"ሱዳንን በአደራዳሪነት ለመውሰድ በቅድሚያ መተማመን አለብን"

የፎቶው ባለመብት, Office of the PM
ኢትዮጵያ ሱዳን ላይ እምነት መጣል የምትችልበት ሁኔታ ካልተፈጠረ በስተቀር ሱዳንን እንደ ታማኝ አደራዳሪ ለመቀበል እንደሚያስቸግር የጠቅላይ ሚንስትር ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም ተናገሩ።
"ሱዳንን በአደራዳሪነት ለመውሰድ በቅድሚያ መተማመን ጉዳይ ላይ በጥልቀት መኬድ አለበት ብለን እናምናለን" ብለዋል።
ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ኢትዮጵያ ሱዳንን እንደ አሸማጋይ ልትቀበል ትችል እንደሆነ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፤ ለማደራደርም ይሁን ለማሸማገል መሠረታዊው ነጥብ እምነት እንደሆነ ጠቅሰው፤ ቅድሚያ የሚሰጠውም የመተማመን ጉዳይ እንደሆነ አስረግጠዋል።
በተለይም የሱዳን ወታደሮች ወደ ኢትዮጵያ ግዛት መግባታቸውን ተከትሎ በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ያለው ግንኙነት እንደሻከረ እና በበላይ አመራሮች ዘንድ እምነት እንደተሸረሸረ ቢልለኔ ጠቁመዋል።
ሱዳን ትሪቢዩን፤ የሱዳን መንግሥት የፌደራሉን መንግሥት እና የህወሓት አማጺያንን ለማሸማገል ፍላጎት እንዳለ አስነብቧል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ጋር በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ መወያየታቸው መዘገቡ አይዘነጋም።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንቶኒ ብሊንከን እና ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ሁሉም ወገኖች በስምምነት ላይ የተመሠረተ የተኩስ አቁም ላይ እንዲደርሱ ለማበረታታት፣ ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ውይይት እና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና አንድነት ለማስጠበቅ እንዲሁም እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ያልተገደበ ተደራሽነት እንዲኖር ለመሥራትም ተስማምተዋል።
በሌላ በኩል ህወሓት የተኩስ አቁም ለማድረግ ባለ ሰባት ነጥብ ቅድመ ሁኔታዎችን በቅርቡ አሻሽሎ ማቅረቡን በተመለከተ "አሸባሪ ቡድን ለሕጋዊ መንግሥት ሰባት ቅድመ ሁኔታ ሊያቀርብ አይችልም" ሲሉ ቢልለኔ ምላሽ ሰጥተዋል።
የፌደራል መንግሥት ከሳምንታት በፊት በትግራይ የተናጠል ተኩስ ካወጀ በኋላ ህወሓት ተኩስ ለማቆም ሁለት ጊዜ ቅድመ ሁኔታዎችን ማቅረቡ አይዘነጋም።
የጠቅላይ ሚንስትር ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ በበኩላቸው መንግሥት የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ እንዲሁም የክረምት የእርሻ ወቅትን ታሳቢ በማድረግ የተናጠል ተኩስ ቢያውጅም ህወሓት ግን በአማራ እና በአፋር ክልሎች ጥቃት መክፈቱን አንስተዋል።
መንግሥት እና አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው ህወሓት "እኩል አይደሉም" በማለት፤ በቡድኑ የቀረቡትን ቅድመ ሁኔታዎች "ሰላም ለማውረድ የሚቀርቡ ጥያቄዎች አይደሉም" ሲሉ አጣጥለዋቸዋል።
የፌደራል መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁሙ ምላሽ እንዳላገኘና የመጀመሪያው እርምጃ የተኩስ አቁሙን መቀበል መሆን እንደሚገባውም አስረግጠዋል።
የሰብዓዊ እርዳታ
ሌላው በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ የተነሳው ነጥብ ወደ ትግራይ ሰብዓዊ እርዳታ የሚደርስባቸው መንገዶች ጉዳይ ነው።
በሱዳን በኩል የሰብዓዊ እርዳታ መተላለፊያ (ኮሪደር) እንዲከፈት ጥያቄ ቀርቧል? የመንግሥት ምላሽስ ምንድን ነው? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው የጠቅላይ ሚንስትር ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ፤ በሱዳን በኩል የሰብዓዊ እርዳታ መተላለፊያ እንዲከፈት ዓለም አቀፍ ጥያቄ እንዳልቀረበ ተናግረዋል።
"ህወሓት የአፋር መንገድ አማራጭ አይደለም። ተዘግቷል የሚል ፕሮፓጋንዳ እያሰራጨ ነው" ሲሉም አክለዋል።
መንግሥት በየትኛው መንገድ የሰብዓዊ እርዳታ ይተላለፍ የሚለውን የመወሰን መብት እንዳለው አስረግጠው "አፋር ለጅቡቲ ወደብ የቀረበው ስለሆነ የተሻለውና ተመራጩ መንገድ ነው" ብለዋል።
"መንግሥት ሰብዓዊ እርዳታ በአፋር በኩል እንደከለከለ ተደርጎ የሚቀርበው ሐሰት ነው" ሲሉም አክለዋል።
የፌደራል መንግሥት ወደ ትግራይ እርዳታ የሚገባባቸውን መንገዶች እየዘጋ ነው የሚል ክስ ሲቀርብበት፤ በምላሹ የህወሓት ኃይሎች እርዳታ እንዳይደርስ ከማሰናክል ባሻገር ጥቃት እየሰነዘሩም ነው ሲል ይወነጅላል።












