ደሴ ከተማ ፡ ተፈናቃዮች የተጠለሉባቸውን ትምህርት ቤቶች ለማደስ ከ21 ሚሊየን ብር በላይ ያስፈልጋል ተባለ

ከትምህርት ቤቶች በተጨማሪም በቆርቆሮ መጋዘን ውስጥ የተጠለሉ ሴቶችና ሕጻናት አሉ

የፎቶው ባለመብት, Melaku Ambaw

የምስሉ መግለጫ, ከትምህርት ቤቶች በተጨማሪም በቆርቆሮ መጋዘን ውስጥ የተጠለሉ ሴቶችና ሕጻናት አሉ

ከ300 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች በሚገኙባት ደሴ ከተማ 22 ትምህርት ቤቶች የተፈናቃዮች መጠለያ በመሆናቸው በወቅቱ ትምህርት ማስጀመር አለመቻሉን የከተማው ትምህርት መምሪያ ለቢቢሲ ገለጸ።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ እያሱ ዘውዱ ተፈናቃዮች የተጠለሉባቸው አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች መሠረተ ልማታቸው በመውደሙ ትምህርት ቤቶቹን ለመማር ማስተማር ሥራ ለማዘጋጀት ከፍተኛ ሥራ እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።

ኃላፊው "በትምህርት ቤቶቹ የውሃና የመብራት ዝርጋታዎች ወድመዋል፤ ወንበሮች፣ መስኮቶች፣ በሮች ተሰባብረዋል፣ መጸዳጃ ቤቶች ተደርምሰዋል፤ ክፍሎቹ ምግብ ማብሰያ በመሆናቸውም ቀለማቸው ተለውጧል፤ አጥራቸውም ቢሆን ተሰባብሯል" ብለዋል።

በዚህ ላይ በተካሄደ ጥናትም ትምህርት ቤቶቹን ወደ ቀደመው ሁኔታቸው ለመመለስ ከ21 ሚሊየን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ አቶ እያሱ ገልጸዋል።

ባለፈው ሳምንት ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) ኢትዮጵያ ውስጥ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ 1.8 ሚሊዮን ሰዎች መጠለያ ለማቅረብ 21.1 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው መግለፁ ይታወሳል።

የደሴ ከተማን ሳይጨምር በዚህ ዓመት በደቡብ ወሎ ዞን 538 ሺህ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን ለማስተማር ቢታቀድም ትምህርት የጀመሩት ግን ቁጥሩ በግማሽ አንሶ 238 ሺህ 310 የሚሆኑት ብቻ መሆናቸውን የዞኑ የትምህርት ባለሥልጣን፣ አቶ ደረጀ አማረ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በተጨማሪም በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትም በዞኑ 148 ሺህ 745 ተማሪዎችን ለማስተማር እቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም ትምህርት የጀመሩት ሲሶ ያህሉ 50 ሺህ ስልሳ አምስት ተማሪዎች መሆናቸውን ባለሥልጣኑ ተናግረዋል።

ከወራት በፊት መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም አውጆ ሠራዊቱን ከትግራይ ማስወጣቱን ተከትሎ፣ የህወሓት አማጺያን ወደ አፋርና አማራ ክልል በመግባት ጦርነት ከፍተዋል። አሁንም ሰሜን ወሎ ዞን፣ ዋግ ኸምራ ብሔረሰብ አስተዳደርና አንዳንድ የደቡብ ወሎ ዞን አካባቢዎች ከአማጺያኑ ቁጥጥር አልወጡም።

ባለፈው ዓመት የህወሓት አማጺያን በትግራይ በነበረው የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መፈፀማቸውን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ጦርነት ለአስር ሺዎች ሞት እና ለሚሊዮኖች መፈናቀል ምክንያት ሆኗል።

ትምህርት ቤቶች መጠለያ በሆኑባቸው ከተሞች ትምህርት መቼ ይጀመራል?

በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ በአብዛኛው የአገሪቷ ክፍል የ2014 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ተጀምሯል።

ይሁን እንጂ የጸጥታ ችግር ባለባቸውና በርካታ ተፈናቃዮችን እያስተናገዱ ባሉ አካባቢዎች ትምህርት ቤቶች ጊዜያዊ መጠለያ በመሆናቸው ትምህርት አልተጀመረም።

ከእነዚህ መካከል አንዷ የደሴ ከተማ ናት።

የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ እያሱ፣ በከተማዋ ትምህርት ለማስጀመር 'በሌላ አካላት የተያዙ' [በሚሊሻ እና መከላከያ ማረፊያነት] አስር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተለቅቀው በአምስቱ ጥቅምት1/ 2014 ዓ.ም፤ ለ2013 ዓ.ም 12ኛ ክፍል ተፈታኞች የክለሳ ትምህርት ተጀምሯል ብለዋል።

የ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ተፈታኞችን ትምህርትም ጥቅምት 8/2014 ዓ.ም ለመጀመር ክፍሎችን የማጽዳት እና ወንበሮችን የማደስ ሥራ መጀመሩን ኃላፊው ገልጸዋል።

በከተማዋ 12 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መኖሩን የገለፁት ኃላፊው፤ ከተለቀቁት ውጭ ባሉት ሁለተኛ እና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ትምህርት ለማስጀመርም ለተፈናቃዮች ጊዜያዊ መጠለያ ለማዘጋጀት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

"ገራዶ ላይ 25 ድንኳን ተተክሏል። የግልና የአነስተኛና ጥቃቅን ሼድ፣ ስምንት የግል ሼዶችን ለጊዜያዊ መጠለያነት ለመጠቀም ኮሚቴ ተዋቅሮ እየሠራን ነው" ብለዋል።

አቶ እያሱ አክለውም አነስተኛ እና ጥቃቅን የማይሰሩባቸውንና በዓለም ባንክ የተሰሩትን ሸዶች ቁልፍ መረከባቸውን ተናግረው፤ መጠለያው ለተፈናቃዮቹ ከተዘጋጀ በኋላ ጥቅምት 15 2014 ዓ.ም ትምህርት ለመጀመር ማቀዳቸውን ገልጸዋል።

"ይህ የሚሆነው ግን የጊዜያዊ መጠለያ ግንባታው ሲሳካ ነው" ሲሉ ኃላፊው አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

በትምህርት ቤቶቹ ከ20 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች መኖራቸውን የገለጹት የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ፤ ርብርብ ካልተደረገ በስተቀር እየተዘጋጀ ያለው መጠለያም በቂ አለመሆኑን አመልክተዋል።

እንደ አቶ እያሱ ከሆነ በደሴ ከተማ በዚህ ዓመት 57 ሺህ 500 የሚሆኑ ተማሪዎችን ለማስተማር የታቀደ ሲሆን፣ ተፈናቃይ የሆኑ 800 ተማሪዎችም ለመማር ተመዝግበዋል።

ትምህርት ቤት ሲከፈትም ከታቀደው በላይ በርካታ ተማሪዎች ይመጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅና ሊገጥም የሚችለውን ተግዳሮት ለመፍታት እያሰቡ መሆናቸውንም አስረድተዋል።

" የሰው ኃይልና የመማሪያ ክፍል እጥረት ለመፍታት ድንኳንም ሆነ ቢሮዎችን ለመማሪያ ከፍል ለማዋል፤ የመምህራን እጥረትንም ለመፍታት ተፈናቃይ መምህራንን እንደ ሁኔታው ጋብዘን እንዲያስተምሩ እናደርጋለን" ብለዋል ኃላፊው።

በደቡብ ወሎ ዞን በምትገኘው ኮምቦልቻ ከተማም ከ5 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች በ12 የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ተጠልለው እንደሚገኙ የዞኑ ትምህርት መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ደረጀ አማረ አስታውቀዋል።

አቶ ደረጀ እንዳሉት በእነዚህ ትምህርት ቤቶችም ሆነ በከተማዋ ባሉ የግል ትምህርት ቤቶች ትምህርት አልተጀመረም።

ከዚህ ባሻገር በጦርነቱ ትምህርት ቤቶች ከወደሙባቸው ወረባቦ [ 2 ትምህርት ቤቶች] እና ተሁለደሬ [ አንድ ትምህርት ቤት] እንዲሁም የጸጥታ ችግር ካለባቸው ደላንታና የተወሰኑ አምባሰል ወረዳ አካባቢዎች በስተቀር በሌሎቹ የዞኑ ወረዳዎች ለትምህርት እንቅፋት የሆነ ችግር አለማጋጠሙን አቶ ደረጀ ተናግረዋል።

በመሆኑም በጦርነቱ የወደሙትን ለመጠገን እና በኮምቦልቻ ከተማ በተፈናቃዮች የተያዙ ትምህርት ቤቶችን አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ለማቋቋም እየተሠራ መሆኑን ምክትል ኃላፊው አክለዋል።

ነዋሪዎችና ወላጆች ምን ይላሉ?

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ወላጆች በአገሪቷ ያለው ጦርነትና አለመረጋጋት እንዲሁም ልጆቻቸው ትምህርት ባለመጀመራቸው ሥነ ልቦናቸውና የወደፊት ተስፋቸው ላይ ጫና ተፈጥሯል ብለዋል።

መላኩ አምባው የደሴ ከተማ ነዋሪና የሁለት ልጆች አባት ናቸው። የ7ኛ እና የ2ኛ ክፍል ተማሪ ልጆች አላቸው።

"የሚያሳስበኝ የልጆቼ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ የተፈናቃይ ልጆችም ጭምር ነው፤ ልጆቼ እየተማሩ ተፈናቃዮች ደግሞ ሲቸገሩ ማየት ለእኔ ራስ ምታት ነው" ይላሉ።

ልጆችም ዕለት በዕለት በሚያዩት ውጥረት ሳቢያ ለመማር ያላቸው ፍላጎት አነስተኛ ነው ብለዋል ነዋሪው።

" ልጆች ጥሩ ያልሆነ ሥነ ልቦና ውስጥ ናቸው፤ የእኔ ትንሹ ልጄ በአንድ ወቅት ሚሊሻዎች በደስታ ከተማ ውስጥ ጥይት ሲተኩሱ ሰምቶ 'ትምህርት ቤት አልሄድም፤ ይገሉኛል' ይላል በማለትም የልጆቹን አዕምሮ ለትምህርት ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግም ነዋሪው ተናግረዋል።

ሌላኛዋ ነዋሪ ሊሻን አሰጋኸኝ ዘንድሮ 12ኛ ክፍል ተፈታኝ የሆነ ተማሪ ልጅ አላቸው።

ወ/ሮ ሊሻን "የልጆቻችን ሞራል ተጎድቷል፤ የማንበብ፣ የማጥናት ሁኔታቸው ተዛብቷል፤ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ይታይባቸዋል፤ ከልጄም የተረዳሁት ያለው ሁኔታ እንደሚያሳስባቸው ነው" ብለዋል።

መምህር አካለ ወልድ ትምህርት ቤት የሚማረው ልጃቸው በጥቅምት ወር ማትሪክ ተፈታኝ በመሆኑ ሰኞ እለት ትምህርት እንደጀመረ ወ/ሮ ሊሻን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ አዕምሯቸው ተረጋግቶ፣ ተምረው፣ ውጤት ያመጣሉ ብዬ አላስብም ብለዋል።

ነዋሪዎቹ ላጋጠመው ችግር መፍትሔ ይሆናል ያሉትን ጠቁመዋል።

የመጀመሪያው ጦርነቱ በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ተፈናቃዮች ወደቀያቸው እንዲመለሱ ማድረግ የሚል ነው። ይህ ግን በአጭር ጊዜ ይሳካል የሚል እምነት የላቸውም።

በመሆኑም ሁሉም ተረባርቦ ለእነዚህ ሰዎች ጊዜያዊ መጠለያ መገንባትና ወደዚያ ማዛወርን እንደ አማራጭ ተመልክተውታል።

ይሁን እንጂ "እነዚህ በጦርነቱ የተጎዱ ወገኖቻችን ያልተገባ ቦታ ላይ እንዲታጎሩ አንፈልግም ፤ ውሃ መብራትና ሌሎች መሠረተ ልማቶች የተሟሉበት መሆን አለበት" ይላሉ ነዋሪዎቹ።

ይህ ውሳኔያቸው የተፈናቀሉ ልጆችም ትምህርት ቤት ገብተው እንዲማሩ፤ ሌላውንም ትውልድ ከችግር ለመታደግ ከማሰብ የመነጨ ነው።

ነዋሪዎቹ ጉዳዩ በመንግሥትና በእርዳታ ድርጅቶች ትኩረት እንዲሰጠውም ጠይቀዋል።

ትምህርት ቤቶቹ በምን ሁኔታ ላይ ነው ያሉት?

የደሴ ከተማ ነዋሪው አቶ መላኩ ትምህርት ቤቶቹ ለረዥም ጊዜ በተፈናቃይ ስለተያዙ መሠረተ ልማታቸውና ቁሳቁሳቸው መውደማቸውንና መበላሸታቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም ልጆችን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ ትምህርት ቤቶቹ ለመማር ማስተማር ምን ያህል ምቹና ንጹህ ናቸው የሚለውም በጤና ባለሙያዎች መረጋገጥ እንዳለበት ተናግረዋል።

የከተማው ትምህርት መምሪያ ኃላፊም ነዋሪው ያነሱት ስጋት ትክክል መሆኑን ገልጸው፤ "ትምህርት ቤቶቹ የውሃና የመብራት ዝርጋታቸው ተበላሽተዋል፤ ሽንት ቤቶች ተደርምሰዋል፤ ክፍሎች ማብሰያ ሆነዋል፤ አጥራቸው ፈርሶ ተማግዷል፤ ወንበሮች ብሎናቸው ተፈትቷል፤ ተሰባብረዋል፤ ቀለማቸው ተጎሳቁሏል፤ ብዙ ነገሮች ጎድለዋቸዋል" ሲሉ በትምህርት ቤቶቹ ላይ የደረሰውን ጉዳት አረጋግጠዋል።

በመሆኑም ተፈናቃዮቹ ጊዜያዊ መጠለያ ካገኙ በኋላ ትምህር ቤቶቹን ለማጽዳትና ለመጠገን እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

line

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ጌታቸው ቢያዝን በክልሉ ከ1.5 ሚሊየን በላይ ተማሪዎች ክትምህርት ገበታቸው እንደቀሩ ለአሜሪካ ድምጽ ተናግረዋል።

በጦርነቱ ምክንያትም 277 ትምህርት ቤቶች መውደማቸውን፤ ከ1300 በላይ ትምህርት ቤቶች ላይ ደግሞ በከፊል ጉዳት መድረሱን ምክትል ኃላፊው ገልጸዋል።

አቶ ጌታቸው ተፈናቅለው የሚገኙ ተማሪዎች ባሉበት አካባቢ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲመዘገቡ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑንም አክለዋል።