ራያ ቆቦ አጋምሳ ከተባለው ስፍራ አቅራቢያ የተከሰተው ምንድን ነው?

በትግራይ ክልል ውስጥ ተቀስቅሶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች በተስፋፋው ጦርነት ውስጥ ከባድ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን ከተለያዩ ወገኖች የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ። ለዚህ ደግሞ በጦርነቱ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም ወገኖች ተጠያቂ መሆናቸውን ይነገራል።
ጦርነቱ ከትግራይ ክልል ወጥቶ ወደ አማራ ክልል ከተስፋፋ በኋላ 'ዘ ቴሌግራፍ' የተባለው ጋዜጣ አማጺያን በሐምሌ ወር መጨረሻ ላይ አማራ ክልል ውስጥ ቆቦ ውስጥ አጋምሳ በሚባለው አካባቢ በአንድ ቀበሌ ላይ በፈጸሙት የጅምላ ጥቃት ከባድ ጉዳት መድረሱን ዘግቦ ነበር።
ጋዜጣው እንዳለው በጥቃቱ የከባድ መሳሪያ ድብደባ መፈጸሙንና በርካታ መኖሪያ ቤቶችም ሆን ተብለው በእሳት እንዲቃጠሉ መደረጋቸውን ዘግቧል።
ዘገባውን ተከትሎ ራሱን "የትግራይ ብሔራዊ መንግሥት" ብሎ የሚጠራ አካል አማጺያኑ ጥቃቱን አለመፈፀማቸውን ያስተባበለ ሲሆን በአካባቢው በሰላማዊ ሰዎች ላይ ተፈጽመዋል በተባሉ ጥቃቶች ዙሪያ ገለልተኛ ማጣራት እንዲደረግ ጠይቋል።
ቢቢሲ ስለ ክስተቱ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት ጥረት አድርጎ በጥቃቱ ወቅት በስፍራው የነበሩና አሁን ከአካባቢው ርቀው የሚገኙ እንዲሁም ጉዳት ደርሶባቸው በህክምና ላይ የሚገኙ ነዋሪዎችን አናግሯል።

በአማራ ክልል በሚገኘው ቆቦ፣ ከሚገኙ ከአርባ በላይ የገጠር ቀበሌዎች መካከል አንዷ የሆነችው ወርቄ ገበያ በጥቃቱ ከባድ ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል ናት።
ከወረዳው ዋና ከተማ ቆቦ በስተደቡብ ምሥራቅ አቅጣጫ የምትገኘው ወርቄ ገበያ ቀበሌ፣ በስተምዕራብ ሮቢት እና ጎብዬ የተሰኙት ታዳጊ ከተሞች የሚያዋስኗት ስትሆን፣ በስተምስራቅ በኩል ደግሞ ከአፋር ክልል ጋር ትዋሰናለች።
የቀበሌዋ ነዋሪዎቿ ከፊል አርብቶ አደር ናቸው።
በቀበሌዋ አጋምሳ ከተማ አቅራቢያ በሐምሌ ወር መጨረሻ አካባቢ በህወሓት ታጣቂዎች ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ በአካባቢው የስልክ ግንኙነት በመቋረጡ ክስተቱን ለማወቅ አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል።
ነገር ግን ጥቃቱ ሲፈጸም በስፍራው የነበሩና ክስተቱን ተከትሎ አካባቢውን ለቅቀው በመውጣት በሌሎች ስፋራዎች የሚገኙ ነዋሪዎችን ቢቢሲ አግኝቶ አናግሯል።
አቶ አደም ሁሴን በወርቄ ገበያ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ በሐምሌ መጨረሻ ላይ የህወሓት ታጣቂዎች ወደ ቀበሌያቸው በመምጣት ጥቃት በመሰንዘራቸው ከጠዋቱ 12፡00 ጀምሮ ለመከላከል ተኩስ መግጠማቸውን ይናገራሉ።
በወቅቱ እርሳቸውና ሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች ባደረጉት መከላከል አማጺያኑ አልፈው በመግባት አካባቢውን ለመቆጣጠር ያደረጉት ጥረት ስላልተሳካ "ራሳቸው ቦታ ይዘው ይታኮሱበት የነበረውን መንደር በከባድ መሳሪያ ደብድበው አቃጥለውታል" ይላሉ።
ይህ የሆነው ሰኞ ቀን ሐምሌ 26/2013 ከቀኑ ሰባት ሰዓት አካባቢ መሆኑን የሚናገሩት አቶ አደም፣ በተኩስ ልውውጡ መካከል ጉዳት ደርሶባቸው ከቦታው ለቅቀው መውጣታቸውን ይናገራሉ።
ሌላኛው በወቅቱ ከህወሓት ኃይሎች ጋር የመከላከል ፍልሚያ ውስጥ ገብተው ከነበሩት የአካባቢው ነዋሪዎች መካከል አንዱ አቶ ነጋ ደግሞ "41 ቤቶች ሲቃጠሉ እዚያው በቦታው ሆኜ ተመልክቻለሁ" ብለዋል።
አማጺያኑ ቤቶቹን ያቃጠሏቸው "እኛ ባደረግነው የመከላከል ጦርነት አልፈው መግባት ስላልቻሉ ተናድደው ነው" የሚሉት አቶ ነጋ፣ በቤቶቹ ውስጥ ምን ያክል ሰው መኖሩን እንደማያውቁ ጠቅሰው ብዙ ከብቶችና ፍየሎች በቤቶቹ ውስጥ መቃጠላቸውንና በርካታ ንብረት መውደሙን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ "ቂልጡ፣ ድቡስቃና አዲውድ የተባሉት መንደሮች በመድፍ ተደብድበዋል። የተወሰኑት ቤቶች ከተቀጣጠሉ በኋላ ታጣቂዎቹ እሳት በእጅ ይዘው እየዞሩ ቤት ለቤት ሲያቃጥሉ ተመልክቻለሁ" ብለዋል።
እንደ አቶ አደም ሁሉ አቶ ነጋም ሆን ተብለው በእሳት እንዲወድሙ የተደረጉት የነዋሪዎቹ ቤቶች በርካታ መሆናቸውን ይናገራሉ።
ሁለቱም ግለሰቦች ሰኞ ዕለት በነበረው ጥቃት ቀበሌያቸውን ለመከላከል ከግማሽ ቀን በላይ ከአማጺያኑ ጋር ከባድ የተኩስ ልውውጥ ካደረጉ በኋላ፣ በተኩስ ልውውጡ ከነዋሪዎቹ መካከል 14 ሰዎች መገደላቸውን እና አቶ አደምን ጨምሮ 16 የሚሆኑት ደግሞ እንደቆሰሉ ተናግረዋል።
ጨምረውም ጥቃት ሊፈጽሙ ከመጡት አማጺያን መካከልም በርካታ ታጣቂዎች መገደላቸውን የሚናገሩት ነዋሪዎቹ በአካባቢው የመከላከያ ሠራዊትም ሆነ የክልሉ ልዩ ኃይል እንዳልነበረ አረጋግጠዋል።
ነገር ግን ከነዋሪው ከባድ መከላከል ገጥሟቸው እንደነበር አቶ አደም ጠቅሰው "መንደሮቹን ያቃጠሉት እኛን እንደ ልዩ ኃይል በመቁጠር እና የአካባቢው ሰዎች ደግሞ ልዩ ኃይል የለም ስላሏቸው 'ዋሽታችሁናል' በሚል በበቀል ነው" ይላሉ።
አያይዘውም "አርሶ አደሩ በተለምዶ መሳሪያ የመታጠቅ ባህል ስላለው ራሱን በራሱ አደራጅቶ ነው አካባቢውን ለመከላከል የገጠማቸው" ብለዋል።
ሌላኛው የአካባቢው ነዋሪ እና በወርቄ ገበያ ታዳጊ ከተማ በመንግሥት የኃላፊነት ቦታ ላይ የነበሩ፣ አሁን በሌላ ቦታ የሚገኙና ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ግለሰብ ደግሞ ጥቃቱ በደረሰባቸው መንደሮች ቢያንስ እስከ 150 ቤቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ እና ከ800 እስከ 900 የሚጠጋ ነዋሪ እንዳለ ይገመታል ይላሉ።
ከዚህም በተጨማሪ አካባቢው ከፊል አርብቶ አደር በመሆኑ ነዋሪው በሺዎች የሚቆጠሩ ከብቶች እና ሌሎች የቤት እንስሳት እንዳሏቸው ተናግረዋል።
በተጨማሪም እኚሁ ግለሰብ እንዳሉት ከሆነ ከ50 በላይ የአርሶ አደር መኖሪያ ቤቶች በከባድ መሳሪያ ጥቃትና ሆን ተብሎ በእሳት እንዲቃጠሉ የተደረገ ሲሆን "አንድን ሽማግሌ ከቤት ውስጥ በሽቦ ታስረው ከቤታቸው ጋር አብረው ተቃጥለዋል" ሲሉ የሚያውቁትን ገልጸዋል።
በወቅቱ ከአማጺያኑ ጋር በነበረው ውጊያ ቆስለው አሁን በደሴ ሆስፒታል የሕክምና ክትትል እያደረጉ የሚገኙት አቶ አደም፣ "የስምንት ቤተሰብ አስተዳዳሪ ነኝ። እኔ አካባቢዬን ልከላከል ስታኮስ ቆሰልኩ። ከዚያም ወደ ደሴ ወንድሞቼ ይዘውኝ ለህክምና ሲመጡ መንገድ ላይ እንደደረስኩ ሚስቴ መውለዷን ነግረውኛል። አሁን ግን በምን ሁኔታ ላይ እንዳለች አላውቅም" ብለዋል።
በደቡብ ወሎ የተለያዩ አካባቢዎች ውስጥ በሕክምናና ከሰዎች ጋር ተጠግተው የሚገኙት ጥቃት ከተፈጸመባት አካባቢ የመጡት ግለሰቦች የስልክ ግንኙነት በመቋረጡ ስለቤተሰቦቻቸው የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የአካባቢው አስተዳዳሪዎች በአቅራቢያ ወደ ሚገኙ አጎራባች የክልሉ ወረዳዎች ተሰድደዋል። የራያ ቆቦ ወረዳም በህወሓት ታጣቂዎች እጅ በመውደቁ የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ ከአካባቢው ባለሥልጣናት ተጨማሪ መረጃ ማግኘት አልተቻለም።
ይህንን ክስተት በተመለከተ 'ዘ ቴሌግራፍ' ያወጣውን ዘገባ ተከትሎ እራሱን "የትግራይ ብሔራዊ መንግሥት" ብሎ የሚጠራ አካል ባወጣው መግለጫ አማጺያኑ የተባለውን ጥቃት እንዳልፈጸሙ አስተባብሏል።
ከጥቅምት ወር ጀምሮ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ጦርነት ውስጥ የገባውና በአሸባሪ ድርጅትነት የተፈረጀው የህወሓት ኃይሎች ጥቃቱን በተመለከተ "በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ የትኛውንም አይነት የጭካኔ ድርጊቶች በጽኑ እንደሚያወግዝ" ገልጾ የቀረበውን ክስ ውድቅ አድርጎታል።
ከዚህ በተጨማሪም በአማራ ክልል በሰላማዊ ሰዎች ላይ ተፈጽመዋል በተባሉ የወንጀል ድርጊቶች ዙሪያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሚሰየም አካል ገለልተኛ ማጣራት እንዲደረግ ጠይቋል።













