ህወሓት ደሴን ይዣለሁ ቢልም መንግሥት ከተማዋ አሁንም በቁጥጥሬ ስር ናት አለ

የፎቶው ባለመብት, Dessie city communication/fb
በአማራ ክልል የደቡብ ወሎ ዞን ዋና ከተማ ከሆነችው የደሴ ከተማ የፌደራሉ ሠራዊት ማፈግፈጉንና የህወሓት ኃይሎች መግባታቸው መዘገቡን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት ከተማዋ አሁንም በቁጥጥሩ ስር መሆኗን ገለጸ።
ቢቢሲ ቅዳሜ ረፋድ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች የህወሓት አማፂያን ወደ ከተማው ሲገቡ መመልከታቸውንና የመንግሥት ኃይሎች ማፈግፈጋቸውን ገልፀዋል።
በተጨማሪም አማፂያኑ ወደ ሰኞ ገበያ፣ ተቋም እና ሳላይሽ አካባቢዎች ሲያመሩ እንደታዩና በከተማዋ ዳርቻ አካባቢ ተኩስ እንደሚሰማ ለቢቢሲ ገልፀው ነበር።
በደሴ ከተማ በአንዳንድ ቦታዎች ከትናንት አርብ ጀምሮ የኤሌትሪክ መቋረጥ የገጠመ ሲሆን ዛሬ ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ ጀምሮም ስልክ ተቋርጧል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት በኩል ባወጣው መግለጫ ውጊያ እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሶ "አሁንም ደሴና አካባቢዋ በመንግሥት የፀጥታ ኃይል ስር ናቸው" ብሏል።
ሮይተርስ የዜና ወኪል የአማጺያኑን ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳን ጠቅሶ የትግራይ ኃይሎች የመንግሥት ሠራዊትን ከደሴ ከተማ ገፍቶ በማስወጣት ከተማዋን መቆጣጠራቸው ካልተጠቀሰ ቦታ በሳተላይት ሰልክ እንደነገሩት ዘግቧል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የህወሓት ኃይሎች ሌሊቱን ሙሉ ደሴን ለመያዝ በተለያዩ መስመሮች ጥቃት ማካሄዳቸውን ጠቅሶ፣ በአካባቢው ያለው የመንግሥት የፀጥታ ሃይል ጥቃቱን መመከቱን እና የፀረ ማጥቃት እርምጃ መቀጠሉን በመግለጫው አመልክቷል።
የፈረንሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ ነዋሪዎችን ጠቅሶ ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ እንደዘገበው የኢትዮጵያ መንግሥት ኃይሎች ከትግራይ ክልል ጋር በሚዋሰነው የአማራ ክልል ውስጥ ከምትገኘው የደሴ ከተማ ማፈግፈጋቸውን የከተማዋ ነዋሪዎች እንደነገሩት ዘግቧል።
ጨምሮም ከባድ ውጊያ ከተካሄደ በኋላ በከተማዋ አንዳንድ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጡን ዜና ወኪሉ አመልክቷል።
የአማጺው የትግራይ ኃይሎች በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ በጦርነት የተፈናቀሉ ሰዎች የሚገኙባትን ቁልፍ ከተማ ደሴን መቆጣጠራቸውን ለሮይተርስ የዜና ወኪል የነገሩት አቶ ጌታቸው ረዳ ተዋጊዎቻቸው ወደ ኮምቦልቻ እያመሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ግን የህወሓት ኃይሎች ደሴን እንዳልያዙና አማጺው "ያለውን ኃይል ሁሉ አሰባስቦ በጦር ግንባር ያቃተውን በወሬ ለማግኘት አሁንም መፍጨርጨሩን ቀጥሏል" ሲል ዜናውን አጣጥሎታል።
ሮይተርስ እና ኤኤፍፒ አናገርናቸው ያሏቸው የደሴ ከተማ ነዋሪዎች የመከላከያ ሠራዊቱ ቅዳሜ ጠዋት ከከተማዋ በመውጣት ወደ ኮምቦልቻ ሲያመሩ መመልከታቸውን ተናግረዋል።
አንድ የትምህርት ቤት ዳይሬክተር እና አንድ ነዋሪ የፌደራሉ ሠራዊት አባላት ሲወጡ እንዳዩና በከተማዋ የኤሌክሪክ ኃይል ከአርብ ጀምሮ መቋረጡን እንዲሁም የህወሓት ኃይሎች መግባታቸው ሲነገር ቢሰሙም እንዳላዩ ለሮይተርስ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በደሴ ከተማና በአካባቢዋ ስላላው ሁኔታ ባወጣው መግለጫ ላይ በአገሪቱ ሠራዊት የሚመራው ኃይል የአማጺያኑን ጥቃት እየመከተ የፀረ ማጥቃት ዘመቻ እያካሄደ ነው ብሏል።
ከአዲስ አበባ 385 ኪሎ ሜትር የምትርቀው የደሴ ከተማ በአማራ ክልል ውስጥ ካሉ ትልልቅ ከተሞች መካከል አንዷ ስትሆን የደቡብ ወሎ ዞን ዋና ከተማ ናት።
በትግራይ ውስጥ የተቀሰቀሰው ጦርነት ወደ አማራ እና አፋር ክሎች ከተስፋፋ በኋላ ከሰሜን ወሎ በጦርነቱ የተፈናቀሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በከተማዋ ተጠልለው ይገኛሉ።
ከቀናት በፊት መንግሥት ሽብርተኛ የሚለው የህወሓት ሊቀመንበር ደብረጺዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ደሴ እና ኮምቦልቻን ለመቆጣጠር ውጊያ እየተካሄደ መሆኑን በመጥቀስ የከተማዎቹ ነዋሪዎች ከቤት እንዳይወጡ ተዋጊዎችም እጃቸውን እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበው ነበር።
ከሁለት ሳምንት በፊት መልሶ ያገረሸው ውጊያ በአማራና በአፋር ክልሎች እየተካሄደ ሲሆን በተለይ በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ውስጥ ከባድ ውጊያ እየተካሄደ ቀናት ተቆጥረዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይልም በትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀለ እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች የህወሓት ኃይሎች ይጠቀሙባቸዋል ያላቸው ስፍራዎች ላይ የአየር ጥቃት መፈጸሙ በተከታታይ ተዘግቧል።
በዚህም ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸውን የሆስፒታል ምንጮች እና የህወሓት ኃይሎች ቢገልጹም መንግሥት ግን ዒላማዎቹ የተመረጡና ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ በጥንቃቄ የተካሄዱ የአየር ጥቃቶች መሆኑን በመግለጽ አስተባብሏል።















