሊቢያ ከገባ ዘጠኝ ወራት አልፈዋል። ሆኖም ህይወት እየከፋ ሦስት ጊዜ በሊቢያ ፖሊስ ታስሮ፣ ሁለት ጊዜ ገንዘብ ከፍሎ አንድ ጊዜ ደግሞ አምልጦ እንደወጣ ይናገራል።

'የገቡበት የማይታወቀው 50 ስደተኞች'

በትግራይ ክልል፣ ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት 100 ሺህ የሚጠጉ ኤርትራውያን ስደተኞች ይኖሩ እንደነበረ ይገለጻል።

ሆኖም ግን ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ባሉት ወራት የኢትዮጵያ መንግሥት ስደተኞችን በሕጋዊ መንገድ መቀበል እና መመዝገብ አቁሞ ስለነበረ በርካታ ስደተኞች በተለያዩ የክልሉ ከተሞች በመኖራቸው ቁጥሩ ከዚህ ሊበልጥ እንደሚችል የስደተኞች መብት ተሟጋቾች ይናገራሉ።

"ሽመልባና ህጻጽ ሙሉ ለሙሉ ስለወደሙ በእነዚህ መጠለያዎች የነበሩ ስደተኞች ወደ ማይ ዓይኒ እና ዓዲ ሐርሽ ሲገቡ ብዙዎች ደግሞ ወደ አዲስ አበባ ሄደዋል፤ የገቡበት ያልታወቀም አሉ" ይላል የመብት ተሟጋቹ ጆርጆ ገብረሥላሴ።

እርሱ፣ ከጥር እስከ ሐምሌ 2021 (እአአ) ባሉት ወራት 13 የግድያ፣ የጾታዊ እና የዝርፊያ ጥቃቶች ሪፖርቶች እንደደረሱት ይናገራል።

"በሁለቱም መጠለያዎች የህክምና እና የእርዳታ አቅርቦት ስለሌለ ስደተኞቹ ለረሃብ መጋለጣቸው እና ህጻናት እየሞቱ እንደሆነ ሪፖርቶች ይደርሱናል" ሲልም ያክላል።

በተጨማሪም በሁሉም መጠለያዎች 100 ሺህ ስደተኞች ከነበሩ እስከ አሁን "23 ሺህ ብቻ ናቸው በሁለቱም መጠለያዎች ያሉት። ሌላው የት ገባ ከተባለ እጅግ አሳሳቢ ነው" ይላል።

አሜሪካ የሚገኙ ሱርባና እና ጋንታ አሜሪካ፣ የሚባሉ የኤርትራውያን ማኅበራት አድራሻቸው ጠፋ የተባሉ ስደተኞችን መመዝገብ ጀምረዋል።

በዚህ መሰረት እስከ አሁን "50 የሚደርሱ አድራሻቸው ጠፋ የተባለ ኤርትራውያንን መዝግበናል፤ እነዚህ በሽረ፣ ዓድዋ፣ አክሱም፣ ፈረስ ማይ፣ አዲግራት እና ሐውዜን ይኖሩ ነበር የተባሉ ሰዎችን ያጠቃልላል" ሲል ይገልጻል።

ጆርጆ ገብረሥላሴ፣ ይህንን መረጃ ዓለም አቀፍ ተቋማት ቀይ መስቀል፣ አይኦኤም፣ ዩኤንኤችሲአር እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት እንዲያውቁት መደረጉን ለቢቢሲ ተናግሯል።

ከዚህ ጎን ለጎን በሽረ 450፣ በአዲግራት 550፣ በመቀለ ደግሞ 3000 የሚደርሱ ኤርትራውያን መታሰራቸውን በተመለከተ መረጃ አግኝተናል ብሏል።

የኤርትራውያን ስደተኞች ሁኔታ በኢትዮጵያ

ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ በተለይ ከ21 ሺህ በላይ ስደተኞች ሽመልባ እና ህጻጽ መጠለያ ካምፖች የነበሩ ስደተኞች የመገደል፣ ታፍኖ የመወሰድና መበታተን አደጋ እንደገጠማቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርቶች ይገልጻሉ።

ከእነዚህ ዘጠኝ ሺህ ስደተኞች ወደ ማይ ዓይኒ እና ዓዲ ሐሩሽ መወሰዳቸው የስደት እና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ገልጿል። ሌሎች ከ5200 በላይ ደግሞ በአዲስ አበባ መመዝገባቸው ጠቁሟል።

ከዚህ ውጪ በአፋር ክልል ከ50 ሺህ በላይ ስደተኞች እንደሚገኙ እና በጦርነቱ ምክንያት አደጋ ላይ መሆናቸው ይገለጻል።

በጠቅላላ በኢትዮጵያ ከ200 ሺህ በላይ ኤርትራውያን ስደተኞች እንደሚገኙ ይነገራል።