ሱዳን በኢትዮጵያ ሰላም ለማምጣት ጥረቷን እንደምትቀጥል ገለጸች

ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ

ሱዳን በኢትዮጵያ ያለውን ግጭት ለማሸማገል ያደረገችው ሙከራ ተቀባይነት ባያገኝም በጥረቷ እንደምትገፋበት ገለጸች።

የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ እንደተናገሩት አሁንም አገራቸው በኢትዮጵያ ያለው ግጭት በሰላማዊ መንገድ መፍትሔ እንዲያገኝ ግፊት ማድረጓን ትቀጥላለች።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨምረውም ሱዳን በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ጦርነት ለማስቆም ሁሉንም በሚያስማማ መንገድ ለማስቆም ሁለቱ ወገኖችን በማግኘት ጥረት ሲደረግ መቆየቱን አመልክተዋል።

ሱዳን በመንግሥትና በአማጺው ኃይል መካከል አሸማጋይ ለመሆን ጥረት እያደረገች መሆኗን ይፋ ማድረጓን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት ሐሳቡን ውድቅ ማድረጉ ይታወሳል።

ይህንንም በተመለከተ የጠቅላይ ሚንስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም በሰጡት ምላሽ ኢትዮጵያ ሱዳን ላይ እምነት መጣል የምትችልበት ሁኔታ ካልተፈጠረ በስተቀር እንደ ታማኝ አደራዳሪ ለመቀበል እንደምትቸገር መግለጻቸው ይታወሳል።

"ሱዳንን በአደራዳሪነት ለመውሰድ በቅድሚያ መተማመን ጉዳይ ላይ በጥልቀት መኬድ አለበት ብለን እናምናለን" ያሉት ቢልለኔ፤ ለማደራደርም ይሁን ለማሸማገል መሠረታዊው ነጥብ እምነት እንደሆነ ጠቅሰው፤ ቅድሚያ የሚሰጠውም የመተማመን ጉዳይ እንደሆነ አመልክተው ነበር።

ትግራይ ውስጥ ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ የተከሰተውን ወታደራዊ ግጭት ተከትሎ የሱዳን ወታደሮች በኢትዮጵያውያን ይዞታ ስር ወደነበሩ አወዛጋቢ የድንበር አካባቢዎች ዘልቀው በመግባት መቆጣጠራቸው ይታወሳል።

በዚህም ሳቢያ ኢትዮጵያ ወታደሮቹ ከድንበር አካባቢ ለቅቀው እንዲወጡና የድንበሩ ጉዳይ በውይይት እንዲፈታ በተደጋጋሚ ብትጠይቅም ሱዳን በቁጥጥሯ ስር ያስገባቻቸው ስፍራዎች የግዛቷ አካል እንደሆኑ በመግለጽ ወታደሮቿ እንደማይወጡ ስትገልጽ ቆይታለች።

በዚህም ሳቢያ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነትና መተማመን እንደሻከረና በኢትዮጵያ በኩል በሱዳን ባለሥልጣናት ላይ የነበረው እምነት እንደተሸረሸረ ቃል አቀባይዋ ተናግረው ነበር።

በኢትዮጵያ አቋም ደስተኛ ያልሆነችው ሱዳን ከሳምንት በፊት በኢትዮጵያ የሚገኙትን አምባሳደሯን ወደ ካርቱም መጥራቷን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቦ ነበር።

ለዚህም እንደ ምክንያትነት የተጠቀሰው በትግራይ በቀጠለው ጦርነት ለማደራደር ያቀረበችው ሃሳብ በኢትዮጵያ ባለስልጣናት ውድቅ መደረጉን ተከትሎ ነው።

የአገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ላይ ኢትዮጵያ የሱዳንን ጥረት ሙሉ በሙሉ ውድቅ ከማድረግ ይልቅ፤ ሱዳን ማድረግ የምትችለውን በመገንዘብ የያዘችውን አቋም እንድታሻሽል ጠይቆ ነበር።

ከሳምንታት በፊት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ጋር በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል የሚካሄደው ጦርነት ስለመስፋፋቱና በትግራይ ክልል እያሽቆለቆለ ስለመጣው የሰብዓዊ ሁኔታ በተመለከተ ያላቸውን ስጋት አንስተው ተወያይተው ነበር።

ከዘጠኝ ወራት በፊት በትግራይ ክልል ውስጥ በተቀሰቀሰውና ወደ አጎራባች ክልሎች በተስፋፋው ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወት ሳያልፍ እንደማይቀር ሲነገር በመቶ ሺህዎች ደግሞ ለመፈናቀልና ለረሃብ አደጋ ተዳርገዋል።

ሱዳን ግጭቱ በመሸሽ ከኢትዮጵያ የተሰደዱ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እያስተናገደች እንደሆነ የእርዳታ ድርጅቶች ገልጸዋል።