የአማራ ክልል በየደረጃው ያሉ አመራሮችን ጨምሮ ለሕዝቡ አስቸኳይ ጥሪ አቀረበ

የፎቶው ባለመብት, Fana BC
የአማራ ክልል ምክር ቤት ትናንት እሁድ ጥቅምት 21/2014 ዓ.ም. ባካሄደው አስቸኳይ ስበሰባ ህወሓትን በመደበኛ የሕግ ማስከበር ሥርዓት ብቻ ማሸነፍ ስለማይቻል መላው የክልሉ ሕዝብ ዘመቻውን እንዲቀላቀል አስቸኳይ ጥሪ አቀረበ።
የአማራ ክልል ምክር ቤት ባዋጣው ባለዘጠኝ ነጥብ አስቸኳይ ጥሪ በየደረጃው ያለው የክልሉ አመራር ጥሪውን ተቀብሎ ዘመቻውን ከፊት ሆኖ እንዲያስተባብር፣ ይህን የማያደርግ ካለ ግን ሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ገልጿል።
ምክር ቤቱ ይህን የአስቸኳይ ጥሪ ያስተላለፈው የህወሓት አማጺያን ኮምቦልቻን ጨምሮ የደቡብ ወሎ አካባቢዎችን መቆጣጠራቸውን ካስታወቁ በኋላ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም ሕዝቡ 'የክት' ጉዳዩን አቆይቶ ህወሓትን 'ለመመከት፣ ለመቀልበስና ለመቅበር ማናቸውንም መሳሪያ እና አቅም ይዞ በሕጋዊ አደረጃጀት' ዘመቻውን እንዲቀላቀል ጥሪ አቀርበዋል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት ትናንት ባስተላለፈው አስቸኳይ ጥሪ የትኛውም የመንግሥት ተቋም መደበኛ አገልግሎቱን አቋርጦ "በጀቱን ጨምሮ ሁሉንም ነገር የገጠመንን የህልውና ዘመቻ ለመቀልበስ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ እንዲረባረብ ተወስኗል" ብሏል።
በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ዘመቻውን ተቀብለው ሕዝብ አደራጅተው እና ከፊት ሆነው እየመሩ ወደ ግንባር እንዲዘምቱ ተወስኗል፤ ምክር ቤቱ "ይህን በማያደርጉ አመራሮች ላይ ሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ" መወሰኑን ገልጿል።
ተሸከርካሪዎችን በተመለከተ፤ ምክር ቤቱ ሁሉንም የመንግሥት ተሸከርካሪዎች ወደ አንድ ማዕከል በማሰባሰብ ለሕልውናው ዘመቻ አገልግሎት እንዲውሉ አሳስቧል።
የግል ተሸከርካሪ ባለቤቶች "ለሕልውና ዘመቻው ስኬት ሲባል በተፈለገ ጊዜ ሁሉ ተሸከርካሪዎቻቸውን በመስጠት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ተወስኗል" ሲል ምክር ቤቱ አስታውቋል።
ምክር ቤቱ የመንግሥትም ሆነ የግል የጦር መሳሪያ የታጠቀ በሙሉ ለዘመቻው አገልግሎት እንዲውል ወስኗል።
"ማንኛውም የግል መሳሪያ የታጠቀ የክልሉ ነዋሪ በማንኛውም ምክንያት በሕልውና ዘመቻው ላይ የማይሳተፍ ከሆነ የታጠቀውን የግል መሳሪያ በአደራ ለመንግሥት እንዲያስረክብ ወይም እድሜው ለትግል ለደረሰ . . . ለሌላ ሰው በማስተላለፍ ለህልውና ዘመቻው አገልግሎት እንዲውል እንዲያደርግ" ብሏል ምክር ቤቱ።
የአማራ ክልል ምክር ቤት ባስተላለፈው አስቸኳይ ጥሪ በሁሉም የክልሉ ከተሞች ተፈጻሚ የሚሆን ሰዓት እላፊ አዋጅ አውጥቷል።
ምክር ቤቱ ፍቃድ ከሚሰጣቸው ተቋማት ውጪ በሁሉም ከተሞች ከምሽቱ 2፡00 በኋላ እንቅስቃሴ ማድረግ አይቻልም ብሏል።
ምክር ቤቱ በዚህ ትግል "በተለያየ መንገድ እንቅፋት በሚሆን ማንኛውም ሰው ወይም ቡድን ላይ በየደረጃው እየተወሰነ የጸጥታ አካሉ አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ" መወሰኑን ገልጿል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ “. . . ማንኛውም የክልሉ ነዋሪ በየአካባቢው ተደራጅቶ የአካባቢውን ፀጥታ እንዲጠብቅ፣ ፀጉረ ለውጦችንና ሰርጎ ገቦችን እንዲከታተልና ለሕግ አስከባሪ አካላት አሳልፎ እንዲሰጥና ለሕልውና ዘመቻው የበኩሉን ኃላፊነት ሁሉ ይወጣ” ብሏል።
ምክር ቤቱ እነዚህን አስገዳጅ ውሳኔዎች ዝርዝር አፈጻጸም በተመለከተ በክልል ደረጃ በተቋቋመው የዘመቻ መምሪያ በሚቀመጥ አሰራር የሚወሰን ይሆናል ብሏል።
በአማራ ክልል ውስጥ የሚገኙት የሰሜን ወሎ እና የደቡብ ወሎ አካባቢዎች ጦርነት እተካሄደ መሆኑ የተነገረ ሲሆን የህወሓት አማጺያን ደሴንና የኢንዱስትሪ ከተማዋን ኮምቦልቻን መቆጣጠራቸውን የገለጹ ቢሆንም የመንግሥት ኮሙኑኬሽም ጽህፈት ቤት በከተሞቹ ዙሪያ ውጊያ እተካሄደ ገልጿል።
በከተሞቹ ያለው የስልክ አገልግሎት በመቋረጡ ከተሞቹ ያሉበትን ሁኔታ ከገለልተኛ ወገን ለማረጋገጥ አዳጋች ሆኗል።












