በጦርነት ምክንያት በአማራ ክልል ከ200 ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸው ተገለጸ

አቶ ግዛቸው ሙሉነህ

የፎቶው ባለመብት, AMC

የምስሉ መግለጫ, አቶ ግዛቸው ሙሉነህ

የአማራ ክልል ከትግራይ ጋር በሚዋሰንባቸው አካባቢዎች በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት ከሁለት መቶ ሺህ በላይ ሰዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን ክልሉ አስታወቀ።

የአማራ ክልል የመንግሥት ጉዳዮች ኮምዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በተለያዩ አካባቢዎች የህወሓት ኃይሎች የሰነዘሩትን ጥቃት ተከትሎ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለመፈናቀል የተዳረጉት።

የትግራይ ኃይሎች በደቡብና በምዕራብ ወደ ሚገኙ የአማራ አጎራባች አካባቢዎች በመግፋታቸው 200 ሺህ ሰዎች ከአማራ ክልል 54 ሺህ ደግሞ ከአፋር ክልል መፈናቀላቸውን ሰሞኑን በኢትዮጵያ ጉብኝት ላይ የነበሩትን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ኃላፊ የሆኑትን ማርቲን ግሪፊትስን ጠቅሶ ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

የአማራ ኮምዩኒኬሽን ኃላፊው ለቢቢሲ እንደተናገሩት "በራያ በኩል ብቻ ከ150 ሺህ በላይ የተፈናቀሉ ሲሆን ይህ ከሌሎች አካባቢዎች ጋር ተደምሮ ከ200 ሺህ በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል" ብለዋል።

ኃላፊው ጨምውም ለተፈናቀሉት ሰዎች አስፈላጊውን ድጋፍ ለማቅረብ የአማራ ክልል ከፌደራል መንግሥት ጋር በመተባበር ጥረት እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

በቅርቡ ከተከሰተው ችግር ባሻገር በተለያዩ አካባቢዎች በሚፈጠሩ ግጭቶች ሳቢያ ለመፈናቀል የተዳረጉ ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በክልሉ እንደሚገኙና ከፍተኛ መጠን ያለው ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው አቶ ግዛቸው ገልጸዋል።

ተፈናቃዮቹን ለመደገፍ ከምግብ አንጻር "በወር 150 ሺህ ኩንታል ያስፈልጋል። አልፎ አልፎ ከምናገኛቸው ጥቃቅን ድጋፎች በስተቀር አስፈላጊው ድጋፍን በሙሉ ክልሉ በራሱ እየሸፈነ ነው" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ካርታ

ሰሞኑን ከሁመራ አካባቢ በተከዜ ወንዝ አማካይነት ሱዳን ውስጥ ተገኝተዋል ስለተባሉት አስከሬኖች ጉዳይ የተጠየቁት የሞምዩኒኬሽን ኃላፊው በሰጡት ምላሽ "የአማራ ልዩ ኃይልም ሆነ የፋኖ አባላት እንደዚህ አይነት አጽያፊ ተግባር አይፈጽሙም" ሲሉ ተናግረዋል።

"ህወሓት ከሌሎች አካባቢዎች አስከሬኖችን በማምጣት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የተዛባ መረጃ በመስጠት የተዛባ ውሳኔ ላይ እንዲደርስ ለማድረግ የተፈጠረ የበሬ ወለደ ድራማ ነው።"

አቶ ግዛቸው ጨምረውም ይህንን ዕቅድ ቀድመው እንደተገነዘቡና ቡድኑ "አስከሬን ጭኖ ሲወስድ የሚሰራው ቁማር እንዳለ ለማስገንዘብ ሞክረናል፣ እየሆነ ያለውም ያው ነው። አስፈላጊ ከሆነ ቦታው ድረስ በመሄድ ማጣራት ይቻላል" በማለት "ስለዚህ በተቀነባበረ ሁኔታ ህወሓት የሚሰራው እንጂ እንደ እኛ ያለ ጨዋ ሕዝብ የሚፈጽመው አይደለም።" ብለዋል።

በጥይት የቆሰሉና እጃቸው ከኋላ የተጠፈሩ አስከሬኖች ኢትዮጵያ በትግራይ በኩል በምትዋሰንበት ተከዜ ወንዝ ላይ መገኘቱን አንድ ዶክተር ለቢቢሲ ተናግረዋል። ዶክተር ቴዎድሮስ ተፈራና ሌሎች የአይን እማኞች እንደሚናገሩት ሟቾቹ ከትግራይ ክልል እንደመጡ ነው።

የኮምዩኒኬሽን ኃላፊው በተጨማሪም በኢትዮጵያ በጉብኝት ላይ ያሉት የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ዩኤስ ኤይድ ኃላፊ ሳማንታ ፓወር የህወሓት አማጺያን ከአማራ እና ከአፋር ክልሎች እንዲወጡ እንዲሁም የአማራ ኃይሎች ከምዕራብ ትግራይ እንዲወጡ በተመለከተ ለቢቢሲ ሃሳባቸውን ገልጸዋል።

"የህወሓት ኃይል ከአፋርና ከአማራ ክልሎች ይውጣ ማለቱን እንደግፋለን። ከዚያ ውጪ ግን የአማራ ልዩ ኃይል ከምዕራብ ትግራይ ይውጣ የሚለው ውሃ የማያነሳ ነው። እኛ ምዕራብ ትግራይ የሚባል አካባቢ አልያዝንም" ብለዋል።

ጨምረውም "እኛ ያለነው በጉልበት ተወስዶ ከነበረው ወልቃይት ጠገዴ ነው። ይህ ደግሞ ላለፉት ሰላሳ ዓመታት ሕዝቡ ማንነቱን ተገፎና ተረግጦ ስለነበረ አሁን በራሱ ትግል ነጻነቱን ተጎናጽፏል። ሕዝቡ ባደረገው ትግል አሁን ድጋሚ የወረራ አደጋ ቢደቀንበትም ነጻነቱን ተቀዳጅቷል" ሲሉ መልሰዋል አቶ ግዛቸው።

የይገባኛል ጥያቄ ሲነሳባቸው የቆዩት በአማራና በትግራይ ክልሎች ምሥራቃዊና ምዕራባዊ ክፍሎች ውስጥ የሚገኙት አካባቢዎች ባለፈው ጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ በህወሓት ኃይሎችና በፌደራል መንግሥቱ መካከል ወታደራዊ ግጭት በተቀሰቀሰበት ጊዜ በአማራ ልዩ ኃይል ቁጥጥር ስር መግባታቸው ይታወሳል።

ባለፉት ሳምንታት በእነዚህ አካባቢዎች ጦርነቶች የተካሄዱ ሲሆን በርካታ ቁጥር ያላቸው ነዋሪዎች ለደኅንነታቸው በመስጋት ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸው እየተነገረ ነው።

ከአማራ ክልል የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር በአሁኑ ጊዜ ከ200 ሺህ በላይ ሲሆን በተመሳሳይ በአፋር ክልልም በጦርነቱ ሳቢያ ከ70 ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።