ከሰሜን ወሎ አካባቢዎች ተፈናቅለው ደሴ ከተማ የገቡ ተፈናቃዮች ሁኔታ

ደሴ ከተማ

ነዋሪነታቸው ራያ አላማጣ የነበረና ስማቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉ እናት ከሦስት ልጆቻቸው ጋር ከመኖሪያ ቀያቸው ከተፈናቀሉ አራት ሳምንታት ተቆጥረዋል።

የፌደራል መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ሠራዊቱን ከትግራይ ካስወጣ በኋላ በአላማጣ በኩል በተከፈተ ጦርነት ምክንያት ቀያቸውን ለቀው መውጣታቸውን ይናገራሉ።

ያኔ ከአላማጣ ወደ ቆቦ ነበር ሄደው ከዘመድ ጋር የተጠለሉት።

ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆዩ ነበር ዳግም ከቆቦ ወደ ወልዲያ የተፈናቀሉት። ወልዲያ አካባቢ ባለው የጸጥታ ስጋትም ወደ ደሴ ከተማ መሄዳቸውን ይናገራሉ።

እነዚህ ቦታዎች ለመድረስ የትራንስፖርት ችግር እንደነበር ያስታወሱት እኝህ እናት፤ የቻሉትን በመኪና ያልሆነላቸውን በእግራቸው እያቆራረጡ ደሴ እንደገቡ ገልጸዋል።

ከቤታቸው የወጡት ማቄን ጨርቄን ሳይሉ ነው። በእጃቸው ቤሳ ቤስቲን የለም።

ባለፉበት ሁሉ የከባድ መሣሪያ ተኩስ ስለነበር በሁኔታው ህጻናት ልጆቻቸው መደናገጣቸውንና አሁንም ድረስ ሌሊት እንደሚቃዡ ይናገራሉ።

"እንግዲህ ፈጣሪ ያመጣብንን እርሱ መፍትሔ ይስጠን እንጂ ሌላ ምን ይባላል? ከአጠገባችን እንደ ቀልድ የተለዩን ወንድሞቻችን፣ ጎረቤቶቻችንና ወዳጆቻችን አሉ። እኛ ተርፈን እዚህ ደርሰናል" ይላሉ።

እኝህ እናት በደሴ ከተማ በሚገኘው ዳውዶ ትምህርት ቤት ተጠልለው የዕለት እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

አዲሱ በላይ ነዋሪነቱ በወልዲያ ከተማ ቢሆንም ሰሞኑን በተፈጠረው ችግር ምክንያት ተፈናቅለው ደሴ ከገቡት መካከል አንዱ ነው።

ቆቦ ይኖሩ የነበሩ ቤተሰቦቹም ከቆቦ ተፈናቅለው ደሴ ከገቡ ሳምንት አልፏቸዋል።

ከአንድ ወር በፊት እንደገና በተቀሰቀሰው የራያ አካባቢ ግጭት ከባላ፣ ኮረም፣ አላማጣ፣ ዋጃ እና ጥሙጋ በርካታ ሰው ተፈናቅሎ ወልዲያ ከተማ ተጠልለው ነበር።

ከሦስት ሳምንት በፊት ደግሞ ጦርነቱ ወደ ቆቦ ሲስፋፋ የቆቦ እና አካባቢው ነዋሪዎች 50 ኪሎ ሜትር በእግር ተጉዘው ወልዲያ ገብተዋል።

በከተማው ከፍተኛ የሆነ ተፈናቃይ በመኖሩ ምግብ፣ መጠጥ እና መጠለያ እስከማጣት የደረሰ ችግር እንደነበር አዲሱ ይናገራል።

ግጭቱ ከራያ ወደ ወልዲያ ዙሪያ ሲስፋፋ ደግሞ የወልዲያን ነዋሪ ጨምሮ ከራያ አላማጣ፣ ከኮረም፣ ከራያ ባላ እና ከራያ ቆቦ የመጡ ተፈናቃዮችን ጨምሮ ወደ ደሴ አቅንተዋል።

ምንም እንኳን ወደ ደሴ ለመሄድ የትራንስፖርት አማራጭ ቢኖርም ከ100 ብር የማይበልጥ የነበረው ታሪፍ ከ500 እስከ 1000 ብር ስለገባ ፈተና ሆኖ እንደነበር አዲሱ ያስታውሳል።

በደሴ እና ወልዲያ መካከል ባሉ አካባቢዎች ግጭቱ ሲስፋፋ በትራንስፖርት የመሄድ አማራጭም ጠፍቶ ነበር ይላል።

በዚህ ጊዜ ጋራ እና ሸንተረሩን እያቆራረጠ ህጻናት ልጆቹን ይዞ ደሴ መግባቱን ይናገራል።

አንዳንድ የሰሜን ወሎ አካባቢዎች የጦርነት ቀጠና በመሆናቸው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ተፈናቅሎ ደሴ ከተማ ገብቷል።

በዚህም ምክንያት ደሴ ከተማ ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የተፈናቀለ ሕዝብ አለ።

ይህንን ለማስተናገድም የከተማ አስተዳደሩ አራት ትምህርት ቤቶችን ለተፈናቃዮቹ ጊዜያዊ መጠለያነት አዘጋጅቷል። እርዳታ ለማድረግም ምዝገባ እየተደረገ መሆኑን አዲሱ ተናግሯል።

ረቡዕ እለት ከሰሜን ወሎ አካባቢዎች የተፈናቀሉ በርከት ያሉ አካባቢዎች ሰዎች ደሴ መግባታቸውን የደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት ለቢቢሲ ገልጿል።

የጽ/ቤቱ ኃላፊ አቶ መሳይ ማሩ እንደተናገሩት ተፈናቃዮቹ አንዳንዶቹ ቤተ ዘመድ ጋር እንዲሁም መኖሪያ ቤትና ሆቴል ተከራይተው ተቀምጠዋል።

ይህንን ማድረግ ላልቻሉትና አቅም ለሌላቸው ደግሞ ትምህርት ቤቶችን ለጊዜያዊ ማረፊያነት አመቻችተው እዚያ እንዲያርፉ ለማድረግ ጥረት መደረጉን አቶ መሳይ ተናግረዋል።

ኃላፊው ከክልሉ እና ከፌደራል ብሔራዊ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ጋር በመሆኑ የዕለት እርዳታ ማቅረብ ተጀምሯል ብለዋል።

"የተፈናቃዮች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ነው" ያሉት ኃላፊው፤ አሁን ላይ ያለውን የተፈናቃይ ቁጥር በውል መግለጽ እንደሚቸገሩ ተናግረዋል።

በትክክል ምን ያህል ተፈናቃይ እንዳለ በእድሜና በፆታ ለማጠናቀር እየሰሩ መሆናቸውንም አቶ መሳይ አክለዋል።

ከቀናት በፊት ያነጋገርናቸው የደሴ ከተማ ከንቲባ አቶ አበበ ገ/መስቀል የተፈናቃዮቹን ቁጥር በትክክል ማወቅ ባይቻልም ከ10 እስከ 15ሺህ የሚገመት ሕዝብ እየገባ መሆኑን ተናግረው ነበር።

ደቡብ ወሎ ዞን ከዚህ ቀደም በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በኦሮሚያ ክልል የተፈፀሙ ጥቃቶችን ተከትሎ የተፈናቀሉ ሰዎችን እያስተናገደ መሆኑን ያስታወሱት አቶ መሳይ ፤ የምግብ አቅርቦት ቢኖርም አልባሳትና ምግብ ነክ ያልሆኑ አቅርቦቶች እጥረት መኖሩን ተናግረዋል።

"ሰው ራቁቱን ነው የመጣው። የያዘው ነገር የለም። ቁጥሩ እየጨመረ ሲሄድ የምግብ አቅርቦት ችግርም ሊኖር ይችላል" ብለዋል ኃላፊው።

በዞኑ ከዚህ ቀደም ከተለያዩ አካባቢዎች ጥቃት ሸሽተው የወጡ ከ11ሺህ በላይ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽ/ቤት የቅድሚያ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ቡድን መሪ አቶ መሐመድ ሰይድ ለቢቢሲ መግለጻቸው ይታወሳል።

የፌደራል መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ሠራዊቱን ከትግራይ ካስወጣ በኋላ የህወሓት አማጺያን ወደ አማራ ክልል እና አፋር ክልል በመግባት ጦርነት ከፍተዋል።

ይህንንም ተከትሎ ከሁለቱም ክልሎች ከ300 ሺህ በላይ ሰዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸው ተገልጿል።

ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ፕሬሴክሬታሪ ቢልለኔ ስዩም እነዚህ ተፈናቃዮች ሰብዓዊ እርዳታ ቢያስፈልጋቸውም የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትኩረት ተነፍጓቸዋል ሲሉ ወቅሰዋል።

ይሁን እንጅ የፌደራል መንግሥት ያለውን እርዳታ እያቀረበ ሲሆን ተጨማሪ ድጋፎችን ለማድረግ ከዓለም ምግብ ፕሮግራም ጋር እየተነጋጋረ ነው ብለዋል።