በደሴ ከተማ እና በዙሪያዋ ስላለው ሁኔታ ነዋሪዎች ምን ይላሉ?

ደሴ ከተማ

ባለፉት ቀናት የደቡብ ወሎ ዞን ዋና ከተማ በሆነችው ደሴ አቅራቢያ ባሉ ስፍራዎች በመንግሥት ኃይሎች እና በህወሓት አማጺያን መካከል የሚደረገው ጦርነት ቀጥሎ እየተካሄደ መሆኑን ነዋሪዎች ተናገሩ።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የደሴ ከተማ ነዋሪዎች በከተማዋ ቅርብ ርቀት ዙሪያ ጦርነት እየተካሄደ በመሆኑ ከባድ የጦር መሳሪያ ድምጽ እንደሚሰማ ተናግረዋል።

አንድ የደሴ ከተማ ነዋሪ፤ "ጦርነቱ የሚካሄድበት ቦታ ድረስ ሄጃለሁ። ከደሴ 7 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው። የውጊያው ስፍራ በኩታ በር አቅጣጫ ቦሩ የሚባል ቦታ ነው" በማለት ለቢቢሲ ተናግሯል።

ከሦስት እና አራት ቀናት በፊት አማጺያኑ "በውሸት 'እዚህ ቦታ ገቡ፣ እዚህ ቦታ ደረሱ' እየተባለ ብዙ ሰዎች ከተማዋን ለቀው ወጥተዋል። ከተማው ግን ሰላማዊ ነው" በማለት ይህ ነዋሪ ተናግሯል።

ሌሎች ነዋሪዎችም በቅርብ ርቀት እየተካሄደ ያለው ጦርነት ስጋት የፈጠራባቸው የከተማዋ ነዋሪዎች መኖራቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ባንኮችን ጨምሮ የንግድ ተቋማት አንዴ ተዘግተው ቆይተው አገልግሎት ለመስጠት ደግሞ እንደሚከፈቱ ተናግረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከትናንት በስቲያ ይሰማ የነበረው የከባድ ጦር መሳሪያ ድምጽ መቀነሱን ሌሎች ነዋሪዎች ዛሬ ሐሙስ ረፋድ ላይ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

እንደ ነዋሪዎቹ ከሆነ ምንም እንኳ ጦርነቱ በቅርብ ርቀት ላይ እየተካሄደ ቢሆንም ዛሬ እና ከጥቂት ቀደም ባሉት ቀናት በተሻለ ይሰማ የነበረው የከባድ ጦር መሳሪያ ድምጽ ቀንሷል።

በከተማዋ ውስጥና በዙሪያዋ ባሉ አካባቢዎች እንቅስቃሴ በሚያደርጉ ተሽከርካሪዎችና ግለሰቦች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን የሚናገሩት ነዋሪዎች ዛሬ ሐሙስ አስከ ረፋድ ድረስ እንደተመለከቱት ነዋሪው ላይ የመረጋጋት ስሜት እየተፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

"ከተማ ለቃችሁ አትውጡ"

ይህ በእንዲህ እንዳለ የህወሓት ሊቀ መንበር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) የደሴ እና የኮምቦልቻ ነዋሪዎች ከተማውን ጥለው እንዳይወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

ደብረጽዮን ትናንት ይህን መልዕክት ያስተላለፉት የህወሓት አማጽያን እና የፌደራሉ ኃይል ከክልል ኃይሎች ጋር ታግዞ በደሴ ከተማ ዙሪያ ከባድ ውጊያ እያደረጉ እንደሚገኝ በተገለጸበት ወቅት ነው።

ደብረጽዮን ለደሴ እና ኮምቦልቻ ነዋሪዎች "አትረበሹ ከተማ ለቃችሁ አትውጡ። ተረጋጉ እራሳችሁን ለምስቅልቅል አትዳርጉ ማለት እንፈልጋለን" ብለዋል።

"የትግራይ ሠራዊት በሕዝብ ላይ የሚፈጽመው ግፍ ቂም በቀል የለውም። ይልቁንስ በየአካባቢ ጉዳት እንዳይደርስባችሁ ተገቢውን ጥንቃቄ አድርጉ። . . . ከተማ ውስጥ ሆኖ ቤት ውስጥ ሆኖ የሚተኩስ እንዳይኖር ተገቢውን እርምጃ ውሰዱ" ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ጦርነቱ ለደሴ ቅርብ በሆኑ ስፍራዎች መካሄድ በጀመረበት ጊዜ ከነዋሪዎች መካከል ከተማዋ አየለቀቁ የወጡና ለመውጣት የሞከሩ ሰዎች እንደነበሩ ቢቢሲ ያናገራቸው ነዋሪዋሪች ገልጸዋል።

በዚህም ሳቢያ የትራንስፖርት ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩንና የከተማው አስተዳዳሪዎችም ነዋሪዎች ከተማዋን ለቀው እንዳይወጡ ጥሪ ሲየቀርቡ ቆይተዋል።

የህወሓት አማጺያን እንደ ላሊበለ እና ወልዲያ ያሉ የሰሜን ወሎ ከተሞችን ከተቆጣጠሩ በኋላ የደቡብ ወሎ ከተሞች የሆኑትን ደሴ እና ኮምቦልቻን ለመውረር ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል።

የህወሓት አማጺያን ደሴ እና ኮምቦልቻ ከተሞችን እንዳይቆጣጠሩ በርካታ የአካባቢው ወጣቶች ባለፉት ጥቂት ቀናት ወደ ጦርነቱ ግንባር እየዘመቱ ነው።

የደቡብ ወሎ ዞን ትልቋ ከተማ ደሴ ከ500 ሺህ በላይ ተፈናቀዮችን እያስተናገድች ትገኛለች። ነዋሪው ከሰሜን ወሎ እና ዋግ ኸምራ ተፈናቅሎ የመጣን ሕዝብ ተቀብሎ እያስተናገደ እንደሆነ ነዋሪዎች ጨምረው ተናግረዋል።

ጦርነት ከሚካሄድባቸው የወሎ አካባቢዎች ተፈናቅለው በደሴ ከተማ በትምህርት ቤቶችና በተለያዩ የመጠለያ ስፍራዎች የሚገኙ ሰዎችን የከተማው ነዋሪ እና የአካባቢው መስተዳደር የተለያዩ ድጋፍ እያደረጉላቸው መሆኑ ሲነገር ቆይቷል።

በደሴ ከተማ ያለውን ሁኔታ በተመለከተ እና ስለተፈናቃዮቹ ዝርዝር መረጃ ከከተማዋ እና ከዞኑ አስተዳደር ኃላፊዎች መረጃ ለማግኘት ያደርግነው ጥረት አልተሳካም።